የስፖርት ዘገባ፤ ሰኔ 22 ቀን፣ 2007 ዓ.ም | ስፖርት | DW | 29.06.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ፤ ሰኔ 22 ቀን፣ 2007 ዓ.ም

በሴቶች የዓለም የእግር ኳስ ፍልሚያ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ወደ ፍፃሜው ለማለፍ ነገ ማታ ዩናይትድ ስቴትስን ይገጥማል። አስተናጋጇ ካናዳን ያስወጣችው እንግሊዝ ከ2 ሰዓታት ቀደም ብሎ ከጃፓን ጋር ትፋለማለች። ካናዳ ውስጥ የተከናወኑ ጨዋታዎችን ከቦታው የተከታተለ ኢትዮጵያዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ለኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን መልእክት አለው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:45
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:45 ደቂቃ

የስፖርት ዘገባ፤ ሰኔ 22 ቀን፣ 2007 ዓ.ም

ለዓለም የሴቶች የእግር ኳስ የግማሽ ፍፃሜ ፍልሚያ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ከዩናይትድ ስቴትስ አቻው ጋር ነገ ማክሰኞ ሞንትሪያል ውስጥ ይጋጠማል። በበነጋታው ጃፓን ከከእንግሊዝ ጋር ትገናኛለች። ያለፈውን ዋንጫ በእጇ ያስገባችው ጃፓን ከትናንት በስትያ አውስትራሊያን 1 ለምንም አሸንፋ ነው ለግማሽ ፍፃሜ የደረሰችው። እንግሊዝ በበኩሏ ለነገው ፍልሚያ የበቃችው አስተናጋጇ ሀገር ካናዳን 2 ለ1 በሆነ ውጤት ከውድድር በማስወጣት ነው። ጀርመን ከፈረንሳይ ጋር ባደረገችው ጨዋታ መደበኛውም፣ ጭማሪውም ሰአት የተገባደደው አንድ እኩል በሆነ ውጤት ነበር። ጀርመን በፍፁም ቅጣት ምት 5 ለ4 በማሸነፍ ነው ለነገው ጨዋታ የደረሰችው።

ካናዳ ውስጥ የሚኪያሄደው የዓለም የሴቶች የእግር ኳስ ግጥሚያ ሊገባደድ ጥቂት ቀናት ይቀሩታል። የሐትሪክ የስፖርት ጋዜጣ ባለቤትና ዋና አዘጋጅ ኢሳቅ በላይ ውድድሩን ለመከታተል ወደ ካናዳ አቅንቶ ነበር። በቦታው ተገኝቶ የተከታተለውን ውድድር እንዲህ ቃኝቶታል።

የጀርመን የሴቶች የእግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎች

የጀርመን የሴቶች የእግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎች

የስፖርት ጋዜጠኛው ኢሳቅ በላይ በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማሕበራት ፌዴሬሽን ተጋብዞ ነበር ካናዳ ውስጥ ለሦስት ሳምንት የቆየው። በካናዳ ቆይታው እና በሌላ የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ ከታዘባቸው በመነሳት የኢትዮጵያ የሴቶች የእግር ኳስ ቡድንም መሰል ውድድሮች ላይ ለመሳተፍ ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅበት ጠቁሟል።

የዓለም የሴቶች የእግር ኳስ ውድድር በዚህ ሳምንት ውስጥ ይጠናቀቃል። የደረጃ እና የፍፃሜ ጨዋታዎቹ ኤድሞንተን እና ቫንኮቨር ካናዳ ውስጥ የሚከናወኑት የፊታችን ቅዳሜ እና እሁድ ነው።

የጀርመን የእግር ኳስ ሊግ የስፔን አቻው በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማሕበራት ፌዴሬሽን በእንግሊዘኛ ምኅጻሩ FIFA ላይ የጀመረው ሕጋዊ ዘመቻ ላይ እንደማይሳተፍ ዛሬ አስታውቋል። የስፔን የእግር ኳስ ሊግ ቓታር ላይ እንደ ጎርጎሪዮሣዊው አቆጣጠር በ2022 የሚኪያሄዱ የክረምት ጨዋታዎችን ፊፋ በማሸጋሸጉ ኪሳራ ይደርስብኛል በሚል መክሰሱ ይታወቃል። የጀርመን የእግር ኳስ ሊግ ከእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እና ከጣሊያን ሴሪ ኣ ጋር በመሆን ዓለም አቀፉን የእግር ኳስ ተቋም የሚጎዳ ጥያቄ የመሳካት ዕድሉ አነስተኛ ነው ብሏል። ሆኖም የስፔን የእግር ኳስ ሊግ የስፖርት ጉዳዮች ተመልካች ለሆነው ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የጨዋታዎቹን መሸጋሸግ በመቃወም ክስ አቅርቧል። ፊፋ ጨዋታዎቹን በባሕረ-ሠላጤው እጅግ ሞቃታማ የአየር ጠባይ የተነሳ ለክረምት በማሸጋሸጉ የስፔን የእግር ኳስ ሊግ የ72 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ እንደሚገጥመው ተናግሯል።

የ79 ዓመቱ ሴፕ ብላተር መስከረም፤ 2007 ዓ.ም.

የ79 ዓመቱ ሴፕ ብላተር መስከረም፤ 2007 ዓ.ም.

በሌላ ዜና የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማሕበራት አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን የፊፋ ፕሬዚዳንት ሴፕ ብላተር ግልጽ በሆነ መልኩ ሥልጣን እንደሚለቁ ማረጋገጥ እንዳለባቸው አሳሰቡ። የፊፋ የዕጩዎች ተቆጣጣሪ ዶሜኒኮ ስካላ «ፊፋ ከበላይ የሚጠብቀው አካል የሚቀየር ስለመሆኑ ምንም በማያሻማ መልኩ መገለጥ አለበት» ብለዋል።

የአሜሪካ እና የስዊዘርላንድ የፌዴራል መርማሪዎች የሙስና ጉዳይ ምርመራን ተከትሎ የፊፋው ፕሬዚዳንት ሴፕ ብላተር ስልጣን እንደሚለቁ ካሳወቁ በኋላ ቴክኒካዊ በሆነ መልኩ ሥልጣን ባለመልቀቃቸው በሥራ መቆየት እንደሚፈልጉ መናገራቸው ተጠቅሷል። ይኽን ተከትሎም የፊፋ የዕጩዎች ተቆጣጣሪ ዶሜኒኮ «በሥልጣን የመሞዳሞጃው በእርግጥም ጊዜው አክትሟል» ሲሉ ፕሬዚዳንቱ በቃላቸው መሠረት ሥልጣናቸውን እንዲለቁ አሳስበዋል። ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማሕበራት ፌዴሬሽን ልዩ ኮሚቴም ፕሬዚዳንት ሴፕ ብላተርን የሚተካ ሰው ለማግኘት በቅርቡ ስብሰባ እንደሚያደርግ ተጠቅሷል።

በፊፋ የሙስና ቅሌት 18 ባለሥልጣናቱ ምርመራ እየተደረገባቸው ሲሆን፤ ሰባት ባለሥልጣናቱ 150 ሚሊዮን ዶላር ጉቦ ተቀብለዋል ተብሏል። ምክትል ፕሬዚዳንቱ ስዊዘርላንድ ዙሪክ ከተማ ውስጥ በሚገን እጅግ ዘመናይ ሆቴል ውስጥም ሲንደላቀቁ መያዛቸው መዘገቡ ይታወቃል። ይኽ እና ሌሎች የሙስና ቅሌቶች ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽንን ለ17 ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉት የ79 ዓመቱ ሴፕ ብላተር ሥልጣን እለቃለሁ እንዲሉ ማስገደዱም ይታወሳል። መልሰው በሥልጣን ለመቆየት ማቅማማታቸው ባይቀርም ማለት ነው።

ቴኒስ ዌምብልደን፤ ኖቫክ ጆኮቪች ፊሊፕ ኮልሽራይበርን አሸንፎ

ቴኒስ ዌምብልደን፤ ኖቫክ ጆኮቪች ፊሊፕ ኮልሽራይበርን አሸንፎ

በሜዳ ቴኒስ የውንብልደን ውድድር ከሚሳተፉ 18 ጀርመናውያን መካከል ግማሽ ያህሉ በመክፈቻው ቀን ይወዳደራሉ። የዓለማችን ምርጥ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች የሆነው ሰርቢያዊው ኖቫክ ጄኮቪች ከጀርመን አውስቡርግ የሄደው ፊሊፕ ኮልሽራይበርን ገጥሟል። ሁለት ሰአት ያኽል በፈጀው የሜዳ ቴኒስ ጨዋታ የ31 ዓመቱ ጀርመናዊ ፊሊፕ በ28 ዓመቱ ሠርቢያዊ የዓለም ኮከብ ሦስቱንም ዙር ጨዋታ የተረታው 4 ለ6 በሆነ የጠበበ ልዩነት ነበር። በዚህም ልዩነት ኖቫክ ወደ ሁለተኛው ዙር ማለፍ ችሏል። በመቀጠል ሠርቢያዊው የሚፋለመው ከሌይተን ሔዊት አለያም ከጃርኮ ሚይሚነን ጋር ይኾናል ተብሏል።

በዌምብልደኑ የሜዳ ቴኒስ የሴቶች ፉክክር አሜሪካዊቷ ዝነኛ የሜዳ ቴኒስ ኮከብ ሴሬና ዊሊያምስ የሩሲያዋ ማርጋሪታ ጋስፓሪያን 6:4፣ እና 6:1በሆነ ልዩነት በማሸነፍ ወደ ሁለተኛው ዙር ለማለፍ በቅታለች።

ፖርቹጋል ከ21 ዓመት በታች የግማሽ ፍፃሜ የእግር ኳስ ጨዋታ ጀርመንን በሰፋ ልዩነት አሸነፈች። የጀርመን ቡድን ድንቅ ጨዋታ ቢያከናውንም በፖርቹጋል ቡድን በከባዱ ከመቀጣት አልተረፈም። ከመጀመሪያው አጋማሽ ረፍት በፊት 3 ለዜሮ ትመራ የነበረችው ጀርመን በፖርቹጋል የተረታችው 5 ለባዶ ነው።

ከ21 ዓመት በታች፤ ጀርመን ከፖርቹጋል

ከ21 ዓመት በታች፤ ጀርመን ከፖርቹጋል

ፖርቹጋል ከ21 ዓመት በታች የእግር ኳስ ተጨዋቾች በሚሳተፉበት የአውሮጳ ውድድር ፍፃሜ ለሁለት ጊዜያት መድረሷ ይታወቃል። የፖርቹጋል ቡድን ለፍፃሜው ነገ ቼክ ሪፐብሊክ መዲና ፕራግ ውስጥ ከስዊድን ጋር ይፋለማል። የስዊድን ቡድን ለፍፃሜ የበቃው ዴንማርክን 4 ለ1 በመርታት ነው።

የአውሮጳ ጨዋታዎች የአትሌቲክስ ፉክክር በአዘርባጃን ከመጠናቀቁ ጥቂት ቀደም ብሎ አንዲት ትውልደ-ኢትዮጵያዊት የአዘርባጃን አትሌት ኃይል ሠጪ ዕጽ መጠቀሟ ተገልጧል። የ18 ዓመቷ አትሌት ጫልቱ ቤጂ ከ3000 ሜትር የመሰናከል ሩጫ ውድድር መሰናበቷም ተዘግቧል። የጫልቱ የአንደኛነት ውጤት መሰረዙ የአዘርባጃን ቡድን የአምስተኛነት ደረጃን እንዳልቀየረውም ተጠቅሷል። ቦንቱ መገርሳ ለአዘርባጃን ተሰልፋ የነሐስ ሜዳሊያ ማግኘቷ ይታወቃል። ሌላኛው ትውልደ-ኢትዮጵያዊ የአዘርባጃን አትሌት ኃይሌ ኢብራሂሞቭ የመካከለኛ ርቀት ውድድሮችን በአጠቃላይ አሸንፏል። ኃይሌ የ1,500, የ3,000 እና የ5,000ሜትር የሩጫ ውድድሮችን ማሸነፍ የቻለው በሁለት ቀናት ልዩነት ውስጥ ብቻ ነው።

የሀገር ውስጥ ተጨዋቾችን ብቻ በሚያሳትፈው የቻን የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ሞሪታንያ ሴራሊዮንን በማሸነፍ ማለፏን አረጋግጣለች። ሞሪሽየስ ሴራሊዮንን 2 ለዜሮ ነው የረታችው። ከ6 ወር ከዓሥራ አምስት ቀን በኋላ ሩዋንዳ ውስጥ ለሚከናወነው የቻን ውድድር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም የመልስ ጨዋታውን የፊታችን እሁድ ኬንያ ውስጥ ያኪያሂዳል። ባህር ዳር ውስጥ በተከናወነው የመጀመሪያ ዙር ግጥሚያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የኬንያ አቻውን 2 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎች

የኔዘርላንድ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ጉስ ሒዲንክ ዛሬ ከአሠልጣንነታቸው መነሳታቸው ተገለጠ። አሠልጣኙ እንደ ጎርጎሪዮሳዊው አቆጣጠር በ2016 ለሚኪያሄደው የአውሮጳ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ቡድናቸው ደካማ አቋም ካሳየ በኋላ በአሠልጣኝነት የመቆየታቸው ነገር አጠያያቂ ሆኖ ቆይቶ ነበር።

የቱኒዝያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አሠልጣኝ ጂዮርጅ ሊከንስም ቃል የተገባልኝ ተጨማሪ ክፍያ ስላልተሰጠን የአሠልጣኝነት ውሌን አቋርጫለሁ ሲሉ ዛሬ አስታውቀዋል። የ66 ዓመቱ ቤልጂየማዊ የቱኒዝያ አሠልጣኝ ኾነው ከዓመት በላይ አገልግለዋል። ቡድናቸው ለአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ ጅቡቲን 8 ለ1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic