የስፖርት ዘገባ፤ መጋቢት 14 ቀን፣ 2007 ዓ.ም | ስፖርት | DW | 23.03.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ፤ መጋቢት 14 ቀን፣ 2007 ዓ.ም

ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች በሮም ማራቶን በወንድም በሴትም አሸናፊ ሆነዋል። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ የዘንድሮ ውድድር ባየር ሙይንሽን በሜዳው ለመጀመሪያ ጊዜ ሽንፈት ገጥሞታል። በስፔን ላሊጋ ባርሴሎና ዋነኛ ተፎካካሪው ሪያል ማድሪድን አሸንፏል። የሊቨርፑሉ ሽቴፋን ዤራርድ ከሜዳ በቀይ ካርድ ተሰናብቷል።

በሮም ማራቶን ኢትዮጵያ በወንድም በሴትም የአንደኛ እና የኹለተኛ ደረጃን መቀዳጀት ችላለች። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ኃያሉ ባየር ሙይንሽንን በሜዳው ኃይል ነስቶታል። የትናንቱ ሽንፈት ለባየር ሙይንሽን በዘንድሮ ውድድር የመጀመሪያው ሽንፈት ሆኖ ተመዝግቧል። ሉዊስ ሱዋሬዝ ቡድኑ ባርሴሎና ዋነና ተቀናቃኙ ሪያል ማድሪድን ያሸነፈበትን ኹለተኛውን ግብ አስቆጥሮ ጮቤ ሲረግጥ፥ በቀድሞ ቡድኑ ሊቨርፑል በአማካይ የሚጫወተው ሽቴፋን ጄራርድ ከሜዳ በቀይ ተሰናብቷል። ማንቸስተር ዩናይትዶች አንፊልድ ላይ ባገኙት ድል ሊቨርፑሎችን አንገት አስደፍተው ተመልሰዋል።

ሮም ማራቶን ከፊል ገጽታ

ሮም ማራቶን ከፊል ገጽታ

በሮም ማራቶን የሩጫ ውድድር ትናንት ኢትዮጵያውያኑ አበበ ደገፋ እና ብርሐኑ አዲስ አንደኛ እና ኹለተኛ በመሆን ተከታትለው በመግባት ድል ተቀዳጅተዋል። በሴቶች ተመሳሳይ ውድድር በተመሳሳይ ውጤት መሠረት እና ፍቅሬ ድል ተጎናጽፈዋል። 15000 ሯጮች በተሳተፉበት በትናንትናው ዝናባማ ቀን የተኪያሄደው የሮም ማራቶን የሩጫ ፉክክር አበበ ደገፋ ውድድሩን በአንደኛነት ለማጠናቀቅ የፈጀበት ጊዜ 2 ሠዓት ከ12 ደቂቃ ከ23 ሠከንድ ነው። ብርሐኑ አዲስ ኹለተኛ የወጣው በአበበ በ9 ሠከንዶች ብቻ ተቀድሞ ነው። ጣሊያናዊው ጃመል ቻትቢ 2 ሠዓት ከ14 ደቂቃ ከ04 ሠከንድ በመግባት ሦስተኛ ለመሆን ችሏል።

በሮም ማራቶን የሴቶች ፉክክር መሠረት ቶልዋልቅ በአንደኛነት ለማጠናቀቅ የፈጀባት ጊዜ 2 ሠዓት ከ30 ደቂቃ ከ25 ሠከንድ ነው። ፍቅሬ ዊልቄ ከመሠረት በ36 ሠከንዶች ተቀድማ ኹለተኛ ለመሆን ችላለች። ልክ እንደወንዶቹ ሁሉ በሴቶችም ሦስተኛነት ደረጃ ያገኘችው ጣሊያን ናት። ጣሊያናዊቷ ዴቦራህ ቶኒዮሎ ውድድሩን በ2 ሠዓት ከ36 ደቂቃ ከ30 ሠከንድ በማጠናቀቅ ነው ሦስተኛ ለመውጣት የቻለችው።

የዓለማችን ቁጥር አንድ ምርጥ በረኛ ጀርመናዊው ማኑዌል ኖየር ትናንት ከባድ ስህተት ፈጽሟል። ቡድኑ ባየር ሙይንሽን ከቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ጋር ባከናወነው የትናንቱ ጨዋታ ግብ ጠባቂው ጉድ የሆነው በ29ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ከቀኝ ማዕዘን አቅጣጫ በፓትሪክ ሔርማን የተላከችውን ኳስ በቀጥታ አክርሮ በመምታት ለሞይንሽንግላድባኅ የመጀመሪያዋን ግብ ያስቆጠረው ብራዚሊያዊው ራፋኤል ነው። ለጀርመን ብሔራዊ ቡድንም ተሰላፊ የሆነው የባየር ሙይንሽኑ ግብ ጠባቂ ማኑዌል ኖየር ኳሷን መቆጣጠር ባለመቻሉ መስመሩን አልፋ ልትገባ ችላለች። ግብ ጠባቂው ጥቂት ሴንቲሜትሮች ወደ ፊት ወጣ ብዬ ቢሆን ኖሮ ግብ አይሆንም ሲል ተፀፅቷል።

ጀርመናዊው ግብ ጠባቂ ማኑዌል ኖየር

ጀርመናዊው ግብ ጠባቂ ማኑዌል ኖየር

«እንደሚመስለኝ ስህተት የሠራሁት ኳሷን ለመያዝ በመሞከሬ ነበር። በተለምዶ አደርግ የነበረው ወደፊት ወጣ ብዬ ኳሷን ገጭቶ ማራቅ ነበር። ግን ያን እንዳላደርግ በቃ አደጋው ጎላብኝ። በእርግጥም ኳሷ ከረር ብላ የተመታችው ከአስራ አንድ አስራ ኹለት ሜትር ርቀት ላይ ነበር። እንዲያም ሆኖ ጥሩ ነገር ለማድረግ ነበር የፈለግኹት፤ ኳሷ ግን መስመሩን አለፈች። 20 ሳንቲሜትር ወደፊት ወጣ ብዬ ቢሆን ኖሮ የቆምኩት ወደ ውስጥ አትገባም ነበር። ይኼ ሁሉ ተደማምሮ ነው።»

ትናንት የግብ ጠባቂው ማኑዌል ኖየር ቀን አልነበረም ማለት ይቻላል። ኹለተኛዋንም ግብ ያስቆጠረበት ይኸው ብራዚሊያዊ ግብ አዳኝ ራፋኤል ነበር። ከሌቨርኩሰን በውሰት የመጣው አማካይ ተጫዋች ክሪስቶፍ ክራመር በ76ኛው ደቂቃ ላይ የባየር ሙይንሽን ተከላካዮችን አታሎ የላካትን ኳስ ራፋኤል በማኑዌል እጅ ሥር አሾክሎ ከመረብ ማሳረፍ ችሏል። በዚህም ባየር ሙይንሽን በቦሩሲያ ሞይንሽንግላድባኅ 2 ለባዶ ሽንፈትን ቀምሷል። የመጀመሪያው ግብ እንዲገባ ለራፋኤል ኳሷን ያመቻቸው ፓትሪክ ሔርማን ቡድኑ ድንቅ ጨዋታ ማከናወኑን ገልጧል።

ሽንፈት የቀመሰው ባየር ሙይንሽን

ሽንፈት የቀመሰው ባየር ሙይንሽን

«ባየርን በዚህ የጨዋታ ዘመን በሜዳው ተሸንፎ አያውቅም ነበር። እናም ዛሬ ምንም እንኳን ኳስ አብላጫውን በእኛ ቁጥጥር ባትሆንም ድንቅ ጨዋታ ነው ያከናወንነው። ከዚያም ኹለት ግቦችን በድንቅ ሁናቴ አስቆጠርን። እንዲህ ነው ካሸነፉ አይቀር።»

በእርግጥም ኳስ አብላጫውን በባየርን ሙይንሽን ቁጥጥር ሥር ነበረች። ባየርን ትናንት የመጀመሪያውን ሽንፈት ቢቀምስም በደረጃ ሠንጠረዡ ግን አሁንም አንደኛ ነው። 54 ነጥብ ይዞ በኹለተኛነት ከሚከተለው ቮልስፍስቡርግ በ10 ነጥብ ልቆ ይገኛል። ቮልፍስቡርግ ትናንት ከማይንትስ ጋር አንድ እኩል በመለያየት ነጥብ መጋራት ችሏል። ከትናንት በስትያ በርካታ ጨዋታዎች የተከናወኑ ሲሆን፤ የባየር ሙይንሽን የቀድሞው ዋነና ተፎካካሪ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ሐኖቨርን 3 ለ2 ማሸነፍ ችሏል።

ዶርትሙንድ በ33 ነጥቡ 10 ደረጃ ላይ ይገኛል። ባየር ሙይንሽን ትናንት አሸንፎ ያገኘው ሦስት ነጥብ ተደምሮለት ሞይንሽንግላድባኅ 47 ነጥብ ይዞ በደረጃ ሠንጠረዡ ሦስተኛ ነው። ሻልከን ቅዳሜ ዕለት 1 ለዜሮ የረታው ባየር ሌቨርኩሰን በ45 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሽቱትጋርት በ23 ነጥብ የመጨረሻው 18ኛ ደረጃ የሙጥኝ ብሏል።

የቸልሲው ዲዬጎ ኮስታ

የቸልሲው ዲዬጎ ኮስታ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቸልሲ አሁንም በ67 ነጥብ መሪነቱን እንዳስጠበቀ ነው። ትናንት ሑል ሲቲን ሦስት ለ2 ሲያሸንፍ የመጀመሪያዋን ግብ በ2ኛው ደቂቃ ላይ ለቸልሲ ያስቆጠረው ኤደን ሐዛርድ ነው። ከዚያም በ9ኛውደቂቃ ላይ ዲዬጎ ኮስታ 2ኛዋን በ77ኛው ደቂቃ ሎይች ሬሚ ሦስተናዋን ግብ አስቆጥረዋል። ለሁልሲቲ አህመድ ሙሐማዲ እና አቤል ሔርናንዴዝ በ26ኛው እና 28ኛው ደቂቃ ላይ ለማስቆጠር ችለዋል።

ሊቨርፑል እና ማንቸስተር ዩናይትድ ትናንት ባደረጉት ፍልሚያ ሊቨርፑል የቁርጥ ቀን ልጁ ሽቴፋን ጄራርድ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተሰናበተበት ሲሆን፤ የ2 ለ1 ሽንፈትን ቀምሷል። ሽቴፋን ጄራርድ በ46ኛው ደቂቃ ላይ ከሜዳ የተሰናበተው አንደር ሄሬራን እግር በመርገጥ ግልጽ ስህተት በመፈፀሙ ነበር።

የማንቸስተር ዩናይትዱ ጁዋን ማታ በ14ኛው እና በ59ኛው ደቂቃዎች ላይ ኹለት ግቦችን ማስቆጠ ችሏል። በተለይ አየር ላይ በመንሣፈፍ አክሮባት ሠርቶ ያስቆጠራት ኹለተኛውን ግብ ድንቅ ሆና ተመዝግባለች። ለሊቨርፑል ብቸኛዋን ግብ በ69ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ጠባቂው ባጠበበት እና ተከላካይ በነበረበት አቅጣጫ ከበስተቀኝ በኩል በፈጣን ውሳኔ ከመረብ ያሳረፈው ዳንኤል ስቱሪጅ ነው።

በቀይ ካርድ የተሰናበተው ሽቴቨን ጄራርድ

በቀይ ካርድ የተሰናበተው ሽቴቨን ጄራርድ

ቅዳሜ ዕለት ማንቸስተር ሲቲ ዌስት ብሮሚችን 3 ለ ባዶ በማሸነፍ በደረጃ ሠንጠረዡ በኹለተኛነት ይገኛል። 61 ነጥብ አለው መሪው ቸልሲ 67 ነጥብ ሰብስቧል። ኒውካስልን 2 ለ1 ያሸነፈው አርሰናል ደረጃው ሦስተኛ ነው፤ ነጥቡ 60። ማንቸስተር ዩናይትድ በ59 ነጥብ 4ኛ ደረጃን ተቆናጧል፤ ትናንት እጅ የሰጠው ሊቨርፑል በ54 ነጥብ ከስሩ በ5ኛነት ይገኛል። 19 ነጥብ ያለው ላይስተር 20ኛ ደረጃ የመጨረሻውን ጠርዝ ይዟል።

በስፔን ላሊጋ ባርሴሎና ተቀናቃኙ ሪያል ማድሪድን ትናንት 2 ለ1 መርታት ችሏል። ማርሴሎ ከግራ ክንፍ በፍጥነት ወደ መሀል እየገፋ ያመጣትን ኳስ ለቤንዜማ በማቀበል ቤንዜማ በቀጥታ የክሪስቲያኖ ሮናልዶ ቀኝ እግር ላይ ያሳረፋት ኳስ የግቡን ማዕዘን ገጭታ የወጣችው በ12ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። የማርሴሎ ኳስ አያያዝ እና ቅልጥፍና የቤንዜማ ኳሷን መጥኖ መላክ እጅግ የሚደነቅ ነው። ወዲያውኑ ግን ባርሴሎናዎች የመልሶ ማጥቃት በማድረጋቸው ኔይማር ላይ ጥፋት ይሠራል። ቅጣት ምቱን ከበስተግራ በኩል ሊዮኔል ሜሲ በመምታት በቀጥታ የላካትን ኳስ ጄሬሚ ማቲው በጭንቅላት በመግጨት ለባርሴሎና በ19ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያውን ግብ አስቆጥሯል።

ጋሬት ቤይል በባርሴሎና ተጨዋቾች መሀከል

ጋሬት ቤይል በባርሴሎና ተጨዋቾች መሀከል

30ኛው ደቂቃ ላይ ኔይማር ከግብ ጠባቂው ፊት ለፊት ያገኛት ኳስ ለባርሴሎና ግብ ልትሆን ትችል ነበር። ብዙም አልቆየ በ30 ሠከንድ ልዩነት የሪያል ማድሪዶቹ ጋሬት ቤይል፣ ሉካ ሞድሪች እና ቤንዜማ ተቀባብለው ቤንዜማ በተረከዙ አመቻችቶ የላካትን ኳስ ሮናልዶ ከመረብ አሳርፏታል። የሮናልዶ እና የቤንዜማ ጨዋታ መናበብ እጅግ ድንቅ ነበር። በዓለም ዋንጫ ወቅት የጣሊያኑ ተከላካይ ጂዮርጂዮ ቺሊኒን በመንከሱ ለአራት ወራት ለቡድኑ እንዳይጫወት የታገደው ሉዊስ ሱዋሬዝ በ55ኛው ደቂቃ ላይ ከመሀል ሜዳ የተመታለትን ኳስ ከኹለት ተከላካዮች መሀል ፈጥኖ በመውጣት ከመረብ በማሳረፍ ኹለተኛዋን ግብ አስቆጥሯል። በ39ኛው ደቂቃ የሪያል ማድሪዱ ጋሬት ቤይል ያስቆጠረው ግብ ከጨዋታ ውጪ ተብሎ ተሽሮበታል። የተቀረፀው በዝግታ በተደጋጋሚ ሲታይ ግን ከጨዋታ ውጪ አልነበረም።

ባርሴሎና የትናንቱ በሪያል ማድሪድ ላይ የተቀዳጀው የ2 ለ1 ድል ተደምሮ በደረጃ ሠንጠረዡ 68 ነጥብ ይዞ አንደኛ ነው። ሪያል ማድሪድ 64 ነጥብ አለው ኹለተኛ ነው። ቫሌንሺያ በ60 ነጥብ ደረጃው ሦስተኛ ነው።

አጫጭር የስፖርት ዜናዎች

የዓለም ቁጥር 1 የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ኖቫክ ጆኮቪች

የዓለም ቁጥር 1 የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ኖቫክ ጆኮቪች

በሜዳ ቴኒስ ባለሙያዎች ማኅበር ፉክክር ሠርቢያዊው ኖቫክ ጆኮቪች በነጥብ አንደኛ ሆኖ በመምራት ላይ ይገኛል። የዓለማችን ኹለተኛው ምርጥ የሜዳ ቴኒስ ተጫዋች ስዊዘርላንዳዊው ሮጀር ፌደረርን ትናንት የህንድ ዌልስ ውድድር ላይ ገጥሞ በማሸነፍ የሰበሰበው ነጥብ ተደምሮለት እስካሁን ኖቫክ 13 ነጥብ አለው። ሮጀር ፌዴሬር በ9 ነጥብ ኹለተኛ ነው። የስፔኑ ራፋኤል ናድል በ5 ነጥብ ይከተላል። አሸናፊው በስተመጨረሻ በሚሊዮናት የሚቆጠር ዶላር ተሸላሚ ይኾናል።

በጉዳት ትናንት ከሜዳ ተቀይሮ የወጣው የባየር ሙይንሽኑ የክንፍ ተጫዋች አርየን ሮበን ሀገሩ ኔዘርላንድ ለአውሮጳ ዋንጫ ማጣሪያ እሁድ ከቱርክ ጋር ለምታደርገው ጨዋታ እንደማይሰለፍ ተነገረ። አሪየን ሮበን ትናንት የሆዱ ጡንቻ ላይ ባጋጠመው ኅመም ተቀይሮ መውጣቱ ይታወሳል።

በሌላ ዜና የዓለማችን ምርጥ ግብ ጠባቂ ጀርመናዊው ማኑዌል ኖየር ጀርመን ለአውሮጳ ዋንጫ ማጣሪያ ረቡዕ ከአውስትራሊያ ጋር ለምታደርገው ጨዋታ እንደማይሰለፍ ተነገረ። ግብ ጠባቂው ዛሬ ከሠዓት ወደ ፍራንክፉርት አየር ማረፊያ መምጣት ሲገባው መሄድ የሚችለው ማታ ላይ መሆኑን በመግለጹ ነው ሳይካተት የቀረው ተብሏል። ትናንት ቡድኑ ባየር ሙይንሽን በሞይንሽንግላድባኅ ኹለት ለባዶ ተሸንፏል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic