የስድተኞች ቀዉስና ያስከተለዉ ወጭ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 04.02.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የስድተኞች ቀዉስና ያስከተለዉ ወጭ

ወደ ጀርመን የገቡ ስደተኞችን ለመርዳት እና ከማኅበረሰቡ ጋር ለማዋኃድ መንግሥት በያዝነዉ የጎርጎረሳዉያኑ 2016 እና 2017 ዓ,ም 50 ቢሊዮን ዩሮ ወጭ እንደሚያስፈልገዉ አንድ ጥናት አመለከተ። ጀርመን ያለባትን ይህን ከፍተኛ ወጭ በተመጣጠነ መልኩ ለመሸፈን ሃገሪቱ ካለባት የተለያዩ ወጭዉች ከፍተኛ ቁጠባ ማድረግ እንዳለባትም ተመልክቶአል።

የጀርመን መንግሥት ከዜጎቹ ከሚሰበሰበዉ ግብር በያዝነዉ የጎርጎረሳዉያኑ 2016 እና 2017 ዓ,ም ለስደተኞች መኖርያ፤ ምግብና ስልጠናን ለማሟላት 50 ቢሊዮን ዩሮ እንደሚያስፈልገዉ ኮለኝ ከተማ የሚገኘዉ የኤኮኖሚ ተቋም ያካሄደዉ አንድ ጥናት አመልክቶአል። ጥናቱ በተለያዩ ኮባንያዎችና የንግድ ማኅበራት መደገፉም ተጠቅሷል። በጥናቱ መሠረት በጀርመን

አንድ ስደተኛ ለመኖርያ ቤት፤ ምግብና፤ ጤና ጥበቃ፤ በዓመት የ 12 ሺህ ዩሮ ወጭን ይፈልጋል። ከዚህ በተጨማሪ እያንዳንዱ ስደተኛ ለቋንቋና ከማኅበረሰቡ እንዲዋኃድ ለሚሰጠዉ ትምህርት በዓመት 3,300 ዩሮ ወጭ ያስፈልገዋል። ያ ማለት አንድ ስደተኛ በዓመት በአጠቃላይ 15 ሺህ ይሮ ወጭ እንደሚጠይቅ ጥናቱ በዝርዝር አስቀምጦአል። በጀርመን የኤኮኖሚ ተቋም ዉስጥ ከጥናቱ አቅራቢ አንዱ የሆኑት ቶብያስ ሄንዘ እንደሚሉት፤ ለስደተኞች የሚወጣዉ ወጭ በኤኮኖሚዉ ላይ ትንሽም ቢሆን እገዛ ያደርጋል።

« መንግሥት የሚያመጣዉ በሙሉ ለሌላዉ የገቢ ምንጭ ነዉ። ለስደተኞች መጠለያ የሚሆኑ ቤቶች ለመሥራት፤ ቋንቋን ለማስተማርያ የገንዘብ ወጭ ሲደረግ ለኤኮኖሚዉ እድገት እገዛ ያደርጋል። ስለዚህ ለስደተኞች የሚዉለዉ ርዳታ በጥቅሉ ሲታይ አንድ ትንሽ የኤኮኖሚ መርሃ -ግብር በመሆኑ በያዝነዉ 2016 ዓ,ም በትንሹ የኤኮኖሚ እድገትን ያስገኛል»

በመንግሥት ወጭ ላይ ብቻ ትኩረቱን ያደረገዉ ይህ ጥናት ይፋ በሆነዉ የስደተኞች ቁጥር ላይ መመርኮዙም

Deutschland Wolfgang Schäuble Haushaltsdebatte

የጀርመኑ የፊናንስ ሚኒስትር ዎልፍጋንግ ሾይብለ

ተመልክቶአል። ባለፈዉ የጎርጎረሳዉያን 2015 ዓ,ም ወደ ጀርመን የገባዉ የስደተኛ ቁጥር 1.1 ሚሊዮን ሲሆን በዚህ በያዝነዉ የጎርጎረሳዉያኑ 2016 ዓ.ም ወደ 800 ሺህ ስደተኛ ጀርመን ይገባል ተብሎ ይጠበቃል። የኮለኝ የኤኮኖሚ ተቋም ይህን ቁጥር ተንተርሶ የዓመት አማካይ ስሌትን ማዉጣቱን አንዱ የጥናት አቅራቢ ቶብያዝ ሂንዘ ተናግረዋል።

« ሁለት ስደተኞች ሐምሌ አንድ ቀን ወደ ጀርመን ቢገቡ፤ በጠቅላላዉ በአማካይ ሲታይ ልክ አንድ ስደተኛ ሙሉዉን ዓመት እዚህ እንደኖረ ነዉ መታየት ያለበት።»

በዚህም መሰረት ጥናቱ በያዝነዉ የጎርጎረሳዉያኑ ዓመት 1.5ሚሊዮን ስደተኛ በመጭዉ የጎርጎረሳዉያኑ 2017 ደግሞ 2.2ሚሊዮን ስደተኛ ይገባል ሲል በአማኻኝ የያዘዉን ቁጥር ይፋ አድርጓል። ይህን ተከትሎ ምን ያህል ወጭ እንደሚያስፈልግ ጥናቱ በግልፅ አስቀምጧአል። በተጨማሪ ጥቂት ስደተኞች በሃገሪቱ የሥራ ፈቃድ የማግኘትና ሥራ የመቀጠር ቢሮክራሲን አልፈዉ ሥራ እንደሚያገኙም ጥናቱ ያመለክታል። እንደ ምሁራኑ ግምት በያዝነዉ የጎርጎረሳዉያን ዓመት 99 ሺህ በሚቀጥለዉ 2017 ዓ,ም 276 ሺህ ስደተኞች ከቋንቋና በሃገሪቱ ለመዋሃድ ከሚሰጥዉ ትምህርት ወጭዎች በስተቀር ከመንግሥት ድጋፍ እንደሚወጡ ያሳያል። እንድያም ቢሆን ይላሉ ቶብያዝ ሂንዘ በመቀጠል፤

« ስደተኞቹ ሥራ ሲያገኙ -እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚገባን ዝቅተኛዉን የደሞዝ ገደብ በሕግ ወስነናል-እና ግብርን እና ማኅበራዊ አስተዋጾዎችን ሲከፍሉ ገንዘቡ በሙሉ ወደ መንግሥት ኪስ ይገባል።»

ጥናቱ በማጠቃለያዉ ለስደተኞች ወጭ ለያዝነዉ የጎርጎረሳዉያኑ 2016 ዓ,ም 22.1 ቢሊዮን ይሮ በ 2017 ዓ,ም 27.6 ቢሊዮን ይሮ ባጠቃልይ ወደ 50 ቢሊዮን ይሮ እንደሚያስፈልግ ነዉ የተመለከተዉ።

የጀርመኑ የፊናንስ ሚኒስትር ዎልፍጋንግ ሾይብለ መንግሥታቸዉ ከግብር ያገኘዉ ገቢ ከቀዳሚዎቹ ዓመታት በ 12 ሚሊዮን

ይሮ ብልጫ እንዳለዉ ታህሳስ ወር ላይ ማሳወቃቸዉ ይታወሳል። ይህ ጥሩ ዜና የክፍለ ሃገራት ሚኒስትሮች ተጨማሪ ገንዘብ እንዲመደብላቸዉ የፊደራሉን መንግሥት ለመጠየቅ አነሳስቶአቸዋል። የኤኮኖሚ ጉዳይ ምሁሩ ሄንዘ ይህ ጥያቄ በቂ ምክንያት ነዉን? ሲሉ ይጠይቃሉ። እንደ ሄንዝ መንግሥት ያለምንም ብድር ስደተኞችን ለመርዳት አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ላይ ማተኮር ይገባዋል።

የፊደራል ክፍለ ሃገራት ባለስልጣናት በሌሎች መስኮች ያለባቸዉን የገንዘብ እጥረት ካላሳወቁ በቅርቡ ተጨማሪ ገንዘብን ለመበደር ይገደዳሉ ሲልም በኮለኝ የሚገኘዉ በስደተኞች ቀዉስና ወጭ ላይ ጥናቱን ይፋ ያደረገዉ የኤኮኖሚ ተቋም አስታዉቋል።

አንድርያስ ቤክ / አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሃመድ

Audios and videos on the topic