የስፖርት ዘገባ፤ ሰኔ 29 ቀን፣ 2007 ዓ.ም. | ስፖርት | DW | 06.07.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ፤ ሰኔ 29 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.

በቱር ደ ፍሯንስ የብስክሌት ሽቅድምድም ዘንድሮ 2 ኤርትራውያን ተሳታፊ ሆነዋል። ሁለቱም ከፈረንሳይ የሚሉት አላቸው። ገንዘቤ ዲባባ እና አልማዝ አያና ከፍተኛ ፉክክር ባደረጉሩበት የፈረንሳዩ ዲያመንድ ሊግ የ5000 ሜትር የሩጫ ውድድር ውጤት አልማዝ ደስተኛ አልነበረችም። ፉክክሩንና ውጤቱን በተመለከተ የስፖርት ጋዜጠኛ ከአዲስ ሰበባ ትንታኔ ሰጥቷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:02
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
11:02 ደቂቃ

የስፖርት ዘገባ፤ ሰኔ 29 ቀን፣ 2007 ዓ.ም

ፈረንሳይ ፓሪስ ውስጥ ቅዳሜ የተደረገው የዳያመንድ ሊግ የአትሌቲክስ ፍልሚያ የዓለም ክብርወሰን ባይሰበርበትም ኢትዮጵያውያቱ ተፎካካሪዎችን ግን እርስ በርስ እጅግ አታግሏል። ውድድሩ እጅግ በጣም በጉጉት እንዲጠበቅ ያደረገው ምን ነበር? የፕላኔት ስፖርት ሬዲዮ መሰናዶ አዘጋጅ እና አቅራቢ ምሥግናው ታደሰ በተለይ የመሠረት ደፋር እና የጥሩነሽ ዲባባ በወሊድ ምክንያት ተሳታፊ አለመሆን ካለፉት ሁለት ዓመታት አንስቶ ገንዘቤ ዲባባ ገና እንድትወጣ አስችሏታል ብሏል። አሁን ደግሞ አትሌት አልማዝ አያና ጠንካራ ተፎካካሪ ሆና ብቅ ብላለች ሲል አክሏል።

አትሌት ገንዘቤ ዲባባ

አትሌት ገንዘቤ ዲባባ

ከፍተኛ ፉክክር የታየበት የፓሪሱ ዳያመንድ ሊግ የ5000 ሜትር የሩጫ ውድድር ሊጠናቀቅ አንድ ዙር ሲቀረው አትሌት ገንዘቤ ዲባባ ተፈትልካ በመውጣት ብቃቷን አሳይታለች። ከፊት ከፊት ትመራ የነበረችው አልማዝ አያናን በመራቅም የአንደኛነቱን ክብር ልትቀዳጅ ችላለች።

ውድድሩን ከፊት ከፊት ሆና በመምራት በስተመጨረሻ ሁለተኛ የወጣችው አትሌት አልማዝ አያና በውጤቱ ቅሬታ እንደተሰማት ለፓሪስ ወኪላችን ሃይማኖት ጥሩነህ ገልጣ ነበር።

በተለይ በአትሌቲክስ ዘርፍ ትኩረት የሚያደርገው ጋዜጠኛ ምሥግናው ታደሰ የአትሌት አልማዝ አያናን ቅሬታ እና የገንዘቤን ድል በተመለከተ ልምድ እና ብልጠት ሚና መጫወቱን ጠቁሟል። ገንዘቤ ዲባባ በፓሪሱ የዳያመንድ ሊግ የ5000 ሜትሩን የሩጫ ውድድር ለማጠናቀቅ የፈጀባት ጊዜ 14:15.41 ነበር። አልማዝ አያና ሁለተኛ የወጣችው በ14:21.97 በመግባት ነበር።

ብስክሌት

በዘንድሮ የቱር ደ ፍሯንስ የብስኪሌት ሽቅድምድም ሁለት ኤርትራውያን ብስክሌተኞችን ጨምሮ አምስት የአፍሪቃ ተወዳዳሪዎች ብቅ ማለታቸው በዓለም የስፖርት ዜና መነጋገሪያ ሆኖ ነው የሰነበተው። MTN Qhubeka በተሰኘው ቡድን ውስጥ የሚገኙት ሁለቱ ኤርትራውያን የብስክሌት አሽከርካሪዎች ዳንኤል ተክለኃይማኖት እና መርሐዊ ቅዱስ ይባላሉ። ዳንኤል ከቱር ደ ፍሯንስ ውድድር ልምድ ይቀስም እንደሆን ተጠይቆ የሚከተለውን ብሏል።

የቱር ደ ፍሯንስ የብሽክሌት ሽቅድምድም

የቱር ደ ፍሯንስ የብሽክሌት ሽቅድምድም

«እንደሚመስለኝ ጥሩ ልምድ አለኝ፤ ስለዚህ ከአሁን በኋላ መማር የሚያስፈልገኝ አይመስለኝም። በቡድኔ ውስጥ ከሚገኙ ታላላቅ ፕሮፌሽናል ብስክሌተኞች ቀደም ሲልም ቢሆን በቂ ልምድ አካብቼያለሁ። በውድድሩ በመዝለቅ ቡድኔን መደገፉ ብሎም ለራሴ ወደ ቀጣይ ዙሮች መሸጋገር ላይ ነው የማተኩረው።»

ከቱር ደ ፍሯንስ ተወዳዳሪዎች እጅግ ወጣቱ እንደሆነ የሚነገርለት የ20 ዓመቱ መርሐዊ ቅዱስ ወደ ውድድሩ ሲገባ የተደረገለት ድጋፍ በጣም እንዳስደሰተው ገልጧል።

«ከሦስት ቀናት በፊት ነው የመጣሁት። በርካታ የቴሌቪዥን ዝግጅቶች እና ቃለ-መጠይቆች ላይ ተሳትፌያለሁ። በተለይም የኤርትራ ፕሬዚዳንት ለውድድር የሚሆኑ ስጦታዎችን አበርክተውልናል። ስለዚህ በጣም ደስ የሚል ድባብ ነው።»

ኔዘርላንድ ኡትሬሽት ውስጥ ትናንት በተከናወነው የ166 ኪሎሜትር የቱር ደፍሯንስ ሁለተኛ ዙር የብስክሌት ሽቅድምድም የጀርመኑ አንድሬ ግራይፕል በ3 ሰአት ከ29 ደቂቃ ከ3 ሰከንድ አንደኛ በመውጣት አሸናፊ ሆኗል።

የኤርትራው ብስክሌተኛ ዳንኤል ተክለኃይማኖት በ3:34:07.በመግባት የ170ኛ ደረጃን ይዟል። ሌላኛው የሀገሩ ልጅ መርሐዊ ቅዱስ ከኋላው 10 ተወዳዳሪዎችን አስከትሎ 189ኛ ወጥቷል። ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀበት 3:34:07. ነው። ኔዘርላንድ ኡትሬሽት ውስጥ እሁዱ በተከናወነው የቱር ደ ፍሯንስ የብስክሌት ሽቅድምድም የአውስትራሊያው አዳም ሐንሰን በ3:40:09. በመግባት የመጨረሻውን 198ኛ ደረጃ አግኝቷል።

የቱር ደ ፍሯንስ የብሽክሌት ሽቅድምድም 3ኛ ዙር አሸናፊ

የቱር ደ ፍሯንስ የብሽክሌት ሽቅድምድም 3ኛ ዙር አሸናፊሦስተኛው ዙር የቱር ደፍሯንስ የብስክሌት ሽቅድምድም ሰኞ ሰኔ 29 ቀን፣ 2007 ዓ.ም. በቤልጂግ ተከናውኗል። አጀማመሩ ላይ የብስክሌቶች መንሸራተት እና መደራረብ አደጋ በተከሰተበት የዛሬው ሽቅድምድም የስፔኑ ተወዳዳሪ ሮድሪጌዝ አሸናፊ ለመሆን ችሏል። የመንሸራተት እና የመደራረብ አደጋ የደረሰው ከውድድሩ ማብቂያ 60 ኪሎሜትር ላይ የፈረንሣዩ ዊሊያም ቦኔ ከነብስክሌቱ አስፓልቱ ላይ ተንሸራቶ በመውደቁ ነበር። ከዚያም ውድድሩን በመምራት ላይ የነበረው ፋቢያን ካንቼላራ ጨምሮ በርካታ ብስክሌተኞች አስፓልቱ ላይ በመንሸራተት እርስ በርስ የመደራረብ አደጋ ደርሶባቸዋል። ሦስት ተወዳዳሪዎች ውድድሩን አቋርጠዋል። ውድድሩን በድጋሚ ለማስጀመር ከ10 ደቂቃ በላይ ጊዜ መጀቱም ተጠቅሷል።

ከቅዳሜ ሰኔ 27 ቀን፣ 2007 ዓ.ም. አንስቶ የጀመረው የቱር ደ ፍሯንስ የብስኪሌት ሽቅድምድም ለሦስት ሳምንታት ከተኪያሄደ በኋላ እሁድ ሐምሌ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ይጠናቀቃል። 102ኛው የቱር ደ ፍሯንስ የብስክሌት ሽቅድምድም 21 ዙር ውድድሮች ሲኖሩት በአጠቃላይ ውድድሩ የ 3,360 ኪሎ ሜትሮችን ርቀት ያካትታል።

የሜዳ ቴኒስ

አሜሪካዊቷ የሜዳ ቴኒስ ባለድል ሴሬና ዊሊያምስ

አሜሪካዊቷ የሜዳ ቴኒስ ባለድል ሴሬና ዊሊያምስ

በዌምብልደን የሜዳ ቴኒስ የመክፈቻ ግጥሚያ ሴሬና ዊሊያምስ ታላቅ እህቷ ቬኑስ ዊሊያምስን ዛሬ አሸንፋታለች። ታላቅ እህቷ ቬኑስን 6-4 እና 6-3 በሆነ ልዩነት ያሸነፈችው የ20 ጊዜያት ባለድሏ ሴሬና ዊሊያምስ ወደ ሩብ ፍፃሜ ግስጋሴዋን ቀጥላለች። ሁለቱ እህትማማቾች የእንግሊዝ ቡድኖች አምስት ጊዜያት ባለድል ሲሆኑ፤ ሴሬና የአውትራሊያ እና የፈረንሳይ ውድድሮችን በማሸነፏ ለዋናው ድል ግስጋሴዋን አመቻችታለች። የሩስያዋ ማሪያ ሻራፖቫ ደግሞ የካዛክስታኗ ዛሪያን ዲያስን ሁለቱንም ዙር 6-4 አሸንፋታለች።

ካናዳ ቫንኮቨር ከተማ ውስጥ በተከናወነው የሴቶች የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ የፍፃሜ ግጥሚያ ትናንት የዩናይትድ ስቴትስ ቡድን የጃፓን ቡድንን 5:2 በመርታት አሸናፊ ሆኗል። የዩናይትድ ስቴትስ ቡድን በትናንቱ ድል የዓለም ዋንጫን ለሦስተኛ ጊዜ በእጁ ከማስገባቱም ባሻገር ከአራት ዓመታት በፊት ጀርመን ፍራንክፉርት ከተማ ላይ ጉድ ያደረገው የጃፓን ቡድንን ለመበቀል ችሏል። የጀርመን ቡድን ለሦስተኛ ደረጃ ባደረገው ፍልሚያ በእንግሊዝ ቡድን 1 ለ0 መሸነፉም ተዘግቧል።

በደቡብ አሜሪካ የእግር ኳስ ፍፃሜ ደግሞ የቺሊ ቡድን የአርጀንቲና ቡድንን በሰፋ ልዩነት መርታት ችሏል። ቺሊ አርጀንቲናን ያሸነፈችው 4 ለ1 በሆነ ሰፊ የግብልዩነት ነው። ለአርጀንቲናዎች ብቸኛዋን ግብ በፍፁም ቅጣት ምት ማስቆጠር የቻለው የዓለማችን ኮከብ የእግር ኳስ ተጨዋቹ ሊዮኔል ሜሲ ነው።

አሜሪካዊቷ የሜዳ ቴኒስ ባለድል ሴሬና ዊሊያምስ

ጃፓንን ያሸነፈው የዩናይትድ ስቴትስ ቡድን

የዓለም ዋንጫን በተደጋጋሚ በእጇ ማስገባት የቻለችው አርጀንቲና የኮፓ አሜሪካ ዋንጫን ለማሸነፍ ከ20 ዓመታት በላይ ደጅ መጥናት ግድ ሆኖባታል። ያም ሆኖ ትናንት ሊሳካላት አልቻለም።

ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች በማይሰለፉበት የቻን የአፍሪቃ ዋንጫ የእግር ኳስ ማጣሪያ ኢትዮጵያ እና ቡሩንዲ ተሳክቶላቸዋል። በሳምንቱ ማገባደጃ ላይ ቡሩንዲ ጅቡቲን ቡጁምቡራ ውስጥ 2 ለ0 አሸንፋለች። ዋሊያዎቹ ደግሞ ናይሮቢ ውስጥ ከኬንያ ጋር ያለምንም ግብ ተለያይተዋል። በዚህም መሠረት የኬንያ አቻውን በደርሶ መልስ 2 ለዜሮ ያሸነፈው የኢትዮጵያ ቡድን በደርሶ መልስ ጅቡቲን 4 ለ1 ከረታው የቡርንዲ ቡድን ጋር ከሦስት ወራት በኋላ ይጋጠማል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic