የስፖርት ዘገባ፤ ሚያዝያ 19 ቀን፣ 2007 ዓ.ም | ስፖርት | DW | 28.04.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ፤ ሚያዝያ 19 ቀን፣ 2007 ዓ.ም

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌን ዋና አሠልጣኝ አድርጎ መምረጡን ይፋ አድርጓል። አሠልጣኙ የተመረጡት ከቀረቡት አራት አሠልጣኞች የውድድር መስፈርቱን በማሟላት ልቀው በመገኘታቸው ነው ሲል ፌዴሬሽኑ ተናግሯል።ታዋቂ የስፖርት ጋዜጠኛ እና ተንታኝ አሠልጣኙ ለቦታው ብቃት የላቸውም፣ የተመረጡበት መስፈርት ይፈተሽ ሲል ተችቷል።

ከ14 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ በለንደን ማራቶን በሴቶች ውድድር አሸናፊ ሆናለች። በወንዶቹ ግን ኬንያውያን ልቀው ተገኝተዋል። በሐምቡርግ ማራቶንም ኢትዮጵያ አሸናፊ ሆናለች። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አዲስ አሠልጣኝ መምረጡ ታወቀ። ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሠልጣኖች መካከል አቶ ዮሐንስ ሳህሌ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ እግር ኳስ ቡድን በዋና አሰልጣኝነት መመረጣቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይፋ አድርጓል። የፌዴሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንድምኩን አላየው።

«ቅዳሜ የሥራ አስፈፃሚው ባኪያሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ከፕሪሚየር ሊግ አሠልጣኞች መካከል አቶ ዮሐንስ ሣህሌን ዋና አሠልጣኝ አድርጎ መርጧል።»

አሠልጣንኝ ዮሐንስ ሳህሌ በዋና አሰልጣኝነት የተመረጡትምርጫው ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ሆኖ በመገኘቱ ከቀረቡት አራት ተወዳዳሪዎችመካከል በብቃት እና ደረጃቸው ልቀው በመገኘታቸው እንደሆነ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።

የቀድሞው የአዲስ ጉዳይ ጋዜጣ ምክትል አዘጋጅ የነበረው የስፖርት ጋዜጠኛ እና ተንታኝ ኢብራሒም ሻፊ የአሠልጣኝ ዮሐንስ ሣህሌ ምርጫ ላይ ብዙ ግልፅ ያልሆኑ እንቆቅልሽ ነገሮች አሉ ይላል።

«የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሠልጣኞችን ሲመርጥ ምን መስፈርት አስቀምጦ እንነበር በጣም እንቆቅልሽ ነው።»

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምርጫውን ያኪያሄድኩበት በሚለው መስፈርት መሰረት አሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም እና ፋሲል ተካልኝንየሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ እንደሰጣቸው ለማወቅ ተችሏል። አቶ ወንድምኩን አላዩ ፌዴሬሽኑ ዋና አሠልጣኙን የመረጠበትን መስፈርት እንዲህ ያብራራሉ፡፡

አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በአሠልጣኝነት የያዙትን ደደቢት ቡድን ከነበረበት አቋም ፈቀቅ ማድረግ አልቻሉም የሚለው ጋዜጠኛ ኢብራሒም ሻፊ አሠልጣኙ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስመዘገቧቸው ውጤቶች ደካማ እንደነበሩ ጠቅሷል። የሞርሺየስን ቡድን ከማለፍ ውጪ ጠንከር ያለ ዓለም አቀፍ ቡድን ሲገጥማቸው በሀገር ቤትም ሆነ በውጪ ሀገር ግብ ማስቆጠር ያልቻሉ አሠልጣኝ ናቸው የሚለው ጋዜጠኛ ኢብራሒም የአሠልጣኙ ድክመቶች የሚላቸውን ነጥቦች እንደሚከተለው ይተነትናል።

በዕጩነት ከቀረቡት አራት ተፎካካሪዎች መካከል፦ማለትም ከአሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም፣ፋሲል ተካልኝ እና አሸናፊ ከበደ መካከል አስልጣኝ ዮሐንስ ሣህሌ ልቀው መገኘታቸውን ፌዴሬሽኑ ገልጧል። «በማወዳዳሪያው መስፈርት መሰረትም ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም እና ፋሲል ተካልኝ የሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ እንዳገኙም ለማወቅ ተችሏል» ሲል ፌዴሬሽኑ ትናንት በኢሜል ባሰራጨው መልእክቱ አስታውቋል። አስልጣኝ ዮሐንስ ሣህሌ ተገምግመው ስለተመረጡበት መስፈርት አቶ ወንድምኩን አላዩ ሲያብራሩ እንዲህ ይላሉ።

አሠልጣኝ ዮሐንስ ሣህሌ የአሠልጣኝነት ሕይወታቸው አጭር ጊዜ ሆኖ ሳለ እንዴት ለብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ተደርገው ይቀጠራሉ? የረዥም ጊዜ የአሠልጣኝነት ዘመን ልምድ ያላቸውን ተወዳዳሪዎች በምን በልጠው ተመረጡ የሚለው ጋዜጠኛ ኢብራሒም ሻፊ ጥያቄ ማቅረብ አለብን ሲል ይቀጥላል።

ለውድድር የቀረቡት አሠልጣኝ ዮሐንስ ሣህሌ ከህጻንነታቸው አንስቶ በተለያዩ የእግር ኳስ ቡድኖች የተጫወቱ መሆናቸውን፣ ለቅዱስ ጊዮርጊስ እና ለብሔራዊ ቡድን ከተጫወቱ በኋላ በውጭ ሀገር በከፍተኛ የአሠልጣኝነት ስልጠና መውሰዳቸውን ፌፌሬሽኑ አስታውቋል።

አሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም፣ፋሲል ተካልኝ እና አሸናፊ ከበደ ቢያንስ ከአስልጣኝ ዮሐንስ ሣህሌ ይሻላሉ ያለው ጋዜጠኛ ኢብራሒም ሻፊ ሌሎች የተሻለ ልምድ ያላቸው አሠልጣኞችን ለውድድር ሳያቀርቡ «አራቱ ሰዎች ዕጩ የሆኑበት መንገድ በራሱ እንኳን» የሚገርም ነው ብሏል።

ይልቁንስ ፌዴሬሽኑ አሠልጣኙ በውጭ ሀገር አገኘሁት ያሉትን ስልጠና ተዓማኒነት ሊመረምር ይገባል ሲል ጋዜጠኛ ኢብራሂም አስጠንቅቋል። የፌዴሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንድምኩን አላዩ የአሠልጣኙ የውጭ ሀገር ሥልጠና ተዓማኒነት ላይ የሚባል አንዳንድ ጭምጭምታ ቢኖርም በአሁኑ ወቅት አጠራጣሪ ነገር አላየንም ብለዋል።

ለአንድ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝነት የሚታጭ ሰው የግል ሠብዕናም ለቡድኑ ውጤት የሚኖረው ተፅዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ አዲስ የተመረጡትን አሠልጣኝ ሰብዕናን በተመለከተ ምን ጥናት አድርጋችኋል ለሚለው ጥያቄ አቶ ወንድምኩን ዝርዝሩን አብራርተዋል።

ጋዜጠኛ ኢብራሒም ሻፊ ከጥቂት ወራት በኋላ በቻን 2016 እና በ2017 የአፍሪካ ዋንጫ በአንፃራዊነት ከዚህ ቀደም ቀለል ያሉ ቡድኖች ለገጠሙት ብሔራዊ ቡድን ቀና ነገር እንደሚመኝ በመግለጥ ጊዜው ያላለፈበት ነው ያለውን መልእክት አስተላልፏል።

አትሌቲክስ

ትናንት በተከናወነው የለንደን ማራቶን የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያዊቷ ትዕግስ ቱፋ በ2:23:22 በመግባት በአንደኛነት ድል ተጎናፅፋለች። የትናንቱ ድል ከዛሬ 14 ዓመት ወዲህ በለንደን ማራቶን ሩጫ ደራርቱ ቱሉ ካገቸችው ድል ወዲህ የመጀመሪያው ሆኖ ተመዝግቧል። በዚህ ውድድር ሌላኛዪቱ ኢትዮጵያዊት ትርፊ ፀጋዬ በኬኒያዊቷ ማሪ ኬታኒ ለጥቂት በአንድ ሠከንድ ብቻ ተቀድማ በ2:23:41 ሦስተኛ ወጥታለች። በወንዶች የለንደን ማራቶን የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያዊው ጥላሁን ረጋሳን አምስተኛ ጣልቃ በማስገባት ኬንያውያን ከ1ኛ እስከ 6ኛ ደረጃ ተቆጣጥረዋል። ኬኒያዊው ኤሊውድ ኪፕቾግ ውድድሩን በ2:04:42 በማጠናቀቅ አንደኛ ሆኗል።

ጀርመን ሐምቡርግ ትናንት በተከናወነ የማራቶን ሩጫ ደግሞ በሴቶች ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ መሠረት ኃይሉ በ2:25:41 በመግባት የአንደኛነትን ድል ተጎናፅፋለች። በወንዶች የሐምቡርግ ማራቶን የኬኒያው አትሌት ሉቃስ ሮቲች በ2:07:17 አንደኛ ሲወጣ የኤርትራው ግርማይ ገብረሥላሴ በ2:07:47 ኹለተኛ፣ እንዲሁም ሌላኛው የኬኒያ ሯጭ ስቴፋን ቼቦጉት በ2:08:01 በሦስተኛነት አጠናቋል። በሐምቡርጉም ሆነ በለንደኑ ድል ክብር ወሰን አለመሰበሩ ታውቋል። የሴቶች የማራቶን የሩጫ ውድድር ክብር ወሰን ዓምና በኢትዮጵያዊቷ ነፃነት አቤዮ በበ2:24:12 የተያዘ ነው።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ትናንት ማንቸስተር ዩናይትድ በኤቨርተን 3 ለ ዜሮ ተሸንፏል። ቸልሲ ከአርሰናል ያለምንም ግብ ተለያይቷል። በዚህም መሠረት የደረጃ ሠንጠረዡን አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ቸልሲ በ77 ነጥብ ይመራል። ማንቸስተር ሲቲ በ67 ይከተላል። አርሰናል ከማንቸስተር ሲቲ በግብ ልዩነት ብቻ ተበልጦ ሦስተኛ ነው፤ ግን አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ይቀረዋል። ማንቸስተር ዩናይትድ 65 ነጥብ አለው ። አራተኛ ነው። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ሊቨርፑል በ58 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ከትናንት በስትያ ሑርታ ቤርሊንን 1 ለዜሮ ያሸነፈው ኃያሉ ባየር ሙይንሽን የጀርመን ቡንደስ ሊጋ ዋንጫን ከወዲሁ በእጁ ማስገባቱ ተረጋግጧል። የደረጃ ሠንጠረዡን በ76 ነጥብ እየመራ ነው። ቮልፍስቡርግ በ61 ነጥብ በርቀት ይከተለዋል። ቦሩስያ ሞይንሽን ግላድባኅ በ57 ነጥብ በሦስተኛነት እየተከተለ ነው። ባየር ሙይንሽን ለሻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ ፍልሚያ ከፊታችን ረቡዕ ሣምንት ከባርሴሎና ጋር ይገናኛል። ባየር ሙይንሽን በካምፕኑ ስታዲዬም የሚያደርገው ጨዋታ ከ40 ቀናት በኋላ በርሊን ለሚካሄደው ፍጻሜ መንገድ ጠራጊ ነው።

የባየር ሙይንሽን አሠልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ ረዥም ዕድሜያቸውን እንዳሳለፉበት የተናገሩለት ባርሴሎና ላይ ጠንካራ ተጨዋቾች ነው የሚጠብቋቸው። ባርሴሎና እነ ኔይማር፣ ሉዊስ ሱዋሬዝ፣ ሊዮኔል ሜሲ እና አንድሬ ኢኔስታ የመሳሰሉት ተጨዋቾች ይዞ ነው የሚጠብቃቸው። ከነባርሴሎና ጨዋታ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ሌላኛው የስፔን ቡድን ሪያል ማድሪድ እና የጣሊያኑ ጁቬንቱስ ይጋጠማሉ። በላሊጋው ከትናንት በስትያ ሪያል ማድሪድ ሴልታቪጎን 4 ለ2 በመርታት ከመሪው ባርሴሎና ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ማጥበብ ችሏል። 81 ነጥብ ካለው ባርሴሎና የማድሪድ ልዩነቱ 2 ነጥብ ብቻ ነው። አትሌቲኮ ማድሪድ በ72 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ቡጢ

ዩክሬናዊው ቭላድሚር ክሊችኮ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ አሜሪካዊው ብሪያን ጄኒንግስን በዳኛ ውሳኔ በማሸነፍ የከባድ ሚዛን ቀበቶውን ማስጠበቅ ችሏል። ቭላድሚር ክሊችኮ ቅዳሜ ዕለት ያከናወነው የቡጢ ፍልሚያን ጨምሮ በተከታታይ ሲኢሸንፍ ለ18ኛ ጊዜ ሲሆን፤ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ውድድሩን ሲኢደርግ ደግሞ ከ7 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው።

የኢትዮ ኮሎኝ ስፖርት እና ባሕል ማኅበር በሊቢያ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ ኢትዮጵያውያንን በማሰብ ቅዳሜ እለት በጀርመን ኮሎኝ ከተማ የሻማ ማብራት ስነስርዓት ማኪያሄዱ ታውቋል።

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ ከታች የሚገኘውን የድምጽ ማጫወቻ ይጫኑ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic