የስፖርት ዘገባ፤ መጋቢት 21 ቀን፣ 2007 ዓ.ም | ስፖርት | DW | 30.03.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ፤ መጋቢት 21 ቀን፣ 2007 ዓ.ም

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከበርሊን ማራቶን እስከ ቻይና አገር አቋራጭ የሩጫ ፉክክር ብሎም የካርልስባድ ካሊፎርኒያ ውድድር አመርቂ ድሎችን ተቀዳጅተዋል። በዩሮ 2016 የእግር ኳስ የማጣሪያ ፍልሚያ ጆርጂያ ጀርመንን ለግማሽ ሠዓት ያህል ተገዳድራለች፤ ከመሸነፍ ግን አልዳነችም። ትንሺቱ ጅብራልታር እንደለመደችው የግብ ጎተራ ሆናለች።

በቻይና ኩያንግ ከተማ ቅዳሜ ዕለት በተኪያሄደው ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (IAAF)ሀገር አቋራጭ የዓለም ውድድር በተለይ በወጣቶች ኢትዮጵያ በወንድም በሴትም ድል ቀንቷታል። በሴቶች ውድድር ለተሰንበት ግደይ በ 19:48 በአንደኛነት በማጠናቀቅ በዓለም አቀፍ መድረክ የመጀመሪያዋ የሆነውን የወርቅ ሜዳሊያ አጥልቃለች። ደራ ዲዳ በአንድ ሠከንድ ተቀድማ በኹለተኛነት ብር ስታስገኝ፣ እታገኝ ወልዱ በ 19:53 ነሐስ ተሸልማለች። ከአራተኛ በስተቀር አምስተኛ እና ስድስተኛም ኢትዮጵያውያት ነበሩ። ምህረት ተፈራ እና ዳግማዊት ክብሩን በማስከተል በአራተኛነት ያጠናቀቀችው የኬንያዋ ሯጭ ዴይሲ ኬፕጄሚ ናት።

በወንዶች ፉክክር ያሲን ሐጂ በ23:42 አንደኛ በመውጣት ወርቅ አስገኝቷል። ከሴቶች ውድድር በተቃራኒው ኬንያውያን ከ2 እስከ 4 ያለውን ደረጃ ተቆጣጥረውታል። የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር የኢትዮጵያ ዘጋቢ ኤልሻዳይ ነጋሽ በቻይና የተገኘው ውጤት የተሻለ ቢሆንም የበለጠ መሥራት እንደሚገባ ጠቁሟል።

በዚሁ የቻይና ኩያንግ ዓለም አቀፍ ውድድር በአዋቂዎች በወንድም በሴትም ኬንያውያን አይለው ታይተዋል። ጄኦፍሬይ ኪፕሳንግ በ34:52 አንደኛ ሲወጣ የሀገሩ ልጅ ቤዳን ካሮኪ ሙቺሪ በ35:00 ኹለተኛ ወጥቷል፤ ኢትዮጵያዊው ሙክታር ኢድሪስ 35:06 በመግባት ሦስተኛ ለመውጣት ችሏል። ከ9 ሠከንዶች በኋላ ሙክታርን በመከተል ሐጎስ ገብረሕይወት አራተኛ ለመውጣት ችሏል።

በሴቶች የአዋቂዎች ውድድርም ኬኒያዊቷ አግነስ ጄቤት ቲሮፕ በ26:01 አንደኛ ስትወጣ፣ ኢትዮጵያዊቷ ሠንበሬ ተፈሪ በ5 ሰከንዶች ተቀድማ በኹለተኛነት ማጠናቀቅ ችላለች። ነፃነት ጉደታ በ26:11 በመግባት ነሐስ አጥልቃለች።

በቻይና ኩያንግ ፉክክር በአጠቃላይ የሜዳሊያ ብዛት ኢትዮጵያ በቡድን እና በነጠላ 5 የወርቅ፣ 3 የብር እና 3 የነሐስ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ነው አንደኛ የወጣችው። ኬንያውያን በግል ባገኙት 3 የወርቅ፣ 5 የብር እና 1 የነሐስ ሜዳሊያ በቡድን ኹለተኛ ሆነዋል። ባህሪን እና ኡጋንዳ ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃን አግኝተዋል።

ከእዚሁ ከአትሌቲክስ ውድድር ሳንወጣ፦ ትናንት ጀርመን እና ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በተከናወኑ ውድድሮችም ኢትዮጵያውያን ድል ቀንቷቸዋል። በተለይ በካሊፎርኒያ የ5000 ሜትር የሩጫ ፉክክር ገንዘቤ ዲባባ በ14:48 በመግባት አንደኛ ከመሆኗም ባሻገር በዚህ ርቀት ዘርፍ ሦስተኛው ፈጣን ሠዓትን አስመዝግባለች። የዓለም ክብርወሰንን ለመስበር ግን 2 ሠከንንድ ብቻ ዘግይታለች።

አትሌት ገንዘቤ ዲባባ

አትሌት ገንዘቤ ዲባባ

በዚህ ውድድር ኢትዮጵያውያቱ ገለቴ ቡርቃ እና ውዴ ይመር ኹለተኛ እና ሦስተኛ በመሆን አጠናቀዋል። ገለቴ ከገንዘቤ በ25 ሠከንዶች ተቀድማ ነው የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ለመሆን የቻለችው። ውዴ ይመር በሦስተኛነት ያጠናቀቀችው በ15:13 በመግባት ነው።

በበርሊኑ ግማሽ ማራቶን የሩጫ ውድድር ደግሞ ትናንት ብርሐኑ ለገሰ በ59:45 አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል። ኬንያውያን እስከ አምስተኛ ደረጃን በመደዳ ተቆጣጥረዋል።

የዩሮ 2016 የእግር ኳስ ማጣሪያ ጨዋታ ውጤቶችን እንቃኛለን። ለማጣሪያው ትናንት ወደ ጆርጂያ ቲፊሊስ አቅንቶ የነበረው የዓለም ዋንጫ ባለቤቱ የጀርመን ቡድን አስተናጋጇ ጆርጂያን 2 ለዜሮ አሸንፏል። ከ54 ሺህ በላይ የስፖርት አፍቃሪያን በታደሙበት የቲፊሊስ ስታዲየም የጆርጂያ ቡድን በመጀመሪያው አጋማሽ ለግማሽ ሠዓት ያኽል ግብ ሳይቆጠርበት ያሳየው ጥረት የሚደነቅ ነው። ሆኖም በጨዋታው ጀርመኖች የበላይ ሆነው ታይተዋል። ግብ ሊሆኑ የሚችሉ ሙከራዎችንም አምክነዋል። በዕለቱ ኮከብ የነበረው የቦሩስያ ዶርትሙንዱ አማካይ እና አጥቂ ማርኮ ሮይስ በ39ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያውን ግብ ሲያስቆጥር፣ ቶማስ ሙይለር በ44ኛው ደቂቃ ላይ ኹለተኛዋን ግብ ከመረብ አሳርፏል። የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አሠልጣኝ ዮዓሒም ሎይቭ ከኹለተኛው አጋማሽ ይልቅ በመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አሠልጣኝ ዮኣሂም ሎይቭ

አሠልጣኝ ዮኣሂም ሎይቭ

«ቡድናችን በመጀመሪያው አጋማሽ ኹለት ወሳኝ ግቦችን አስቆጥሯል። በኹለተኛው አጋማሽ ደግሞ ጨዋታውን በትንሹም ቢሆን ለመቆጣጠር ችለናል። በእርግጥ ኹለት ተጨማሪ ግቦችን ማስቆጠር እንችል ነበር። ይልቅ በመጀመሪያው አጋማሽ ደስተኛ ነበርኩ፤ ምክንያቱም ፈጣን በሆነ መልኩ ወደፊት እየሄድን ተጫውተናል።»

ከማርኮ ሮይስ በተጨማሪ ተከላካዩ ጄሮሜ ቦኣቴንግ የጆርጂያ አጥቂዎች ወደ ግብ ጠባቂው አልፈው እንዳይሄዱ በአስተማማኝ ሁናቴ ገድቦ በመያዝ የማኑዌል ኖየርን ሥራ አቃሎለታል። RTLበተሰኘው የጀርመን ቴሌቪዥንጣቢያ ጨዋታውን ሲዘግብ የነበረው ጋዜጠኛ የጆርጂያ አጥቂዎች ኳስ ይዘው ወደ ጀርመን ግብ አቅራቢያ ሲጠጉ ጄሮሜ ቦኣቴንግን ፈጽመው አልፈው እንደማይሄዱ በእርግጠኝነት ሲናገር ተደምጧል። በእርግጥም የጄሮሜ ቦኣቴንግን አጥር ጥሶ ማለፍ የቻለ አልነበረም። ከ10 ሚሊዮን በላይ ተመልካቾች RTLበተሰኘው የጀርመን ቴሌቪዥንጨዋታውን እንደተከታተሉት ተዘግቧል።

ባስቲያን ሽቫይንሽታይገር

ባስቲያን ሽቫይንሽታይገር

በትናንቱ ጨዋታ የሰበሰበችው ሦስት ነጥብ ተደምሮ ጀርመን በምድብ መ በኹለተኛነት ትገኛለች። ፖላንድ በ11 ነጥብ የምድቡ መሪ ናት። መከረኛዋ ጂብራልታርን 6 ለ1 ያንኮታኮተችው ስኮትላንድ ነጥቧ ከጀርመን እኩል ነው፤ በግብ ክፍያ ልዩነት ግን ሦስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። አየርላንድ 8 ነጥብ አላት አራተኛ ናት። ጆርጂያ በ3 ነጥብ የምትበልጠው ምንም ነጥብ የሌላት ጂብራልታርን ብቻ ነው። የጀርመን ቡድን አምበል ባስቲያን ሽቫይንሽታይገር ነጥቡ ዝቅተኛ ከሆነ ቡድን ጋር መጋጠም አስቸጋሪ መሆኑን ጠቁሟል።

«ሦስት ነጥብ መሰብሰባችን ጠቃሚ ነበር፤ ያን አሳክተናል። እጅግ ካሽቆለቆለ ቡድን ጋር መጫወት ምንጊዜም ከባድ ነው፤ ጥሩ ሠርተናል ማለት እችላለሁ። እርግጥ ነው የተለያዩ ስህተቶችን ፈጽመናል፤ ከፊትት መሥመርም ቢሆን ማለቴ ነው። ያ ግን ይከሰታል። ምንም አይደለም፤ ሦስት ነጥብ ሠብስበናል፤ ጨዋታችንም ጥቱ ነበር። »

ባስቲያን ሽቫይንሽታይገር አስተናጋጇ ሀገር ጆርጂያ ቲፊሊስ ውስጥ ትናንት ለጀርመን ብሔራዊ ቡድን ለ109ኛ ጊዜ በመሰለፍ ከዬርገን ክሊንስማን በአንድ በልጧል። እስካሁን ለጀርመን ብሔራዊ ቡድን በብዛት በመሠለፍ ሎታር ማቲያስን የሚስተካከለው አልተገኘም፤ 150 ጊዜ ለጀርመን ተሰልፎ ተጫውቷል። ሚሮስላቭ ክሎዘ 137 ጊዜ በመሠለፍ በኹለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ፊሊፕ ላም ለ113 ጊዜያት ለጀርመን ቡድን ተሰልፎ ተጫውቷል።

አሪየን ሮበን

አሪየን ሮበን

ከምድብ ሀ ሆላንድ ከቱርክ ጋር አንድ እኩል ተለያይታለች። ቀደም ሲል ቱርክ 1 ለዜሮ አሸንፋ ነበር። ሆኖም 7 ነጥብ ባለው የሆላንድ ቡድን በ2 ተበልጣ 4ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። አይስላንድ በ12 ነጥብ ኹለተኛ፣ ቼክ ሪፐብሊክ በ13 ነጥብ ምድቡን ትመራለች። በምድብ ለ እስራኤልን 3 ለባዶ የረታችው ዌልስ በ11 ነጥብ እየመራች ትገኛለች። በምድብ ሐ ስፔን ዩክሬንን 1 ለዜሮ አሸንፏል። በምድቡ ስፔን 12 ነጥብ ይዞ ኹለተኛ ነው። ስሎቫኪያ በ15 ነጥብ ትመራለች።

በምድብ ሠ እንግሊዝ ሊትዋኒያን 4 ለዜሮ፣ ስዊዘርላንድ ኤስትላንድን 3 ለምንም አሸንፈዋል። ስሎቫኒያ ሣን ማሪኖን 6 ለዜሮ ረትታለች። ምድቡን እንግሊዝ በ15 ነጥብ እየመራች ትገኛለች። ስዊዘርላንድ በ9 ትከተላለች። ምድብ ረ ሩሜንያ በ13 ነጥብ ትመራለች። ምድብ ሰ ኦስትሪያ በ13 ነጥብ አንደኛ ስዊድን በ9 ኹለተኛ ናቸው። የሩስያ እና ሞንቴኔግሮ ግጥሚያ በ67ኛው ደቂቃ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ በመግባታቸው ያለምንም ግብ ጨዋታው ተቋርጧል። በጀርመን እና ጆርጂያ ጨዋታ ወቅትም ደጋፊዎች በተደጋጋሚ ወደ ሜዳ መግባታቸው ከፍተኛ ነቀፌታን አስከትሏል።

ሠባስቲያን ፌትል

ሠባስቲያን ፌትል

ምድብ ሸ ጣሊያን ከቡልጋሪያ ጋር ኹለት እኩል ወጥታለች፤ በ11 ነጥብ ደረጃዋ ኹለት ነው። መሪዋ ክሮሺያ ናት፤ 13 ነጥብ ሰብስባለች።በመጨረሻው ምድብ ፖርቹጋል በ9 እየመራች ነው ዴንማርክ በ7 ነጥብ ትከተላለች።

የመኪና ሽቅድምድም

በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ትናንት ማሌዢያ ውስጥ በተደረገው ውድድር ጀርመናዊው ሠባስቲያን ፌትል በፌራሪ ተሽከርካሪው የመጀመሪያ ድሉን ለመቀዳጀት ችሏል። ሌዊስ ሐሚልተን ኒኮ ሮዝበርግን ቀድሞ ኹለተኛ ወጥቷል።

ከኹለት ሣምንት በፊት አውስትራሊያ ውስጥ በተደረገው ሽቅድምድም ሠባስቲያን ፌትል በጥቅሉ 40 ነጥቦችን በመሰብሰብ ኹለተኛ ነበር የወጣው። በወቅቱ የአውስትራሊያ ሽቅድምድም አሸናፊው ሌዊስ ሀሚልተን የሰበሰበው ነጥብ 43 ነበር። ትናንት ድል የሠባስቲያን ቬትል ሆናለች።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic