የስፖርት ዘገባ፤ ሐምሌ 13 ቀን፣ 2007 ዓ.ም. | ስፖርት | DW | 20.07.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ፤ ሐምሌ 13 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.

በዛሬው ሳምንታዊው የስፖርት ዘገባ በተለይ የምናተኩረው ጀርመን ፍራንክፉርት ከተማ ውስጥ ስለተከናወነው «13ኛው በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን ስፖርት እና ባሕል ፌስቲቫል» ነው። ባሳለፍነው ሳምንት ረቡዕ ጀምሮ ቅዳሜ የተጠናቀቀው» በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን ስፖርት እና ባሕል ድግስ ደማቅ በሆነ መልኩ ተጠናቋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:43
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
11:43 ደቂቃ

የስፖርት ዘገባ፤ ሐምሌ 13 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.

«13ኛው በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን ስፖርት እና ባህል ፌስቲቫል» ባሳለፍነው ሳምንት ረቡዕ ጀምሮ ቅዳሜ ዕለት ተጠናቋል። እጅግ ደማቅ በሆነው ስፖርታዊ ውድድር እስከ አምስት ሺህ የሚደርሱ ታዳሚያን መሳተፋቸው ተገልጧል። የ7 ዓመቱ ናታን ቢንግ የኢትዮ ስዊስ ቡድን አጥቂ ነው። ፍራንክፉርት ውስጥ በተከናወነው ውድድር ሲሳተፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ሌላኛው ተወዳዳሪ ደግሞ ቅዱስ አክሊለ ይባላል እድሜያቸው ከ11 እስከ 14 የሆኑ አዳጊዎች በሚጫወቱበት ውድድር ላይ ኢትዮ ስዊስን ወክሎ ነው የተጫወተው።

የእነቅዱስ ቡድን ኢትዮ ስዊስ ለፍፃሜ ደርሶ በኢትዮ ዙሪክ 4 ለ1 ተሸንፏል። እነቅዱስ ግን ሁለተኛ በመውጣታቸው ደስተኛ ሆነው ለሚቀጥለው ውድድር ጠንክረው መምጣታቸው አይቀርም። የህፃናቱን እና የታዳጊዎችቹን ውድድር በክብር እንግድነት በመጋበዝ የከፈተው የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የረዥም ጊዜ ግብ ጠባቂ እና የቡና ቡድን ተሰላፊው በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂዎች አሠልጣን ዓሊ ረዲ ነበር።

የነዓሊ ቡድን ኢትዮ አበበ ቢቂላ በሁለተኛ ዲቪዝዮን የአዋቂዎች የፍፃሜ ውድድር በኢትዮ ኤሚሊያ ቢሸነፍም ሁለቱም ቡድኖች ለሚቀጥለው ዓመት ውድድር ወደ አንደኛ ዲቪዚዮን አልፈዋል። የውድድሩ አስተባባሪ አቶ ከበደ ኃይሌ

በአዋቂዎች በተደረው ውድድር ለፍፃሙ የደረሰው ኢትዮ ለንደን ቡድን ነበር። መጀመሪያ ላይ በኢትዮ ኖርዌይ 1 ለባዶ ሲመራ ቆይቶ የማታ ማታ ከመረብ ባስቆጠራት አንድ ግብ አቻ ለመውጣት ችሏል። በፍፁም ቅጣት ምቱም ኢትዮ ለንደን ኢትዮ ኖርዌይን 6 ለ5 አሸንፏል።

በዚህ ደማቅ የስፖርት ውድድር ሊታደሙ ከተለያዩ የአውሮጳ ሃገራት፤ ከአሜሪካ እና ከመላው ዓለም በርካታ ሰዎች ተገኝተው ነበር። ነዋሪነቱ በአሜሪካን ሀገር የሆነው አቶ ያሬድ ይፍሩ በድግሱ በመገኘቱ ደስተኛእንደሆነ ግልጧል።

ፌዴሬሽኑ ለረዥም ጊዜ እያገለገሉ ከሚገኙ ሰዎች መካከል አቶ ግርማ ሳህሌ ዮሐንስ ይገኝበታል። የአውሮጳው ፌዴሬሽን ህዝብ ግንኙነት ናቸው። በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን የስፖርት እና የባሕል ድግስ ኢትዮጵያንን በአንድነት የሚያገናኝ መድረክ መሆኑን ተናግረዋል። ነዋሪነታቸው በለንደን የሆነው አቶ ዮሐንስ መሰለ በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን ስፖርት እና ባህል ፌዴሬሽን ሊቀመንበር ናቸው። የስፖርት እና ባህል ድግሱ በያመቱ መሻሻል እንዳሳየ ይናገራሉ። አቶ ዮሐንስ የሚኖሩበት የለንደን ከተማ ቡድን ኢትዮ ለንደን ዋንጫውን ይዞ ወደ ለንደን አቅንቷል።

ለኢትዮ ስዊስ የሚጫወተው ናታንም ምኞቱ እና ፍላጎቱ ተሳክቶለታል ቡድኑ ኢትዮ ስዊስ ከኢትዮ ጀርመን ጋር ያለምንም ግብ ተለያይቷል። ሆኖም በፍፁም ቅጣት ምት ኢትዮ ጀርመን 5 ለ4 ማሸነፍ ችሏል። ፓስፖርቱ እና ገንዘቡን የያዘው ቦርሳው የጠፋበት ዓሊ ረዲም ገንዘቡን ባያገኝም ፓስፖርቱን እና ሌሎች ሰነዶቹን ግን ማግኘት ችሏል። ውድድሩ ቢጠናቀቅም ፌዴሬሽኑ ባዘጋጀው የሙዚቃ ድግስ ታዋቂው ቴዎድሮስ ካሳሁን ምሽቱንታዳሚያንን እያዝናና የኢትዮጵያውያኑ የስፖርት እና ባህል ድግስ ተጠናቋል።

አትሌት ገንዘቤ ዲባባ በ1,500 ሜትር ርቀት የሩጫ ውድድር ለበርካታ ዓመታት ተከብሮ የቆየውን የዓለም ክብርወሰን ባሳለፍነው ሳምንት መገባደጃ ላይ ፈረንሳይ ሞናኮ ውስጥ መስበሯ በርካታ መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል። ገንዘቤ እንደ ጎርጎሪዮሳዊው አቆጣጠር በ1993 በቻይናይቱ ዩንሺያ ኩ ተይዞ የቆየውን ክብርወሰን ነው የሰበረችው።

ኮሎምቢያ ካሊ በተከናወነው የዓለም ወጣቶች ሻምፒዮን ውድድር ኢትዮጵያውያቱ በዳቱ ሒርጳ እና ሹሩ ቡሎ በ1500እና 3000ሜትር የሩጫ ውድድር ለኢትዮጵያ ወርቅ አስገኝተዋል።

የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማሕበራት ፌዴሬሽን በእንግሊዝኛ ምኅፃሩ FIFA ፕሬዚዳንት ሴፕ ብላተር በሚቀጥለው ሳምንት ማሌዢያ ውስጥ በሚከናወነው የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ እንደማይገኙ ታውቋል። ስብሰባው እንደ ጎርጎሪዮሳዊው አቆጣጠር በ2022የክረምት ኦሎምፒክ አዘጋጅ ከተማን ለመምረጥ የሚኪያሄድ ነው። ላለፉት 16 ዓመታት የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አባል የሆኑት ሴፕ ብላተር ዘንደሮ ባልተለመደ መልኩ በስብሰባው የማይገኙት ፊፋ ውስጥ ተከሰተ የተባለውን ዉስና ተከትሎ በቅርቡ በዩናይትድ ስቴትስ ምርመራ ከተጀመረባቸው ወዲህ ነው ሲሉ የዜና አውታሮች ዘግበዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic