የስፖርት ዘገባ፤ ሐምሌ 20 ቀን፣ 2007 ዓ.ም. | ስፖርት | DW | 27.07.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ፤ ሐምሌ 20 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ማጣሪያ ጨዋታ ከደካማዋ ሳዎቶሜና ፕሪንሲፕ ጋር ተደልድሏል። ያን ካለፈ ጠንካራው የኮንጎ ሪፐብሊክ ቡድን ይጠብቀዋል። የስፖርት ጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ ለሳዎቶሜም ቢሆን መዘናጋት የለብንም ብሏል። በቱር ደፍሯንስ የብስክሌት ሽቅድምድም ፍፃሜ ክሪስ ፍሮሜ ለሁለተኛ ጊዜ አሸናፊ ሆኗል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:28
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:28 ደቂቃ

የስፖርት ዘገባ፤ ሐምሌ 20 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.

ኢትዮጵያ ከሦስት ዓመታት በኋላ ሩስያ በምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ውድድር ለመሳተፍ ለማጣሪያው ከማን ጋር እንደምትጫወት ድልድሉ ይፋ ሆኗል። ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የዙር ውድድር ኢትዮጵያ ከንዑሷ ሳዎቶሜ እና ፕሪንሲፕ ጋር ተደለደለች። ሳዎቶሜን ካሸነፈች ወደ ማጣሪያው ለመግባት ጠንካራውን የኮንጎ ሪፐብሊክ ቡድን ገጥማ ማሸነፍ ይጠበቅባታል። ከዚያም ከሌሎች 19 አሸናፊዎች ጋር በመሆን እያንዳንዱ አራት ሃገራት ያሉበት አምስት ቡድን ይደለደላል። ከየምድቦቹ ከፍተኛ ነጥብ ያገኘ ቡድን በቀጥታ ለዓለም ዋንጫ ያልፋል ማለት ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ሁለቱን ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎቹን አልፎ ወደ ሦስተኛው የመጨረሻው የምድብ ማጣሪያ ለመግባት አሁን ያለበት አቋም ምን ይመስላል? መንሱር አብዱልቀኒ በብሥራት በFM 101.1 ብስራት ስፖርት የሬዲዮ ሥርጭት ዋና አዘጋጅ ለሳዎቶሜ እና ፕሪንሲፔም ቢሆን መዘናጋት አይገባንም ብሏል።

እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2018 ለሚኪያሄደው የዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ዙር የማጣሪያ ውድድር ጎረቤት ጅቡቲ ከስዋዚላንድ ጋር ስትደለደል፤ ኤርትራ ቦትስዋናን ትገጥማለች። ሶማሊያ ኒጀርን፣ ደቡብ ሱዳን ሞሪታንያን እንዲሁም ጎረቤት ኬንያ ሞሪሺየስን ይገጥማሉ። ከጎረቤት ሃገራት መካከል በቀጥታ ሁለተኛው ዙር ማጣሪያ ውስጥ የተደለደለችው ብቸኛ ሀገር ሱዳን ናት፤ ከዛምቢያ ጋር ትፋለማለች።

አትሌቲክስ

ለንደን ውስጥ በተከናወነው የአትሌቲክስ ውድድር የቅዳሜ ዕለት ውጤት መሰረት፤ በ5000 ሜትር የሩጫ ፉክክር ኬንያውያን እና አሜሪካውያን የበላይ ሆነዋል። ኢትዮጵያዊቷ ሯጭ ሐፍታምነሽ ተስፋይ በአምስተኛነት ባጠናቀቀችበት ውድድር፤ ኬኒያዊቷ ሜሪ ቼሮኑ በ14:54.81 በመግባት አንደኛ ወጥታለች። የዩናይትድ ስቴትሷ ሞሊ ሀድል ሁለተኛ ስትሆን፤ ሦስተኛ ደረጃ ያገኘችው ኬንያዊቷ ጃኔት ኪሳ ናት። ማሪል ሐል የተባለችው ሌላኛዋ አሜሪካዊት አራተኛ ደረጃን አግኝታለች።

ብስክሌት

የቱር ደ ፍሯንስ የብስክሌት ሽቅድምድምን የብሪታንያው ብስክሌተኛ ክሪስ ፍሮሜ ትናንት ፓሪስ ከተማ ውስጥ ማሸነፍ ችሏል። ክሪስ በብስክሌት የውድድር ዘመኑ ትናንት በፍፃሜ ድሉ ያስመዘገበው ውጤት ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። ስካይ ለተሰኘው ቡድን የተሰለፈው ክሪስ የትናንትናውን የፍፃሜ ሽቅድምድም ሲያጠናቅቅ አጠቃላይ ውጤቱ በ1 ደቂቃ ከ12 ሰከንድ የላቀ መሆኑም ታውቋል። የ30 ዓመቱ ብሪታንያዊ በ102ኛው የቱር ደ ፍሯንስ ሽቅድምድም ያስመዘገበው ውጤት የተገኘው የተከለከለ የኃይል ሰጪ መድሐኒት ተጠቅሞ ነው በሚል ጭምጭምታ ጥላ አጥልቶበት ነበር። ሆኖም ብስክሌተኛው ከአላስፈላጊ ድርጊቶች የጸዳ መሆኑ ተገጋግጧል ተብሏል።

ለደቡብ አፍሪቃው MTNQhubeka የተሰለፈው የኤርትራው ብስክሌተና ዳንኤል ተ/ሃይማኖት ከ160 ብስክሌተኞች 49ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። ቅዱስ መሐሪ በአጠቃላዩ ነጥብ 84ኛ ወጥቷል።

የመኪና ሽቅድምድም

በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የሐንጋሪ ውድድር ጀርመናዊው ሰባስቲያን ፌትል በፌራሪ ተሽከርካሪው አንደኛ ወጥቷል። የሩስያው አሽከርካሪ ዳኒል ክቪያት በሁለተኛነት አጠናቋል። ሌላኛው የሬድ ቡል አሽከርካሪ የአውስትራሊያው ዳንኤል ሪካርዶ ሦስተኛ ሆኖ ጨርሷል።

አጫጭር የስፖርት ዜና

ወደ ቬትናም አቅንቶ ዛሬ ከቬትናም ምርጥ ጋር የተጫወተው ማንቸስተር ሲቲ ቬትናምን 8 ለ1 አሸንፏል።

የባየር ሙይንሽኑ አሠልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ በሚቀጥለው የውድድር ዘመን ወደ እንግሊዝ አቅንተው የማንቸስተር ሲቲ አሠልጣኝ ለመሆን መስማማታቸውም ተሰምቷል።

የማንቸስተር ዩናይትዱ አሠልጣኝ ሉዊስ ቫን ጋል ለባለቤታቸው ሲሉ ከ2 ዓመት በኋላ ከማንቸስተር አሠልጣኝነት በገዛ ፈቃዳቸው እንደሚነሱ ተናግረዋል። ሌላ ቡድን የማሠልጠን ዕቅድ እንደሌላቸው ይልቁንም ጊዜያቸውን ለባለቤታቸው ማድረግ እንደሚፈልጉ ጠቅሰዋል። ቫን ጋል ከአንድ ሳምንት በኋላ 64 ዓመታቸውን ይደፍናሉ። በ2 ዓመት የማንቸስተር የወደፊት ቆይታቸው ለቡድናቸው ተደጋጋሚ ድል ለማስመዝገብ መቁረጣቸውንም አስታውቀዋል።

አሰልጣኙ የ28 ዓመቱ የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ሠርጂዮ ሮሜሮን ወደ ቡድናቸው ማስመጣት ችለዋል። ሠርጂዮ ከዚህ ቀደምም በሉዊስ ቫንጋል ስር ሆኖ የሠለጠነ ሲሆን፤ በማንቸስተር ዩናይትድ ለሦስት ዓመታት ሊያስቆየው የሚችለውን ውል እንደፈረመ ተገልጧል። ምናልባትም ውሎ አራት ዓመት ድረስ ሊዘልቅ እንደሚችል ተጠቅሷል።

ሠርጂዮ ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ ሲመጣ ዲ ማሪያ ከማንቸስተር ዩናይትድ ወደ ፓሪስ ሰንጃርሜይን ቡድን የመዘዋወሩ ነገር እየተጠናቀቀ መሆንን የፈረንሣዩ ቡድን አሠልጣኝ ሎሬን ብላክ ይፋ አድርገዋል። አሠልጣኝ ቫን ጋል እንደ ሮናልዶ ያለ ልዩ ችሎታ እና ፍጥነት ያለው ተጨዋች እንደሚያስፈልጋቸው ገልጠዋል።

የሪያል ማድሪዱ ኮከብ ክሪስቲያኖ ሮናልዶን የፈረንሣዩ ፓሪስ ሰንጀርሜን ቡድን በ132 ሚሊዮን ዶላር ለማስመጣት ጠየቀ መባሉን ቡድኑ ዛሬ ማስተባበሉን ዴይሊ ሚረር የተባለው ዕለታዊ ጋዜጣ ዘግቧል።

ለዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ቡድኖች የወዳጅነት ጨዋታ የስፔኑ ኃያል ሪያል ማድሪድ የጣሊያኑ ኢንተር ሚላንን ዛሬ ቻይና ጉዋንጁ ውስጥ ገጥሞ 3 ለ0 አሸንፏል። ግቦቹን ለሪያል ማድሪድ በ29ኛው ደቂቃ ጄሴ፣ በ55ኛው ቫራኔ እንዲሁም በ88ኛው ደቂቃ ላይ ሮድሪጌዝ አስቆጥረዋል።

የሰሜን እና የመካከለኛው አሜሪካ እንዲሁም የካሪቢክ ሃገራት በሚሳተፉበት የ«Gold Cup» የእግር ኳስ ፍልሚያሜክሲኮ ጃማይካን 3 ለ0 አሸንፋለች። ጃማይካ በውድድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ የገባች የካሪቢክ ቡድን ስትሆን ሜክሲኮ ይኽን ዋንጫ ስትወስድ ለ7ኛ ጊዜነው።

የአርሰናሉ አጥቂ ቲዎ ዋልኮት አዲስ ውል ሊፈርም መቃረቡን አሠልጣኝ አርሰን ቬንገር ይፋ አድርገዋል። የ26 ዓመቱ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊ ቴዎ ዋልኮት ውሉ ሊያከትም አንድ ዓመት ብቻ ነው የሚቀረው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic