የስፖርት ዘገባ፤ ሚያዝያ 12 ቀን፣ 2007 ዓ.ም | ስፖርት | DW | 20.04.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ፤ ሚያዝያ 12 ቀን፣ 2007 ዓ.ም

እሁድ ሚያዝያ 11 ቀን፣ 2007 ዓ.ም ሊቢያ ውስጥ በኢትዮጵያውያን ላይ በተከሰተው ዘግናኝ ግድያ የተሰማንን ጥልቅ ሐዘን በቅድሚያ በመግለጥ መፅናናትን እንመኛለን። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ጨዋታ ቸልሲ መሪነቱን አጠናክሯል። የፊታችን ቅዳሜ ቀሪ አንድ ተስተካካይ ጨዋታውን የሚያከናውነው ሊቨርፑል በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ደረጃውን እያሻሻለ ነው።

አራቱም ኃያል ቡድኖች ሥር ተጠግቷል። ማንቸስተር ዩናይትድ ለቸልሲ እጅ ሰጥቷል። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ፓዴርቦርንን 3 ለዜሮ አሸንፏል። አሠልጣኙ ግን ቦሩስያ ዶርትሙንድ ለውጥ ያስፈልገዋል በማለት ከቡድኑ በገዛ ፈቃዳቸው መሰናበት እንደሚፈልጉ ይፋ ሰነባብተዋል። ሌሎች አጫጭር የስፖርት ዜናዎችም ይኖሩናል አብራችሁን ቆዩ!

በደቡብ አፍሪቃ እና በሊቢያ አሰቃቂ ግድያ ለተፈፀመባቸው እና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖቻችንን በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የእግር ኳስ ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ የኅሊና ጸሎት እንደሚደረግ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ። ፌዴሬሽኑ ዛሬ ባወጣው መግለጫ «በደቡብ አፍሪካ እና በሊቢያ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመውን ዘግናኝና አሰቃቂ የወንጀል ድርጊት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና መላው የእግር ኳስ ስፖርት ቤተሰቦች በጥብቅ ያወግዛሉ፡፡በጉዳቱ ለተጠቁት የኢትዮጵያ ዜጎች የተሰማቸውን ሃዘን እየገለጹ ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ይመኛሉ» ብሏል።

በሜዳው ዌስትሀም ዩናይትድን እሁድ 2 ለምንም የረታው ማንቸስተር ሲቲ በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አራተኛ ደረጃውን አጠናክሯል፤ ዳቪድ ሲልቫን ግን በቃሬዛ ከሜዳው አስወጥቷል። በደረጃ ሠንጠረዡ በሦስተኛነት ከሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ችሏል። ማንቸስተር ሲቲ 64 ነጥብ ይዞ አራተኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው።

ከትናንት በስትያ በመሪው ቸልሲ 1 ለባዶ የተረታው ማንቸስተር ዩናይትድ በ65 ነጥቡ ተወስኗል። ቸልሲ በ76 ነጥብ አንደና ደረጃ ላይ ይገኛል፤ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ይቀረዋል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው አርሰናል በአንደኛ ደረጃ ከሚገኘው ቸልሲ የነጥብ ልዩነቱ 10 ነው። 57 ነጥብ ይዞ 5ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ሊቨርፑል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ደግሞ ዘጠኝ አድርሶታል። ሊቨርፑል እንደ ቸልሲ እና አርሰናል አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ይቀረዋል። 36 ነጥብ ይዞ 13ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ዌስት ብሮሚች አልቢኖ ጋር የፊታችን ቅዳሜ ይገናኛል። በFA CUPግጥሚያ ሊቨርፑል ትናንት በአስቶን ቪላ 2 ለ1 ተረትቷል።

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ቅዳሜ እለት ፓዴርቦርንን 3 ለ ዜሮ አሸንፏል። የቦሩስያ ዶርትሙንድ ደጋፊዎች ከቡድኑ እንደሚሰናበቱ በቅርቡ ይፋ ላደረጉት አሠልጣኝ ዬይርገን ክሎፕ ድጋፋቸውን ገልጠዋል። አሠልጣኙ ከመኪናቸው ወርደው ለደጋፊዎች በመፈረም ተመልሰው ወደ መኪናቸው በመግባት አቅንተዋል። በወቅቱ የቦሩስያ ዶርትሙንድ ደጋፊዎች አሠልጣኝ ዬይርገን ክሎፕ ቡድናችንን ጥለው ከሚሄዱ 2 ለ3 መሸነፉ ይሻለን ነበር ሲሉ ለአሠልጣኙ ያላቸውን ፍቅር አሳይተዋል። የ41 ዓመቱ ቶማስ ቱሸል ከሁለት ሣምንት በኋላ የቦሩስያ ዶርትሙንድ አዲስ አሠልጣኝ ሆነው ሥራ እንደሚጀምሩ ይፋ ሆኗል።

በደረጃ ሠንጠረዡ በኹለተኛነት የሚገኘው ቮልስፍስቡርግ እሁድ ከሻልካ ጋር አንድ እኩል ተለያይተዋል። ብሬመን ሐምቡርግን 1 ለዜሮ ረትቷል። በደረጃ ሠንጠረዡ ባየር ሌቨርኩሰን 54 ነጥብ ይዞ በሦስተኛነት ይገኛል። ቮልስፍስቡርግ በደረጃ ሠንጠረዡ 61 ነጥብ አለው ከመሪው ባየር ሙይንሽን የነጥብ ልዩነቱ 12 ነው።

መሪው ባየር ሙይንሽን ከትናንት በስትያ ሆፈንሀይምን 2 ለዜሮ በማሸነፍ ከነበረው 70 ነጥብ ላይ 3 ደምሯል። ለሻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ ነገ በሜዳው አሊያንስ አሬና ከፖርቺጊዙ ፖርቶ ጋር ይገናኛል። ባየርን ሙይንሽን ባለፈው ግጥሚያ በፖርቱ ሜዳ 3 ለ1 መረታቱ ይታወሳል። ወደ ግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ የመልስ ግጥሚያውን ቢያንስ 2 ለዜሮ ማሸነፍ ይጠበቅበታል።

ባየርን ሙይንሽን እንደ ጎርጎሪዮሳዊው አቆጣጠር በ2005 በቸልሲ ከሻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍፃሜ የተባረረ ሲሆን፤ በ2000 ዓም ደግሞ ከግማሽ ፍፃሜው በሪያል ማድሪድ መሰናበቱ ይታወሳል። ባየርን ሙይንሽን ለሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ ባለፈው ከፖርቶ ጋር ሲገናኝ ለ27 ጊዜያት መሆኑ ነበር። የኹለት ጊዜያት የሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊው ፖርቶ በዚህ የውድድር ዘመን ከሜዳው ውጪ ባደረጋቸው 5 ጨዋታዎች ሦስቱን አሸንፏል። ባየርን ሙይንሽን ዘንድሮ በሜዳው ያደረጋቸውን ጨዋታዎች በአጠቃላይ ድምር በ13 ለዜሮ ውጤት ማሸነፉ ይታወቃል።

Philipp Lahm

በነገው እለት የጣሊያኑ ጁቬንቱስ ከፈረንሣዩ ሞናኮ ጋር ለሻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍፃሜ ይጋጠማል። ጁቬንቱስ ባለፈው ግጥሚያ 1 ለዜሮ አሸንፎታል። የስፔኑ ባርሴሎና የፈረንሣዩ ፓሪስ ሳንጀርሜን ጋር በሜዳው ካምፕ ኑ ስታዲዬም ይጋጠማል። በሜዳው የተጫወተው ፓሪስ ሳንጀርሜን 3 ለ1 መሸነፉ ይታወሳል። የሻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍጻሜ ግጥሚያ ከነገ በስትያም ቀጥሎ ኹለቱ የስፔን ቡድኖች ሪያል ማድሪድ እና አትሌቲኮ ማድሪድ ይገናኛሉ። ቀደም ሲል ያለምንም ግብ ተለያይተዋል።

የስፔን ላሊጋን ባርሴሎና በ78 ነጥብ እየመራ ነው። ሪያል ማድሪድ በ76 ይከተላል። አትሌቲኮ ማድሪድ በ69 ነጥብ ይሰልሳል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዋሊያዎቹ አሠልጣኝ ፖርቺጊዙ ማሪያኖ ባሬቶ ከ10 ቀን በኋላ በስምምነት ከቡድኑ እንደሚሰናበቱ ባሳለፍነው ቅዳሜ አስታውቋል። አሠልጣኙ ከቦታቸው ለመነሳታቸው እጅግ ዘግይተዋል ሲሉ በርካቶች ትችታቸውን አሠምተዋል። በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በወር 18 ሺህ ዶላር ደሞዝተኛ የሆኑት ማሪያኖ ባሬቶን ፌዴሬሽኑ ተጨማሪ የሦስት ወር ደመወዝ እንደሚከፈላቸው ገልጧል። የብሔራዊ ቡድኑ የወደፊት አሠልጣኝ ማን ሊሆን እንደሚችል ገና የታወቀ ነገር የለም። የሚታወቀው ነገር ቢኖር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የውጭ ሀገር አሠልጣኝ አልቀጥርም ማለቱ ነው። በጥቂት ቀናት ውስጥ የአሰልጣኞች ውድድር ተደርጎ አዲስ አሠልጣኝ እንደሚቀጠርም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።

የመኪና ሽቅድምድም

ሌዊስ ሐሚልተን ትናንት በባሕሬን ግራንድ ፕሪክስ የመኪና ሽቅድምድም አሸናፊ ሆኗል። ባለፈው ሣምንትም የቻይና ውድድር አሸናፊው ሌዊስ ሐሚልተን ነበር። ካለፉት አራት ተከታታይ ውድድሮች ሦስቱን ከአጠቃላይ 11 ፉክክሮች ዘጠኙን በማሸነፍ ሌዊስ ሐሚልተን እየገሰገሰ ነው። በመርሴዲስ መኪና የተወዳደረው ሌላኛው የቡድኑ አባል ኒኮ ሮዝበርግ ትናንት በፌራሪ አሽከርካሪው ኪሚ ራይኮነን ተቀድሞ ሦስተኛ ወጥቷል።

በሜዳ ቴኒስ ግጥሚያ የዓለማችን ቁጥር አንድ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ሠርቢያዊው ኖቫክ ጆኮቪች ትናንት በሞንቴ ካርሎ ውድድር የቼክ ተወላጁ ቶማስ ቤርዲችን 7-5 እና 6-3 በሆነ ልዩነት አሸንፎታል።

በ100 ሜትር የሩጫ ውድድር ደግሞ ትናንት ሪዮ ውስጥ ጃማይካዊው ኡስያን ቦልት ማሸነፍ ችሏል። ቦልት ይከተለው ከነበረው ሪያን ባይሌ በ30 ሜትር ርቀት ልዩነት በመፍጠን ውድድሩን በአንደኛነት ቢያጠናቅቅም ባስመዘገበው ሠዓት ግን መከፋቱን ገልጧል። ውድድሩን በአንደኛነት ለማጠናቀቅ ያስመዘገበው 10.12 ሠከንድ ነበር።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic