የስፖርት ዘገባ፤ መስከረም 3 ቀን፣ 2008 ዓ.ም | ስፖርት | DW | 14.09.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ፤ መስከረም 3 ቀን፣ 2008 ዓ.ም

ቸልሲ እና ሊቨርፑል በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ዳግም ሽንፈት ተከናንበዋል። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ግስጋሴውን ተያይዞታል። አሜሪካዊው ቡጢኛ ፍሎይድ ሜይዌዘር በተከታታይ አንድም ጊዜ ሳይሸነፍ 49ኛ ግጥሚያውን በድል አጠናቋል። በዳያመንድ ሊግ ውድድር የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድልን የአትሌቲክስ ስፖርት ጋዜጠኛ ትንታኔ ይሰጥበታል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:57
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
09:57 ደቂቃ

የስፖርት ዘገባ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የሳምንቱ መጨረሻ ውድድሮች ቸልሲ እና ሊቨርፑል ከባድ ሽንፈት ደርሶባቸዋል። ቸልሲ በኤቨርተን 3 ለ1 ሲቀጣ፤ ሊቨርፑል በማንቸስተር ዩናይትድ በተመሳሳይ 3 ለ1 ኩም ብሏል። አርሰናል ስቶክ ሲቲን 2 ለ0 ሸኝቶ 3 ነጥቡን በማስተማመኑ 10 ነጥብ ይዞ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ በግብ ብቻ ተበልጦ በነጥብ መስተካከል ችሏል። ማንቸስተር ሲቲ ከግስጋሴው የሚገታው አልተገኘኘም። ክሪስታል ፓላስን 1 ለባዶ ሸኝቶ ነጥቡን 15 አድርሷል። ኖርዊች በርንማውስን 3 ለ1፣ ዋትፎርድ ስዋንሲን 1 ለምንም አሸንፈዋል። ዌስት ብሮሚች ከሳውዝ ሐምፕተን ያለምንም ግብ ተለያይቷል። 11 ነጥብ ይዞ ከማንቸስተር ሲቲ ስር የሚገኘው ላይስተር ሲቲ ትናንት አስቶን ቪላን 3 ለ2 ሲረታ፤ ሰንደርላንድ በቶትንሀም 1 ለባዶ ተሸንፏል። ዛሬ ዌስትሐም ከኒውካስትል ይጋጠማሉ። የቅዳሜው የቸልሲ እና አርሰናል ግጥሚያ ይጠበቃል።

የቸልሲ እና የአርሰናል ግጥሚያ ይጠበቃል

የቸልሲ እና የአርሰናል ግጥሚያ ይጠበቃልየማንቸስተር ዩናይትዱ አምበል ዋይኔ ሩኒ ቡድኑ ለሻምፒዮንስ ሊግ ከፒ ኤስ ቪ አይንድሆቨን ጋር ማክሰኞ ለሚያደርገው ግጥሚያ እንደማይሰለፍ ተገለጠ። ዋይኔ ሩኒ በልምምድ ወቅት በደረሰበት ጉዳት ቅዳሜ እለት ማንቸስተር ዩናይትድ ሊቨርፑልን 3 ለ1 በረታበት ጨዋታ ሳይሰለፍ ቀርቷል። የማንቸስተር ዩናይትድ አሠልጣኝ ሉዊስቫን ጋል ዋይኔ ሩኒ ለሻፕምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ መሰለፍ ባይችልም፤ ከሳውዝሐምፕተን ጋር ለሚኖረው የእሁዱ ጨዋታ ግን ብቁ ይኾናል ብለው እንደሚገምቱ ተናግረዋል።

በተያያዘ ዜና የማንቸስተር ሲቲው ሠርጂዮ አጉዌሩ በጉልበቱ ላይ በደረሰበት አደጋ ለሻምፒዮንስ ሊግ እንደማይሰለፍ ተገልጧል። ማንቸስተር ሲቲ ጁቬንቱስን የሚገጥመው ማክሰኞ ነው። የሻምፒዮንስ ሊግ የየምድቡ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች የሚከናወኑት ማክሰኞ እና ረቡዕ እለት ነው። ማንቸስተር ዩናይትድ ከአንድ አመት ቆይታ በኋላ ወደ አውሮጳ መድረክ ብቅ ማለት ችሏል። የስፔን ላሊጋ ተቀናቃኞቹ ሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎናም ፉክክሩን ያደምቁታል ተብሎ ይጠበቃል።

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ትናንት ሆፈንሃይም በቬርደር ብሬመን 3 ለ1 ተቀጥቷል። ሻልከ ማይንትስን 2 ለ1 አሸንፏል። ዘንድሮ ወደ ቡንደስሊጋው መግባት የቻለው ኢንጎልስታድት በቡንደስ ሊጋው ልምድ ያለው አውስቡርግን ቅዳሜ እለት ተቋቁሞ ያለምንም ግብ በመለያያት ነጥብ ተጋርቷል። ሌላኛው ዘንድሮ ወደ ቡንደስሊጋው ያደገው ዳርምሽታድት ባየር ሌቨርኩሰንን 1 ለዜሮ ጉድ አድርጎታል። ባየር ሙይንሽን አውስቡርግን 2 ለ1 አሸንፏል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ሐኖቨርን 4 ለ2 በሆነ ሰፊ ልዩነት በመርታት ግስጋሴውን ቀጥሏል። በደረጃ ሰንጠረዡ ከባየር ሙይንሽን እኩል 12 ነጥብ በግብ ክፍያ ግን አንደኛ መሆን ችሏል። ሔርታ ቤርሊን ሽቱትጋርትን 2 ለ1 ማሸነፍ ችሏል። ኮሎኝ በአይንትራኅት ፍራንክፉርት 6 ለ2 ከባድ ቅጣት ደርሶበታል።

አትሌት ገንዘቤ ዲባባ

አትሌት ገንዘቤ ዲባባአትሌቲክስ

የአለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር በጎርጎሪዮስ አቆጣጠር 2015 በአለም አቀፍ መድረክ እና በዳያመንድ ሊግ አሸናፊ ለሆኑ አትሌቶች ክፍያ በአጠቃላይ 15,2 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ማድረጉ ተሰማ። ኢትዮጵያዊው አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻም በወንዶች የዳያመንድ ሊግ አጠቃላይ ውጤት አሸናፊ ለመሆን ችሏል። የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር የኢትዮጵያ ዘጋቢ ኤልሻዳይ ነጋሽ ስለ ዳያመንድ ሊግ ውድድር ምንነት ያብራራል።

አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ በዚህ የዳያመንድ ሊግ ውድድር አሸናፊ በመሆኑም የ40 ሺህ ዶላር ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል። በብራስልሱ የ5 ሺህ ሜትር ተፎካካሪው የነበረው የብሪታንያው ሞ ፋራህ በፍፃሜው ውድድር አልተሳተፈም። ጋዜጠኛ ኤልሻዳይ ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያውያት አትሌቶች በዳያመንድ ሊግ ወደፊት የበለጠ ውጤት ያስመዘግባሉ የሚል እምነት አለው።

በሴቶች የዳያመንድ ሊግ ውድድር ደግሞ ቀደም ሲል አትሌት ገንዘቤ ዲባባ የ3 ሺህ ሜትር አሸናፊነቷን አረጋግጣለች። ዘንድሮ በዳያመንድ ሊግ አሸናፊ የሆኑት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በቅርቡ በተጠናቀቀው የቻይና ቤጂንግ አለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር ተሳታፊ ነበሩ።

ጋዜጠኛ ኤልሻዳይ በአትሌቲክሱ ዘርፍ ተተኪ አትሌቶችን ማፍራቱ ላይ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት እንደሚገባ አስገንዝቧል።ተተኪ ተብለው የተገመቱ አትሌቶች በተለይ በዓለም አቀፍ የአትሌቲክ ሻምፒዮን ውድድር ለምን ውጤት አላስመዘገቡም የሚለውን አቢይ ጥያቄ አንስቶ መመርመር ያሻል ሲልም አክሏል።

የሜዳ ቴኒስ
የዓለማችን ቁጥር አንድ የሜዳ ቴኒስ ስፖርተኛ ኖቫክ ጆኮቪች ሮጀር ፌዴሬርን 6-4 5-7 6-4 6-4 በሆነ ውጤት ድል በማድረግ የዓመቱን ውድድሮች ኒውዮርክ ውስጥ አጠናቋል።

ቡጢ

አሜሪካዊው ቡጢኛ ፍሎይድ ሜይዌዘር

አሜሪካዊው ቡጢኛ ፍሎይድ ሜይዌዘር

አሜሪካዊው ፍሎይድ ሜይዌዘር በተከታታይ አንድም ሳይሸነፍ 49ኛ ውድድሩን በሳምንቱ መገባደጃ ላስ ቬጋስ ውስጥ በድል አጠናቋል። የፍሎይድ ሜይዌዘር 49ኛ ተሸናፊ አንድሬ በርቶ ነበር። ፍሎይድ ሜይዌዘር ባለፈው ግንቦት ወር በዓለም የቡጢ ታሪክ ከፍተኛ ገቢ ባስገኘው ግጥሚያ ሜኒ ፔኪያን ካሸነፈ ወዲህ ቅዳሜ እለት ወደ መድረክ ብቅ ሲል ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር። የ38 ዓመቱ ቡጢኛ ፍሎይድ ሜይዌዘር 49ኛ ውድድሩን ሦስቱ ዳኞች 120-108፣ 118-110 እና 117-111.በሰጡት ነጥብ በድል በማጠናቀቁ ከእዚህ ቀደም በሮኪ ማርቺያኖ ተይዞ የነበረው ክብርወሰን ላይ መድረስ ችሏል። ሮኪ 49 ውድድሮችን ሳይሸነፍ በተከታታይ ድል ያደረገ ቡጢኛ ነው።

አሁን ሜይዌዘር ተስተካክሎታል። ምናልባት ለ50ኛ ውድድሩ አስቦበት እንደሆነ ተጠይቆ ሜይዌዘር ሲመልስ «ከእንግዲህ በቃኝ፤ ይኽ ይፋዊ ስንብት ነው።» በማለት መቧቀሻውን መስቀሉን አስታውቋል። ራሱን ከቡጢ ውድድር አለም ባያሰናብት ኖሮ የሚጋጠመው ግንቦት ወር ላይ ካሸነፈው ሜኒ ፔኪያን ጋር ነበር። «መቧቀሻህን መቼ መስቀል እንዳለብህ ማወቅ ይገባሀል። 40 አመት እየተጠጋሁ ነው። በቡጢው አለም ከእንግዲህ የማረጋግጠው የቀረኝ አንዳችም ነገር የለም። አኹን የምፈልገው ከቤተሰቦቼ ጋር ማሳለፍ ነው» ሲል አክሏል። ፍሎይድ ሜይዌዘር በቡጢ ፍልሚያው 34 ሚሊዮን ዶላር ማፈስ ችሏል። በእርግጥ ከእንግዲህ ከቡጢው አለም ተሰናብቶ 50ኛ ውድድሩን እንደማያደርግ ብዙዎች ይጠራጠራሉ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂቱት መለሰ

Audios and videos on the topic