የስፖርት ዘገባ፤ ሰኔ 15 ቀን፣ 2007 ዓ.ም | ስፖርት | DW | 22.06.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ፤ ሰኔ 15 ቀን፣ 2007 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን እሁድ ባሕር ዳር ስታዲየም ውስጥ የኬንያው አቻውን 2 ለ0 በሆነ ውጤት አሸንፏል። ከአንድ ሳምንት በፊትም ቡድኑ በዚሁ ስታዲየም ማሸነፉ ይታወቃል። በተለይ የእግር ኳስ ተንታኝ የሆነ አንድ ጋዜጠኛ ጨዋታው «ከስህተታችን በመነሳት ቡድናችንን ማጠናከር እንደሚገባን፣ ትምህርት የሰጠ ነው የሚመስለኝ» ይላል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:16
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:16 ደቂቃ

የስፖርት ዘገባ፤ ሰኔ 15 ቀን፣ 2007 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ እና ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች በማይካተቱበት የቻን የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር በአንድ ሳምንት ልዩነት ውስጥ በሜዳው ያደረጋቸው ሁለት ግጥሚያዎችን አሸንፏል። ሁለቱም ጨዋታዎች የተከናወኑት ለዋልያዎቹ ከፍተኛ ድጋፍ የሚሰጡ በሺዎች የሚቆጠሩ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች በታደሙበት በባሕር ዳር ስታዲየም ነበር።

ዋሊያዎቹ ትናንት ለቻን ውድድር ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ከኬንያው አቻቸው ጋር በማከናወን ሁለት ለባዶ በሆነ ውጤት አሸንፈዋል። ጨዋታው በቀጥታ በቴሌቪዥን ባለመተላለፉ የስፖርት ባለሙያ ትንታኔ ማካተት አልተቻለም። ሙያዊ ትንታኔውን ለመስጠት በምስል የተቀዳውን ጨዋታ እየመላለሱ ደጋግሞ መመልከት ያስፈልጋል። ሆኖም በብስራት ኤፍ ኤም 101.1የማለዳ ስፖርት ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ ቀደም ሲል ከሌሶቶ ጋር የተከናወነውን ጨዋታ በመንተራስ ቡድኑ «ውህደት ላይ ብዙም የሚባልለት አይልነበረም» ብሏል።

የዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ማኅበራት ፌዴሬሽን በእንግሊዘኛ ምኅፃሩ FIFA ባወጣው የቅርብ ጊዜ መረጃ መሰረት ሌሶቶ በእግር ኳስ ደረጃዋ ከኢትዮጵያ በታች በርቀት ላይ ነው የምትገኘው። እንዲያም ሆኖ ግን የሌሶቶ ቡድን በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ግብ ከማስቆጠሩም ባሻገር የበላይ ሆኖመታየቱን አስመልክቶ ጋዜጠኛ መንሱር የማስጠንቀቂያ ደወል ነው ይላል።

ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች በማይካተቱበት የአፍሪቃ ዋንጫ የቻን ውድድር ማጣሪያ በአጠቃላይ 42 ሃገራት ይወዳደራሉ። ማጣሪያውን አልፈው ወደ ዋናው ውድድር የሚገቡት ሃገራት ግን 15 ብቻ ናቸው። ቀጣዩ የቻን ፉክክር ከአርብ ጥር 8 ቀን 2007 ዓም እስከ ቅዳሜ ጥር 30 ቀን በሩዋንዳ አስተናጋጅነት ይከናወናል። ሩዋንዳ አዘጋጅ ሀገር በመሆኗ በቀጥታ አላፊ ናት።

ካናዳ ውስጥ የሚከናወነው የዓለም የሴቶች የእግር ኳስ ግጥሚያ የእሁድ ሳምንት ይጠናቀቃል። ዖታዋ ካንስዶውን ስታዲየም ውስጥ 18 ሺህ ተመልካቾች በተገኙበት በተከናወነው ጨዋታ የጀርመን የሴቶች የእግር ኳስ ቡድን 4 ለ1 ያሸነፈው የስዊድኑ አቻውን ነበር። የጀርመን ቡድን ጨዋታው በተጀመረ ገና በ2ኛው ደቂቃ 2 ለዜሮ መምራት ችሎ ነበር። ከግንቦት 29 ጀምሮ በመከናወን ላይ የሚገኘው የዓለም የሴቶች የእግር ኳስ ጨዋታ የሚጠናቀቀው እሁድ ሰኔ 28 ቀን ነው።

የሜዳ ቴኒስ

በቴኒስ ባለሙያዎች ማኅበር ፉክክር በወንዶች ጨዋታ ሠርቢያዊው ኖቫክ ጆኮቪች በከፍተኛ ነጥብ በመምራት ላይ ይገኛል። የስዊዘርላንዱ ሮጀር ፌዴሬር እና የብሪታንያው አንዲ ሙራይ በሁለተኛ እና ሦስተኛነት ይከተሉታል። በተመሳሳይ ዘርፍ የሴቶች ፉክክር ደግሞ አሜሪካዊቷ ሴሬና ዊሊያምስ በቀዳሚነት እየገሰገሰች ነው። የቼክ ሪፐብሊኳ ፔትራ ክቪቶቫ እና ሮማኒያዊቷሲሞና ሐሌፕ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ናቸው።

የመኪና ሽቅድምድም

በፎርሙላ አንድ የአውስትሪያ ግራንድ ፕሪ የመኪና ሽቅድምድም ትናንት ጀርመናዊው ኒኮ ሮዝበርግ አሸናፊ ሆኗል። የመርሴዲስ መኪና የቡድን ኃላፊ ቶቶ ቮልፍ ግን የኒኮ ሮዝበርግ የቡድን የበላይነት ለስፖርቱ እንደማይበጅ ተናግረዋል። ኒኮ ሮዝበርግ በመርሴዲስ ተሽከርካሪው የሚፎካከረው የቡድን አባሉ ሌዊስ ሐሚልተንን ቀድሞ ነው ትናንት አሸናፊ የሆነው። ኒኮ ትናንት በማሸነፉ የዘንድሮ ውድድር አጠቃላይ አሸናፊ ለመሆን በግስጋሴ ላይ ለሚገኘው እና 10 ነጥብ ብቻ ለቀረው የቡድኑ አባል ሌዊስ ሐሚልተን ጥሩ እንዳልነበረም የቡድን መሪው አክለው ተናግረዋል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዘንድሮ አራተኛ ሆኖ ያጠናቀው ማንቸስተር ዩናይትድን ለማጠናከር አሠልጣኝ ሉዊስ ቫን ጋል አዳዲስ ተጨዋቾችን ለማስፈረም በዝግጅት ላይ መሆናቸው ተገለጠ። ማንቸስተር ዩናይትድ ሊያስፈርማቸው ካሰባቸው ተጨዋቾች መካከል የጀርመኑ ባየር ሙይንሽን አማካይ ባስቲያን ሽቫይንሽታይገር እና የስፔኑ ሪያል ማድሪድ ተከላካይ ሠርጂዮ ራሞስይገኙበታል ተብሏል። የ30 ዓመቱ ጀርመናዊ ባስቲያን ከባየርን ሙይንሽን ጋር ያደረገው ውል በሚቀጥለው ዓመት ይጠናቀቃል ተብሏል። ከባስቲያን ሽቫይንሽታይገር በአንድ ዓመት የሚያንሰው ሠርጂዮ ራሞስ ከሪያል ማድሪድ ጋር የገባው ውል እንደ ጎርጎሪዮሳዊው አቆጣጠር እስከ 2017 ድረስ የሚዘልቅ መሆኑ ይታወቃል።

ተጨዋቾችን በማስፈረሙ ዙሪያ በሪያል ማድሪድ እና በማንቸስተር ዩናይድ መካከል በቅርቡ ውይይት እንደሚኖርም ተጠቅሷል። ሪያል ማድሪድ በግብ ጠባቂው ዴቪድ ዴ ጊያ ላይ ዓይኑን አሳርፏል። ስፔናዊው ግብ ጠባቂ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር የገባው ውል እንደ ጎርጎሪዮሳዊው አቆጣጠር ከ2016 ወዲያ ለማራዘም ፍላጎት እንደሌለው አስታውቋል።

የማንቸስተር ዩናይድ አሰልጣኝ ሉዊስ ቫን ጋል ቡድናቸውን በተለይ ለማጠናከር የሚፈልጉት በቀኝ ተመላላሽ፣ በመሀል ተከላካይ እና አማካይ እንዲሁም አጥቂ ተጨዋቾች መሆኑ ተጠቅሷል። የፒ ኤስ ቪ አይንዶቨን የክንፍ ተጨዋች ሜምፊስ ዴፓይን በ31 ሚሊዮን ፓውንድ በእጁ ያስገባው ማንቸስተር ዩናይትድ የቶትንሀሙ ሐሪ ኬን ላይም ዓይኑን ጥሏል። ማንቸስተር ዩናይትድ የባርሴሎናው የቀኝ ተመላላሽ ብራዚሊያዊው ዳኒ አልቬስን በማስመጣት ወደ ቡድኑ መቀላቀል ቋምጦ ነበር። ሆኖም ዳኒ አልቬስ ከባርሴሎና ጋር የገባውን ውል በካምፕ ኑ ማደሱ ተነግሯል።

ይኽ በእንዲህ እንዳለ ዳኒ አልቬስ ባለፈው ረቡዕ ብሔራዊ ቡድኑ ብራዚል በኮሎምቢያ 1 ለዜሮ በተረታበት ጨዋታ ኔይማር ባሳየው ባሕሪ በቀይ መሰናበቱ ቡድኑ ብራዚልን እንደሚጎዳ አማሮ ተናገረ።

የ23 ዓመቱ ኔይማር ብራዚል ከኮሎምቢያ ጋር ያደረገችው የደቡብ አሜሪካ ዋንጫ ጨዋታ እንደተጠናቀቀ የኮሎምቢያው ጃይሰን ሙሪሎን በግንባሩ ለመግጨት ሙከራ በማድረጉ ዳኛው በቀጥታ የቀይ ካርድ ሰጥተውታል። ያም ብቻ አይደለም ኔይማር የመሀል ዳኛው ኤንሪኬ ዖሰስን ወደ መልበሻ ክፍል ሲያመሩ የስታዲየሙ የውስጥ መተላለፊያ ላይ አፀያፊ ስድብ በመሳደቡ ለተጨማሪ ችግር ዳርጎታል። ኔይማር በቀጣይ አራት ጨዋታዎች ላይ እንዳይሳተፍ ቅጣት የተጣለበት ወዲያው ነበር።

ለብራዚል ቡድን ለበርካታ ዓመታት በመሰለፍ የረዥም ጊዜ ልምድ ያካበተው ዳኒ አልቬስ የ23 ዓመቱ ወጣት ኔይማር ከባላጋራ ቡድን ተጨዋቾች የሚደርስበትን ትንኮሳ በዘዴ እና በትዕግስት ማሳለፍ ይገባዋል ብሏል። «ተረጋግቶ ከዚህ ሁሉ ነገር ትምህርት በመውሰድ ብራዚልን እጅግ በጣም የሚጎዱ መሰል ስህተቶችን እንዳይፈፅም ነግሬዋለሁ።» ሲል ዳኒ አልቬስ ለጋዜጠኞች አስረድቷል።

አያይዞም «ቅጣቱ እጅግ የከፋ ነው። ሌላ ተጨዋች ቢሆን ኖሮ ይህን ያህል ነገር አይከርበትም ነበር። ለኛ በጣም መጥፎ ነው። ልዩነት ፈጣሪያችንን ነው ያጣነው።» ብሏል። የብራዚል የእግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ዛሬ ይፋ እንዳደረገው ከሆነ ኔይማር ቺሊን ለቆ እንዲወጣ የተላለፈበትን ውሳኔ ፌዴሬሽኑ ይግባኝ እንደማይል ካሳወቀ በኋላኔይማር ሀገሪቱን ለቆ እንደሚወጣ ዛሬ አስታውቋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic