የስፖርት ዘገባ፤ ነሐሴ 11 ቀን፣ 2007 ዓ.ም. | ስፖርት | DW | 17.08.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ፤ ነሐሴ 11 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፤ ቸልሲ ዘንድሮ አጀማመሩ አላመረም። እሁድ በኹለተኛ ጨዋታው በማንቸስተር ሲቲ ተቀጥቶ ወደ 16ኛ ደረጃ አሽቆልቁሏል። ኹለቱ ማንቸስተሮች፤ የመጀመሪያ ሳምንት ውጤታችንን ከመድገም ማን አግዶን ብለዋል። ማንቸስተር ሲቲ 3 ለዜሮ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ ደግሞ 1 ለባዶ በድጋሚ አሸንፈዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:08
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
09:08 ደቂቃ

የስፖርት ዘገባ፤ ነሐሴ 11 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.

በመጀመሪያው ጨዋታ ድል የቀናው ሊቨርፑል ዛሬ ከቦርንመስ ጋር ይገጥማል። ቦርንመስን ከዚህ ቀደም ለስድስት ጊዜያት አግኝቶ ስድስቱንም ጊዜ አደባይቶታል። በጀርመን ቡንደስሊጋ የመጀመሪያ ጨዋታ ኃያሉ ባየር ሙይንሽን ሐምቡርግን የግብ ጎተራ አድርጎታል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በአዲስ አሰልጣኝ በግብ ተንበሽብሿል። የስፔን ሱፐር ካፕ ዋንጫ ዛሬ ማምሻውን ይከናወናል። ባርሴሎና አትሌቲኮ ቢልባዎን ይበቀል ይኾን? ሌሎች ዘገባዎችንም አካተናል!

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት የእግር ኳስ ግጥሚያ ትናንት አርሰናል ክሪስታል ፓላስን 2 ለ1 አሸንፎ ባለፈው ሳምንት የተሰበረ ቅስሙን ጠግኗል። አርሰናል ባለፈው ሳምንት በዌስትሐም 2 ለባዶ ነበር የተሸነፈው። በትናንቱ ጨዋታ ተደጋጋሚ ሙከራ ያደረገው አርሰናል የመጀመሪያዋን ግብ ያስቆጠረው በ16ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ኦሊቨር ጂሮድ ከጀርመናዊው ሜሱት ኦይትሲል በግራ በኩል የተላከለትን ኳስ አየር ላይ እንዳለች በአክሮባት ተጠምዝዞ በግራ እግሩ በመምታት በግቡ ግራ ጠርዝ ከመረብ አሳርፏታል። ለግብ ጠባቂው ያልጠበቀው ውርጅብን ኾኖበታል።

ሠርጂዮ አጉዌሮ

ኦሊቨር ጂሮች በስተቀኝ

አርሰናል አንድ ለዜሮ ሲመራ የቆየው እስከ 27ኛው ደቂቃ ድረስ ብቻ ነበር። የክሪስታል ፓላሱ ጆይል ዎርድ ከመሀል በኩል መሬት ለመሬት አክርሮ የመታትን ኳስ የአርሰናሉ ግብ ጠባቂ ፔተር ቼክ ከግብ ሊታደጋት አልቻለም። ኳሷ በስተቀኝ በኩል መረቡ ላይ ሰፍራለች።

በኹለተኛው አጋማሽ 55ኛው ደቂቃ ላይ አሌክሲስ ሳንቼስ በግቡ ግራ ጠርዝ በኩል ያገኛትን ኳስ በድንቅ ኹኔታ በጭንቅላቱ በመግጨት ነበር ወደ ግቡ የላካት። የክሪስታል ፓላሱ ዴሚየን ዴላኒ ኳሷን አድናለሁ ሲል የዘረጋው እግሩ በገዛ መረቡ ላይ ግብ እንዲቆጠር ሰበብ ሆኖበታል። በዚህም አርሰናል ክሪስታል ፓላስን 2 ለ1 ማሸነፍ ችሏል። ኹለተኛዋ ግብ የተቆጠረችው በክሪስታል ፓላስ የመከላከል ድክመት ነበር።

ቸልሲ ዘንድሮ አጀማመሩ አልሰመረም። ትናንት በማንቸስተር ሲቲ 3 ለዜሮ ተቀጥቷል።ባለፈው ሳምንትም ከስዋንሲ ጋር ተጋጥሞ ነጥብ ለመጋራት ተገዶ ነበር። በማንቸስተር ሲቲ እና ቸልሲ ጨዋታ የመጀመሪያዋ ግብ የተቆጠረችው በ31ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። የማንቸስተር ሲቲው ሠርጂዮ አጉዌሮ በአራት የቸልሲ ተጨዋቾች ተከቦም ነው ግቧን ማስቆጠር የቻለው።

ሠርጂዮ አጉዌሮ

ሠርጂዮ አጉዌሮ

በኹለተኛው አጋማሽ 79ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተላከችውን ኳስ የማንቸስተር ሲቲው ቪንሰንት ኮምፓኒ በጭንቅላት ገጭቶ ከመረብ ማአሳርፏታል። ቪንሰንት ባለፈው ሣምንት ማንቸስተር ሲቲ ዌስትብሮሚችን በተመሳሳይ 3 ለባዶ ባሸነፈበት ጨዋታ የመጀመሪያውን ግብ አስቆጥሮ ነበር። የቤልጂየም ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊ የኾነው ይኽ የ29 ዓመት ወጣት ተከላካይ ዘንድሮ ማንቸስተር ሲቲ ባደረጋቸው ኹለት ጨዋታዎች ኹለት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።

ሦስተኛዋን ግብ በ85ኛው ደቂቃ ላይ ፈርናንዲንሆ ከበስተግራ በኩል በመምታት በአግዳሚው በስተቀኝ ከመረብ ማሳረፍ ችሏል። ኳሷ ፈርናንዲንሆ እግር ላይ ከማረፏ በፊት የማንቸስተር ሲቲ ተጨዋቾች የማጥቃት ሙከራ ጥረታቸው የሚደነቅ ነበር። በዚህ ጨዋታ የቸልሲው አሠልጣኝ ጆሴ ሞሪኒሆ የ34 ዓመቱ አምበል ጆን ቴሪን በመጀመሪያው አጋማሽ ቀይረውታል። ጆን ቴሪ ከ177 ጨዋታዎች ወዲህ ሲቀየር ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ሊቨርፑል

ሊቨርፑል

ጋዜጠኞች ጆን ቴሪ ለምን ተቀየረ ብለው ላቀረቡላቸው ጥያቄ የቸልሲው አሠልጣኝ ጆሴ ሞሪኒሆ መልስ ሲሰጡ ቆጣ ብለው ነበር። «በርካታ ጥያቄዎችን ለራፋኤል ቤኒቴዝ፣ ለአንድሬ ቪላ ቦዋ አለያም ለሮቤርቶ ዲ ማቴዎ ትጠይቁ እንደሆን አላውቅም» አሉ ጆሴ ሞሪንሆ ተቆጥተው። የጠቀሷቸው ሰዎች በሙሉ የቸልሲ የቀድሞ አሠልጣኞች ነበሩ። «መጠየቅ የሌለባችሁ እኮ እኔን ነበር። ጆንን በእያንዳንዱ ጨዋታ ያሰለፍሁ፣ አምበል ያደረግሁት፣ ከሌሎች አሠልጣኞች ጋር ከነበረው አስቸጋሪ ኹኔታ እንዲወጣ ያስቻልሁት እኮ እኔ ነኝ።» ሲሉ ለምን ከጋሪ ይልቅ ጆን ቴሪ ተቀየረ ለሚለው ጥያቄ መልስ ሰጥተዋል።

ጆሴ ሞሪኒሆ በትናንቱ ጨዋታ የተሸነፍነው ተበልጠን አይደለም፤ ውጤቱም «የተሳሳተ ውጤት » ነው በማለት ሽንፈታቸውን እንደማይቀበሉ ተናግረዋል። አያይዘውም «በጨዋታ በልጠን ነበር። እናም ችግር ውስጥ መኾናቸውን ሲያውቁ አጉዌሮን እና ራሂም ስተርሊንግን ቀይረዋል። በማገገም ጨዋታውን ለመቆጣጠር ሞክረዋል» ብለዋል።

ሊቨርፑል ዛሬ ማምሻውን ከቦርንማውዝ ጋር ይገጥማል። ቦርንማውዝ ከሊቨርፑል ጋር ለስድስት ጊዜያት ተገናኝቶ አንድም ጊዜ ማሸነፍ አልቻለም። በዚህም መሠረት ሊቨርፑል የዛሬውን ጨዋታ አሸንፎ ነጥቡን ወደ ስድስት በማሳደግ አጋጣሚውን ይጠቀማል ተብሎ ይታሰባል።

ቦሩስያ ዶርትሙንድ

ቦሩስያ ዶርትሙንድ

የጀርመን ቡንደስ ሊጋ ዐርብ እለት ኃያሉ ባየር ሙይንሽን ሐምቡርግን 5 ለባዶ ባንኮታኮተበት ጨዋታ ተጀምሯል። ቅዳሜ ዕለት በተደረጉ ጨዋታዎች ባየር ሌቨርኩሰን ሆፈንሀይምን 2 ለ1 አሸንፏል። ከ33 ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ቡንደስሊጋው ዘንድሮ የተመለሰው ዳርምሽታትድ ከሐኖቨር 2 እኩል ተለያይቷል። ቤርሊን አውስቡርግን እንዲሁም ኢንግሎሽታድት ማይንትስን 1 ለባዶ ረትተዋል። ኢንግሎሽታድት ዘንድሮ ለቡንደስ ሊጋው አዲስ ቡድን ነው። ከታች ያደገ ቡድን በመኾኑ የመጀመሪያ ጨዋታውን አሸንፎ ሦስት ነጥብ በማግኘቱ አድናቆት አትርፏል። ሻልከ ቬርደር ብሬመንን 3 ለባዶ ማሸነፍ ችሏል።

የረዥም ጊዜ ስኬታማ አሠልጣኙ ዬርገን ክሎፐን ባለፈው የውድድር ዘመን ደካማ ውጤት ምክንያት ያጣው ቦሩስያ ዶርትሙንድ በአዲስ አሰልጣን አዲስ ምዕራፍ አስመዝግቧል። አዲሱ አሠልጣኝ ቶማስ ቱሽል ቡድናቸው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን 4 ለዜሮ እንዳልነበረ ሲያደርግ የመጀመሪያ ድላቸውን በልዩ ኹናቴ አስበዋል። ለቦሩስያ ዶርትሙንድ የመጀመሪያዋን ግብ በ4ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ማርኮ ሮይስ ቡድናቸው ለቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ትልቅ ግምት ሰጥቶ ወደ ሜዳ መግባቱን ጠቅሷል።

አትሌት ኤልቫ አቤይለገሰ

አትሌት ኤልቫ አቤይለገሰ

«በዚህም አለ በዚያ ከፍተኛ ብቃታችንን በማሳየት ነው ጨዋታውን መጀመር የፈለግነው። ግላድባኅ እጅግ ጠንካራ ቡድን እንደኾነ እናውቃለን። የጨዋታ ቴክኒካቸው እጅግ በጣም ጥሩ ነው። በኹለት መስመር የሚሰሩት የአራት ተጨዋቾች አጥር በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም። በዚያ ላይ በመልሶ ማጥቃት በሚገባ ተክነውበታል። ብዙ ኳስ መቆጣጠር የቻልን ይመስለኛል። ትክክለኛዋ ቅጽበት ደርሳ በፍጥነት ወጣ እያልን እስክንጫወት ድረስ በትዕግስት ነው የጠበቅነው። ያን በማድረጋችን በደንብ ነው የተሳካልን። ግብም ማስቆጠርም ችለናል። »

በትናንትናው የቡንደስ ሊጋ ግጥሚያ ዎልፍስቡርግ አይንትራኅት ፍራንክፉርትን 2 ለ1 አሸንፏል። የቦን ከተማ አጎራባቿ የኮሎኝ ከተማ ቡድን ኮለኝ ሽቱትጋርትን 3 ለባዶ ድል አድርጓል።

ለስፔን ሱፐር ካፕ ፍጻሜ ግጥሚያ አትሌቲኮ ቢልባዎ እና ባርሴሎና ዛሬ ምሽት ይገናኛሉ። በመጀመሪያው ግጥሚያ ባርሴሎና በአትሌቲኮ ቢልባዎ የ4 ለባዶ የሽንፈት መሪር ጽዋን ተጎንጭቷል። በመጀመሪያው ጨዋታ ለአትሌቲኮ ቢልባዎ ሦስት ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ሔትሪክ የሠራው አሪትዝ አዱሪዝ የዛሬውን ጨዋታ አሸንፈን ዋንጫውን ካነሳን በእግር ኳስ የጨዋታ ዘመኔ ምርጡ ቀን ይኾናል ብሏል። ባርሴሎና በበኩሉ የዛሬውን ዋንጫ በእጁ ለማስገባት የሞት ሽረት ማድረጉ አይቀርም።ባርሴሎና ዛሬ ማታ ካሸነፈ ዘንድሮ የሰበሰባቸው ዋንጫዎቹን ወደ አምስት ከፍ ያደርጋል ማለት ነውባርሴሎና በሚቀጥለው ሣምንት ለስፔን ላሊጋ ወሳኝ ግጥሚያ ቢኖርበትም፤ አሠልጣኝ ሉዊስ ኤንሪኬ ግን በዛሬው ጨዋታ ለማሸነፍ የግድ ወሳኝ ተጨዋቾቻቸውን ለማሰለፍ ይገደዳሉ። በዛሬው ጨዋታ የመሀል ተመላላሹ አድሪያኖ በጀርባ ችግር አይሰለፍም ተብሏል።

አንዲ ሙራይ

አንዲ ሙራይ

የጣሊያን ሴሪኣ የፊታችን ቅዳሜ ማምሻውን በሮማ እና ሔላስ ቬሮና ግጥሚያ ይጀምራል። ዘግየት ብሎም ላትሲዮ እና ቦሎኛም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።

በሜዳ ቴኒስ ጨዋታ አንዲ ሙራይ ኖቫክ ጄኮቪችን 6-4 እና 6-3 አሸንፎታል። አንዲ ሙራይ ኖቫክ ጄኮቪችን በማሸነፉ ለስምንት ጊዜያት ያጋጠመውን ተከታይ ሽንፈት መቋጫ አበጅቶለታል።

በአትሌቲክስ ሩጫ ቱርክን ወክላ የምትሮጠው ኤልቫ አቤይለገሰ ኃይል ሰጪ መድሐኒት በመጠቀም ተጠርጥራ ምርመራ እየተደረገባት ነው። ትውልዷ ከኢትዮጵያ ሆኖ ለቱርክ የምትሮጠው ኤልቫን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2007 የኦሳካ ሩጫ ውድድር በ10000 ሜትር የብር ሜዳሊያ አግኝታ ነበር። በ2007ቱ ውድድር የወርቁን ሜዳሊያ ያጠለቀችው ጥሩነሽ ዲባባ ናት።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic