የስፖርት ዘገባ፤ ነሐሴ 18 ቀን፣ 2007 ዓ.ም. | ስፖርት | DW | 24.08.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ፤ ነሐሴ 18 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.

የድሬዳዋ ነዋሪዋ ሴት አሠልጣኝ ቡድኗን ወደ ፕሬሚየር ሊግ በማስገባት በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሆናለች። የኢትዮጵያ አትሌቶች በቻይና ቤጂንግ የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ቅኝት ተደርጎበታል። የስፖርት ተንታኝ ትንታኔ ይሰጥበታል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ሲቲ ስጋሴውን ተያይዞታል። ጆን ቴሪን በቀይ ካርድ ያጣው ቸልሲ

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:54

የስፖርት ዘገባ፤ ነሐሴ 18 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.

ትናንት ማሸነፍ ችሏል፤ ከማንቸስተር ሲቲ ግን በአምስት ነጥብ ተበልጧል። ሊቨርፑል እና አርሰናል ዛሬ ተስተካካይ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ቦሩስያ ዶርትሙንድ አሁንም በሰፋ የግብ ልዩነት አሸንፏል።በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ከአርሰናል እና ሊቨርፑል በስተቀር ሁሉም ቡድኖች ሦስተኛ ጨዋታዎችን አኪያሂደዋል። ማንቸስተር ሲቲ በሦስት ጨዋታዎች 9 ነጥብ እና 8 ግቦችን መሰብሰብ ችሏል። ዋነኛ ተፎካካሪዎቹ ማንቸስተር ዩናይትድ እና ሊቨርፑል በቅርብ ርቀት ላይ ናቸው። ቸልሲ 9ኛ ፣ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው አርሰናል 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ዝርዝር ይኖረናል። በቅድሚያ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ታሪክ ስላስመዘገበችው ሴት አሠልጣኝ።

የእግር ኳስ ስፖርትን ገና በልጅነቷ በአሸዋማዋ የድሬዳዋ ሜዳዎች ከወንዶች ጋር የጨርቅ ኳሶችን በመለጋት ነበር የጀመረችው። የድሬዳዋ ከነማ አሠልጣኝ መሠረት ማኒ። ዘንድሮ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ ፍልሚያ ጅማ አባቡናን 2 ለባዶ በመርታት ቡድኗን ወደ ፕሬሚየር ሊግ ማስገባት ችላለች። በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ስኬታማ ሴት አሠልጣኝ ሆናም ታሪክ ሠርታለች። መሠረት በእግር ኳሱ ዓለም ለ30 ዓመታት ግድም ቆይታለች።ድሬድዋ ደቻቱ የሚባለው ሠፈር አካባቢ ተወልዳ ያደገችው መሠረት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በለገሐሬ ትምህርት ቤት ነው ያጠናቀቀችው። ኹለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በድሬዳዋ አጠቃላይ ኹለተኛ ደረጃ ፈጽማለች። መሠረት ኮሌጅ መግባትም ችላ ነበር። ሆኖም የኳሱ ፍቅር አይሎባት ሙሉ ለሙሉ ወደ ኳስ ስፖርት አዘነበልኩ ትላለች። ሴት የእግር ኳስ አሠልጣኝ ከሆነችበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ፈተና ገጥሟታል።

የድሬዳዋ ከነማ አሰልጣኝ መሠረት ለረዥም ጊዜ የአሠልጣኝነት ስልጠና አልወሰደችም ነበር። ዘግየት ብሎ ግን የአሠልጣኝነት ስልጠናዎችን በተለያየ ደረጃ መውሰዷን ገልጣለች። መሰረት የድሬዳዋ ከነማ ቡድን አመራር ጠንካራ ፉክክር በሚታይበት ፕሬሚየር ሊግ የሚጠብቃትን ፈተና እንደምትወጣው አምነው ኃላፊነት መስጠታቸው ብርታት እንደሰጣት ትናገራለች።ዘንድሮ ወደ ፕሬሚየር ሊጉ ያለፉት ቡድኖች ድሬዳዋ ከነማ እና ሆሳዕና ከተማ ናቸው። አሠልጣኝ መሠረት በሚቀጥለው ዓመት የውድድር ዘመን ወደ ፕሬሚከር ሊግ ያሳደገችውን ቡድኗ ድሬዳዋ ከነማን በፕሬሚየር ሊጉ እንዲቆይ የማድረግ ዕቅድ ይዛ እንደተነሳች ገልጣለች። ከባድ ፈተናም ከፊቷ እንደተደቀነ።

በስፖርቱ ዘርፍም ሆነ በሌላ መስክ የተሰማሩ ሴቶች የሚፈልጉበት ቦታ ለመድረስ ጠንክረው መሥራት እንዳለባቸው ትመክራለች።

አትሌቲክስ

ኢብራሂም ውድድሩን በተለይ ኢትዮጵያ የምታኪያሂደውን በአንክሮ እየተከታተለ እንደሚገኝ ጠቅሷል። ኢትዮጵያ የተጠበቀውን ውጤት አለማስገኘቷ በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ላይ ጥያቄ ሊያስነሳ እንደሚችል አስገንዝቧል።

በማራቶን ኢትዮጵያ አንድ ሜዳሊያ እንደምታገኝ ጠብቆ እንደነበር ገልጧል። በእርግጥም አትሌት የማነ ጸጋዬ ኹለተኛ በመውጣት ውጤት አስመዝግቧል። በዚህ የማራቶን ውድድር አሸናፊ የሆነው የኤርትራው ሯጭ ግርማይ ገብረሥላሴ ነበር። በቤጂንጉ የዛሬ የ10 ሺህ ሜትር የሴቶች ውድድር አትሌት ገለቴ ቡርቃ በኬኒያዊቷ ቪቪያን ቼሩዮት ለጥቂት ተቀድማ የብር ሜዳይ አስገኝታለች። ቪቪያን ልጅ ከወለደች በኋላ ያደረገችውን የመጀመሪያ ፉክክሯ በድል ጀምራለች። ዩናይትድ ስቴትሷ ኤሚሊ ነሐስ ሜዳይ ተሸላሚ ሆናለች።እስካሁን አጠቃላይ ውድድሩን ኬንያ በ6 ሜዳሊያ ትመራለች። ኢትዮጵያ በኹለት ብር 11ኛ ደረጃ ላይ ነው የምትገኘው። ቅዳሜ እለት የጀመረው የቤጂንጉ ውድድር የፊታችን እሁድ ይጠናቀቃል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ውድድር ትናንት ማንቸስተር ሲቲ ኤቨርተንን 2 ለባዶ በመርታት ነጥቡን ወደ 9 አሳድጓል። በሦስቱም ጨዋታዎች አንድም ግብ አልተቆጠረበትም። ባለፈው ሳምንት በማንቸስተር ሲቲ 3 ለባዶ የተረታው ቸልሲ ትናንት ዌስት ብሮሚችን 3 ለ2 ማሸነፍ ችሏል። ዋትፎርድ እና ሳውዝሐምፕተን ያለምንም ግብ ተለያይተዋል።
ቅዳሜ እለት ማንቸስተር ዩናይትድ በተመሳሳይ ከኒውካስል ጋር ዜሮ ለዜሮ በመውጣት ነጥብ ተጋርቷል። ሊቨርፑል እና አርሰናል ተስተካካይ ሦስተኛ ጨዋታቸውን ዛሬ በኤሚሬትስ ስታዲየም ያከናውናሉ። ይኽ ጨዋታ አርሰናል ከ13ኛ ደረጃ በመውጣት ወደላይ ለመስፈንጠር፤ ሊቨርፑል ደግሞ ከመሪው ማንቸስተር ሲቲ ጋር ተስተካክሎ በነጥብ ብቻ ለመበላለጥ የሚያርጉት የሞት ሽረት ግጥሚያ ነው።

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ሳምንት የመጀመሪያ ግጥሚያውን ከግላድባኅ ጋር በማድረግ 4 ለዜሮ በድል ያጠናቀቀው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ኹለተኛ ጨዋታው ላይ ደግሞታል። ትናንት ኢንግሎሽታድትን 4 ለባዶ ጉድ አድርጎታል። ኢንግሎሽታድት ወደ ቡንደስሊጋው ዘንድሮ ያደገ ቡድን ነው።ከትናንት በስትያ ባየር ሙይንሽን ሆፈንሐይምን 2 ለ1 በማሸነፍ ነጥቡን ወደ ስድስት አሳድጓል። በግብ ልዩነት ግን በቦሩስያ ዶርትሙንድ ተበልጧል።

ሪያል ማድሪድ በቀድሞው የሊቨርፑል አሠልጣኝ ራፋኤል ቤኒቴዝ እየተመራ ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረገው ጨዋታ ግብ ማስገባት ተስኖት ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል።

በፎርሙላ አንድ የቤልጂየም የመኪና ሽቅድምድም ሌዊስ ሀሚልተን ኒኮ ሮዝበርግን በመቅደም አንደኛ ወጥቷል።
90 ደቂቃ በፈጀ የሜዳ ቴኒስ ግጥሚያ ሮጀር ፌዴሬር ኖቫክ ጆኮቪችን ትናንት ዩናይትድ ስቴትስ ኦሂዮ ውስጥ 7ለ6 እና 6 ለ3 አሸንፎታል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic