የስፖርት ዘገባ፤ ሰኔ 26 ቀን፣ 2009 ዓ.ም. | ስፖርት | DW | 03.07.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ፤ ሰኔ 26 ቀን፣ 2009 ዓ.ም.

ሩስያ ውስጥ ሲከናወን የቆየው የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የእግር ኳስ ውድድር በጀርመን አሸናፊነት ተጠናቋል። በታዳጊዎች የአትሌቲክስ ፉክክር ኢትዮጵያ ተፎካካሪዎቿን በሜዳሊያ ብዛት ልቃ አሸንፋለች። ቅዱስ ጊዮርጊስ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ አዲስ አበባ ስታዲየም ውስጥ ተሸንፏል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:33

ስፖርት፤ ሰኔ 26 ቀን፣ 2009 ዓ.ም.

በሁለት ምድብ፥ የክፍለ-ዓለም አሸናፊ 8 ቡድኖችን ሩስያ ውስጥ ያሳተፈው የኮንፌዴሬሽን እግር ኳስ ዋንጫ  በጀርመን አሸናፊነት ተጠናቋል። የዓለም ዋንጫ ባለድሏ ጀርመን የኮፓ አሜሪካ አሸናፊዋ ቺሊን በመርታት ነው የቅድመ-ዓለም ዋንጫ መሰናዶ ውድድሩ የኮንፌዴሬሽን ካፕን ያሸነፈችው። የኢትዮጵያ ታዳጊ አትሌቲክስ ቡድን አልጀሪያ ውስጥ በተደረገ ፉክክር 38 ሜዳሊያ በመሰብሰብ ከተወዳዳሪዎቹ በአጠቃላይ ልቆ በአንደኛነት አጠናቋል።  የለንደኑ የዓለም አትሌቶች አሸናፊዎች ውድድር ምርጫ መሥፈርት ግልጽ አይደለም ሲሉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ቅሬታ አሰምተዋል። በመካከለኛ ክብደት ሚዛን የቡጢ ፍልሚያ የ6 ጊዜያት ባለድሉ ማኒ ፓኪው ብዙም በማይታወቅ ቡጢኛ ሽንፈት ቀምሷል። የዳኞች ውሳኔ ብዙዎችን አበሳጭቷል።

እግር ኳስ

ሩስያ ውስጥ ለሁለት ሳምንታት የዘለቀው የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የእግር ኳስ ፍልሚያ በጀርመን አሸናፊነት ትናንት ተጠናቋል። ጀርመን ለዋንጫ የደረሰችው በግማሽ ፍጻሜው ሜክሲኮን 4 ለ1 በሆነ ሰፊ ውጤት ድል አድርጋ ነው። በአንጻሩ ለፍጻሜው ደርሳ የነበረችው ቺሌ ደግሞ  ከፖርቹጋል ጋር በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ-ጊዜ ያለምንም ግብ በመለያየቷ በተሰጠው የፍጹም ቅጣት መለያ ምት 3 ለ0 በማሸነፍ ነበር ለፍጻሜ የደረሰችው። በፍጻሜው ግጥሚያም ጀርመን በአንድ ብቸኛ ግብ ቺሊን ረትታ ለድል በቅታለች። የ57 ዓመቱ የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ ዮኣሂም ሎይቭ በወጣት ቡድኑ ድል መደሰታቸውን ገልጠዋል።

«በወጣቶቹ በጣም ተደስቻለሁ። እኔም በበኩሌ የምንፈልገውን ስላሳካን እጅግ ሲበዛ ኩራት ተሰምቶኛል። ስኬታችን በብርቱ  ወኔ የታጀበ  ነበር። ወጣቶቹ በቡንደስሊጋው የውድድር ዘመን ራሱ ብዙ ተጨናንቀዋል፤ ሲበዛም ማስነዋል። ታዲያ ያን ሁሉ አልፈን ነው ለዚህ የደረስነው። እንደሚመስለኝ በስተመጨረሻም ያለአንዳች ሽንፈት ይገባን የነበረውን የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ አሸንፈናል።»

ጀርመን የትናንቱን የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ከማሸነፏ ሁለት ቀን ቀደም ብሎ ደግሞ ዕድሜያቸው ከ21 ዓመት በታች የሆኑ ተጨዋቾች የሚወዳደሩበትን የአውሮጳ እግር ኳስ ዋንጫ በእጇ አስገብታለች። ቡድኑ ዋንጫውን ሊወስድ ይችላል ተብሎ ከፍተኛ ግምት የተሰጠው የስፔኑ አቻውን በተመሳሳይ 1 ለ0 ውጤት አስደንግጦ ነበር ያሸነፈው።

ትናንት ዋንጫውን ያሸነፈው የዋናው ቡድንም የተዋቀረው በወጣቶች በመሆኑ ጀርመን ወጣት የእግር ኳስ ተጨዋቾች ላይ አመርቂ ተግባር ለመፈጸሟ ማረጋገጫ ሆኗል።

የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድንን ካለፉት 11 ኦመታት አንስቶ በመምራት ላይ የሚገኙት አሰልጣኝ ዮኣሒም ሎይቭ ለሚቀጥለው ዓመት የዓለም ዋንጫ ዋና ተሰላፊዎችን ለመምረጥ እስኪቸገሩ ድረስ ዓለም አቀፍ ልምድ ያካበቱ 40 ተጨዋቾችን አሰባስበዋል።  ቺሊን ትናንት ድል ያደረጉት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2014 የዓለም ዋንጫን በእጁ ያስገባውን ቡድናቸውን በማሳረፍ በወጣት ተጨዋቾች የተለያዩ ሙከራዎችን በማድረግ ነበር። ወጣት ቡድናቸውም ለድል የበቃው በ28 ዓመት ተጨዋቹ ላርስ ሽቲንድል ብቸኛ ግብ ነበር።

«እንደሚመስለኝ በሚገርም አይነት ነበር የተፋለምነው። በእርግጥ ወደ ጨዋታው ስልት ለመግባት የተወሰኑ ችግሮች ነበሩብን» ያለው ላርስ «ቺሊዎች ሜዳ ላይ ዳግም ሲበዛ ንቁና ፈጣን ሆነው ነበር» ብሏል።  «መስለኝ ግን» አለ ላርስ «እኛ ባለፉት ሳምንታት ሲበዛ ለፍተናል፤ ብዙም አድርገናል። እናም ድሉ የዚያ ጠንክሮ የመሥራታችን ውጤት ነው ባይ ነኝ፤ ለዚያ ደግሞ እጅግ ደስተኛ ነኝ» ሲል ደስታውን ገልጧል።

ከሩስያዋ ሴንት ፒትስበርግ ከተማ ዋንጫ ይዞ በድል የተመለሰው የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ዛሬ አየር ማረፊያ ሲደርስ ከተወሰነ የፎቶግራፍ መርሐግብር በስተቀር ሌላ አቀባበል አልተደረገለትም። ተጨዋቾቹ ነሐሴ ወር ላይ ዳግም ለሚጀምረው ቡንደስሊጋ ከመመለሳቸው በፊት ለረፍት ወደሚፈልጉበት ሥፍራ ተበታትነዋል። ከረፈት መልስ ግን ከቡንደስሊጋው ባሻገር በሚቀጥለው ዓመት እዛው ሩስያ ውስጥ ለሚከናወነው የዓለም ዋንጫ ውድድር ማጣሪያ ሁለት ወሳኝ ጨዋታዎች ይጠብቃቸዋል። የጀርመን ቡድን ለ2018ቱ የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ለመሆን ያስችለው ዘንድም መስከረም ወር ላይ የማጣሪያ ጨዋታዎቹን ከቼክ ሪፐብሊክ እና ከኖርዌይ ጋር ይገጥማል።  

ከጀርመን እና ቺሊ የፍጻሜ ግጥሚያ ቀደም ብሎ ትናንት ለሦስተኛ ደረጃ በተደረገው ግጥሚያ  ደግሞ ፖርቹጋል ሜክሲኮን  2 ለ1 ድል አድራጋለች። የዓለም ዋንጫን ከአንድ ዓመት በኋላ የምታሰናዳው ሩስያ ለኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታ ያደረገችው ዝግጅት ተደንቋል። የዓለም የእግር ኳስ ማኅበራት ፌዴሬሽን በእንግሊዝኛ ምኅፃሩ (FIFA) ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ የሩስያ መሰናዶን አወድሰዋል። የሩስያ ዝግጅትንም ፕሬዚዳንቱ፦ «ከብዙ አቅጣጫዎች ሲታይ ታላቅ ስኬት ነው» ብለዋል።

ከእግር ኳስ ዜና ሳንወጣ ለአፍሪቃ ቡድኖች አሸናፊዎች አሸናፊ ግጥሚያ ከደቡብ አፍሪቃው ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ጋር በደጋፊዎቹ ፊት የተጫወተው ቅዱስ ጎዮርጊስ 1 ለ0 ተሸንፎ ከውድድሩ ተሰናብቷል። ማሜሎዲ ሰንዳውንስ እና የቱኒዝያዎቹ ኤስፔራንስ እንዲሁም ኢቶይል ሳሄል ወደ ሩብ ፍጻሜው ያለፉ ቀዳሚ ቡድኖች ሆነዋል። በቅዳሜው ጨዋታ አዲስ አበባ ስታዲየም በ30,000 ተመልካቾቹ ጢም ብሎ ሞልቶ ነበር። ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታውን በግብ ለምራት የሚያስችለውን ታላቅ አጋጣሚም አምክኗል። የሰንዳውንሱ ተከላካይ አኔሌ ንግኮንግካ ፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ኳሷን በእጁ በመንካቱ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ሳላሃዲን ሰዒድ በግብ ጠባቂው ቀኝ በኩል ቢመታም ግብ ጠባቂው ዴኒስ ኦንያንጎ ተወርውሮ በማጨናገፍ ግብ ከመሆን አድኗታል።  

አትሌቲክስ

አልጄሪያ ውስጥ በተከናወነው 13ኛው የአፍሪቃ ወጣቶች አትሌቲክ ስፖርት ፉክክር ኢትዮጵያ በርካታ ሜዳሊያ በመሰብሰብ አንደኛ በመሆን አጠናቃለች። ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የሆኑ አትሌቶችን ባሳተፈው ውድድር ኢትዮጵያ 38 ሜዳሊያዎችን ያገኘች ሲሆን፤ 13ቱ ወርቅ ነው። ቀሪው 13 ብር፤ እንዲሁም 12ቱ ደግሞ የነሐስ ሜዳሊያ። ሁለተኛ የወጣው የደቡብ አፍሪቃ ቡድን በአጠቃላይ 17 ሜዳሊያዎችን ማግኘት ችሏል። ኬንያን በእጥፍ ሜዳሊያ በልጣ ሦስተኛ የወጣችው አዘጋጇ አልጄሪያ 20 ሜዳሊያዎችን መሰብሰብ ችላለች።

የኢትዮጵያ ወጣት አትሌቶች እጅግ አመርቂ ድል በማስመዝገባቸው ያስደሰተውን ያህል በለንደኑ የዓለም አትሌቶች አሸናፊዎች ውድድር ተሳታፊዎች ምርጫ መሥፈርት ግልጽ አይደለም ሲሉ አትሌቶች ቅሬታ እያሰሙ ነው። ለለንደኑ ውድድር ሚኒማ ያሟሉ አትሌቶች ቢኖሩም አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ የምርጫ መስፈርቶቹ ግልጽ ባለመሆናቸው እንዲሁም ስም ያላቸው አትሌቶችን ለማካተት ፌዴሬሽኑም አንዳንድ አሰልጣኞችም ጥረት እያደረጉ በመሆናቸው ነገሩ ግራ አጋብቶናል  ሲሉ አትሌቶቹ ቅሬታ አሰምተዋል።  የቅዳሜው የፓሪስ ዳያመንድ ሊግ የሚኒማ ማሟያ የመጨረሻ ውድድር እንደነበር ቢጠቀስም እስካሁን ድረስ ለለንደኑ የዓለም አሸናፊዎች ፉክክር ተሰላፊ አትሌቶች የመጨረሻ ስም ዝርዝር ይፋ አልተደረገም። ምርጫው እንደተጠናቀቀ እና ይፋ እንደተደረገ የባለሙያ አስተያየት ለማሰማት እንሞክራለን።

በሌላ የስፖርት ዜና የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ 34ኛው ዓመታዊ የስፖርት እና የባህል ዝግጅት  በዩናይትድ ስቴትስ ሲያትል ከተማ ውስጥ ትናንት ተከፍቷል። ፌስቲቫሉ እስከፊታችን ቅዳሜ ድረስ እንደሚዘልቅም የፌስቲቫሉ ድረ-ገጽ ላይ ሰፍሯል።

ቡጢ

በመካከለኛ ከባድ ሚዛን የቡጢ ፍልሚያ የዓለማችን የስምንት ጊዜያት የቀበቶ ባለድል ነው፤ የ38 ዓመቱ ቡጢኛ ማኒ ፓስኪያው። በ29 ዓመቱ የቀድሞ የሁለተኛ ደረጃ መምህር ግን ድል ተነስቷል። ማኒ ፓስኪያው ብሪዝባን አውስትራሊያ ውስጥ የተሸነፈው በማያሻማ መልኩ ዳኞች በሰጡት ነጥብ ነው።  የማኒ አሰልጣኝ የቀድሞው የከባድ ሚዛን ተፋላሚው ጀስቲን ፎርቹን፣ ደጋፊዎች እንዲሁም በከባድ ሚዛን ዝነኛ ቡጢኛው ሌኖክስ ሌዊስ እና የዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞው የቅርጫት ኳስ ተጨዋች ኮቤ ብሪያንት የዳኞቹን ውሳኔ አጥብቀው ተችተዋል። የፊልም ተዋንያኑ ሳሙኤል ኤል ጃክሰንም የማኒ ፓስኪያው መሸነፍን ማመን እንዳልቻለ ተናግሯል። ማኒ ፓስኪያው የተሸነፈው በአውስትራሊያዊው መምሕር እና ብዙም በማይታወቀው ቡጢኛ ጄፍ ሆርን ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic