የስፖርት ዘገባ፤ ነሐሴ-25-2007 ዓ.ም | ስፖርት | DW | 31.08.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ፤ ነሐሴ-25-2007 ዓ.ም

ቤጂንግ ውስጥ በተካሄደው የሴቶች የአምስት ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከ1-3 ተከታትለው በመግባት ድል አስመዝግበዋል። አትሌት አልማዝ አያና ተፎካካሪዎቿን በረዥም ርቀት በመቅደም 14 ደቂቃ ከ26 ሰከንድ በሆነ ሰዓት ሩጫውን በአንደኝነት አጠናቃለች።

ሁለተኛ ሰንበሬ ተፈሪ ሦስተኛ ደግሞ ገንዘቤ ዲባባ በመግባት የውድድሩ አሸናፊዎች ሆነዋል። ኢትዮጵያ ከዚህ ሩጫ በፊትም ሌላ አስደሳች ድል ተቀዳጅታለች። በሴቶች የማራቶን ውድድር ማሬ ዲባባ አንደኛ በመውጣት ለኢትዮጵያ 2ኛውን ወርቅ አስመዝግባ ነበር።

የብሪታንያው አትሌት ሞ ፋራህ በ5 ሺህ እና 10 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር አይበገሬ መሆኑን በቤጂንጉ ዉድድር ላይ በድጋሚ አስመስክሮአል። ቤጂንግ ውስጥ በተከናወነው የአምስት ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር ሞ ፋራህ ወርቁን ሲወስድ በኦሎምፒክ አልያም በዓለም አቀፍ ፉክክር በ5 ሺህ እና በ10ሺህ ሜትር በተከታታይ 7ኛ ድል ሆኖ ተመዝግቦለታል።

ሞ ፋራህ በ5 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር የዓለም ሻምፒዮና ለሦስተኛ ጊዜ በተከታታይ የወርቅ ተሸላሚ በመሆን ታሪክ ሠርቷል።

የ32 ዓመቱ ትውልደ-ሶማሊያ የብሪታንያ ዜጋ ሞ ፋራህ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2011 በዴጉ የ10 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር በኢትዮጵያዊው አትሌት ኢብራሒም ጄላን ከተሸነፈ ወዲህ በዘርፉ የሚረታው አልተገኘም። በቤጂንጉ የወንዶች የ5 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር ሐጎስ ገብረሕይወት ለኢትዮጵያ የነሐስ ሜዳሊያ አስገኝቷል። በዚህ ውድድር ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነው የኬንያው አትሌት ካሌብ ምዋንጋኚ ንዲኩ ነው። አትሌት ዮሚፍ አጄልቻ በአራተኛነት አጠናቋል። ሌላኛው አትሌት ኢማነ መርጋ በ13ኛነት ውድድሩን ጨርሷል። በሳምንቱ መጨረሻ የተካሄደዉን የስፖርት እንቅስቃሴ በተመለከተ የለንደንዋ ወኪላችን ያጠናቀረችዉን ሙሉ የድምፅ ዘገባ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።

ሀና ደምሴ

አዜብ ታደሰ