የስድስቱ ቀን ጦርነት 50ኛ ዓመት | ዓለም | DW | 05.06.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የስድስቱ ቀን ጦርነት 50ኛ ዓመት

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ሌቪ ኤሽኮልም ጦርነቱን አይፈልጉትም ነበር።የአሜሪካዉ ፕሬዝደንት ሊንደን ጆንሰንም ሆኑ የሶቬት ሕብረቱ መሪ ሊዮንድ ብሬዥኔቭ በዚያን ወቅት ጦርነት መለኮሶን አልፈለጉትም።ጦር እያደራጁ ጦርነት አንፈልግም፤ ተፋላሚዎችን እስካፍንጫቸዉ እያስታጠቁ ዉጊያ እንዳይጫር አሳሰቡ ብሎ ነገር በርግጥ ግራ አጋቢ ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 13:02

የስድስቱ ቀን ጦርነት 50ኛ ዓመት

ሰኔ 5 1967 ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ።ጄኔራል ሞርዴቺ ሆድ ሥለ-ሥንቅ-ትጥቅ፤ ሥለ ሥልት-ዝግጅት፤የሚያሰላስሉበት ምክንያት የለም።ጊዜም የለም።እሳቸዉ እና ብዙ ብጤዎቻቸዉ  ድፍን ሃያ-ዓመት በተግባር የኖሩ-ሚሊዮኖችን ያኖሩ፤ የተፈተኑ-የፈተኑበት ሐቅ የሚፈጋበት ዕለት ነዉ። የነደፉ፤የከለሱት ዕቅድ፤ ያሰለጠኑ፤ ያለማመዱት ወጣት ዉጤት የሚታይበት ዕለት።ሰኔ 5 1967።ጧት ነዉ።ግብፅ 2 ሰዓት ከአርባ አምስት።እስራኤል 1 ሰዓት ከ45።ቀጥል አይነት አሉ የእስራኤሉ አየር ኃይል አዛዥ። የማስጠንቂያዉ ደወል አጓራ።

                                   

የፈረንሳይ፤ የዩናይትድ ስቴትስና የብሪታንያ ምርጥ ጭንቅላቶች ያፈሯቸዉ  የዘመኑ ምርጥ አዉሮፕላኖች ተመነጠቁ።ቦምብ አዝንበዉ አስከሬን ሊያመርቱ።ከነፉም።መካከለኛዉ ምሥራቅ አዲስ ጦርነት።«የ67ቱ ጦርነት የጀመሪያዉ ቀን በጣም ከባዱ ነበር።»ዛሬ 50 ዓመቱ።አልበረደም።ላፍታ እንዘክረዉ።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፍልስጤም ይባል የነበረዉን ግዛት ለሁለት ገምሶ ባንደኛዉ ገሚስ አይሁድ ነፃ መንግሥት እንዲመሠርቱ የሚፈቅድ ዉሳኔ ከማስፅደቁ ከጥቂት ወራት በፊት የፅዮናዉን

ማሕበረተኞች ካይሮን ጎብኝተዉ ነበር።መስከረም 1967።ማሕበረተኞቹ ለአይሁዶች የመንግስትነት ጥያቄ ድጋፍ ለማሰባሰብ ያለመ በመሰለዉ ጉብኝታቸዉ በይፋ ካነጋገሯቸዉ የዚያ ዘመን ባለሥልጣናት አንዱ የአረብ ሊግ ዋና ፀኃፊ አብዱል ረሕማን አዛም ነበሩ።

«ለኔ» አሉ-አሉ አረቡ ዲፕሎማት ለፅዮናዉያኑ መልዕክተኞች «በተጨባጭ ያላችሁ እዉነት ትሆኑ ይሆናል፤ ለሠፊዉ አረብ ግን እናንተ በተጨባጭ የላችሁም። ጊዚያዊ ክስተት ናችሁ።» ቀጠሉ አረቡ።ታሪክም እየጠቀሱ «ከብዙ ምዕተ-ዓመታት በፊት የመስቀል ጦረኞች ከኛ ፍላጎት ዉጪ እመኻላችን ገቡ።ከሁለት መቶ አመታት በኋላ ነቀልናቸዉ።ይሕ የሆነዉ እነሱን እንደ ተጨባጭ እዉነት የመቀበል ስሕተት ሥላልሰራን ነዉ።»

አይሁድ በተቃራኒዉ ከሜድትራንያን ባሕር እስከ ዮርዳኖስ የሚገኘዉ ሰፊ ግዛት የአይሁድ ጥንታዊ ግዛት በመሆኑ አረቦች እዚያ ምድር ሊኖሩ አይገባም ባዮች ነበሩ።

የሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ድል አድራጊዎች የአይሁድ አረብን ሥር የሰደደ ተቃራኒ ሥነ-ልቡናዊ አስተሳሰብ ከማረቅ ይልቅ በሚዘዉሩት ድርጅት በኩል ፍልስጤም ይባል የነበረዉን ግዛት ለሁለት ገምሰዉ በአንደኛዉ ገሚስ የአይሁድ መንግስት እንዲመሠረት ወሰኑ።ሕዳር 1947።ዉሳኔዉ መንግሥት አልባዎቹ አይሁድ ነፃ መንግሥት እንዲመሠርቱ ሕጋዊ መብት ሰጥቷል።ጥንታዊ  ጥንታዊ ፍላጎታቸዉን፤ ሥነልቡናዊ እምነታቸዉን የሚያረካ ግን አይደለም።በእየሩሳሌሙ የሒብሩ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ፕሮፌሰር ሞሼ ሲመርማን እንደሚሉት ዉሳኔዉ ሁለት አይነት አስተሳሰብ እንዲያጎነቁል ያደረገ ነዉ።

                      

«ታላቅዋ ሳይሆን መላዋ እስራኤል የሚል አስተሳሰብ ነዉ ያለዉ።እስከ 1967 ድረስ በዮርዳኖስ እና በሜድትራኒያን ባሕር መካከል ያለዉን ሥፍራ መላዋ እስራኤል ብሎ የመጥራት ዝንባሌ ትልቅ  ሚና ነበረዉ።

በእስራኤል ማሕበረሰብ ዘንድ በቀኞችና በግራዎች፤በብሔረተኞችና በለዘብተኞች መካከል የሚደረግ ክርክር አለ።ብሔረተኞቹ መላዋ እስራኤል (እንድትመሠረት) ይፈልጋሉ።ግራዎቹና ለዘብተኞቹ በ1947ቱ  የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዉሳኔ የተደነገገዉን ይደግፋሉ።»

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በዩናይትድ ስቴትስና በብሪታንያ ግፊት እና ጫና ያሳለፈዉ ዉሳኔ ቁጥር 181 (II)  አረቦችን አስቆጥቶ፤ አይሁድን ቅር አሰኝቶ ወትሮም ባልበረደዉ ጦርነት ሙሉ በሙሉ እንዲዘፈቁ ያደረገዉም ለዚሕ ነዉ።

ጦርነቱን በድርድር እንዲያስቆሙ ድርጅቱ የሾማቸዉ ልዩ መልዕክተኛ ሲዊዲናዊዉ ዕዉቅ ዲፕሎማት ፎልከ ቤርናዶተ እየሩሳሌም ዉስጥ በፅንፈኛ የሁዲዎች መገደላቸዉ  የራሱ የድርጅቱም ሙያተኞች በቅጡ ይልተጤነዉ፤ የሕዝብን አስተሳሰብና እምነት ያላገናዘበዉ ዉሳኔ ሠለባ መሆናቸዉን አረጋጋጭ ነዉ።

ከዕዉቁ ዲፕሎማት መገደል በኋላ አረብ-እስራኤሎች የሠላም የተባለዉን ዉል የተፈራረሙት ለሌላ ጦርነት ጊዜ ለመግዢያ እንጂ ዘላቂ እንዳልሆነም ግልፅ ነበር።በርግጥም ጦርነቱ መቆሙ በተነገረ ማግሥት አንዱ ሌላዉን ለማጥፋት ሲዛዛቱ ከርመዉ በሰባተኛ ዓመቱ እስራኤል ከብሪታንያና ፈረንሳይ ጋር ግንባር ፈጥራ ግብፅን ወረረች።ሁለተኛ ጦርነት።1956።

ሁለተኛዉም ጦርነት ተዋጊዎቹ ሲደክማቸዉ ቆመ።እስራኤል አይሁድን ለሁለት ሺ ዘመናት ሲፈጁ፤ሲረግጡ፤ሲያግዙ የነበሩ የአዉሮጳ ቅኝ ገዢዎችን ተከትላ ለዝንተ-ዓለም በማትለያት ጎረቤትዋ ላይ የከፈተችዉ ጦርነት ወትሮም የሚያመረቅዘዉን ቁርሾ ከማጠናከር ባለፍ ለሠላም የተከረዉ የለም።

የ1967ቱ ጦርነት የተጀመረዉ የግብፁ ፕሬዝደንት ገማል አብድናስር ከ1956ቱ ጦርነት በኋላ ሲና በረሐ የሠፈረዉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ታዛቢ ሠራዊት በማስወጣታቸዉ ነዉ የሚሉ አሉ።ናስር የቲራንን ሠርጥ በመቆጣጠራቸዉ ነዉ የሚሉም አሉ።ሁለቱም ልክ ይሆኑ ይሆናል።

ግን ጥያቄ ያጭራል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ እየሩሳሌም ዉስጥ ሲገደሉ ጦርነት ለምን አልተጀመረም ነበር? የሚል ጥያቄ።ወይም  እስራኤል በ1948ቱ ጦርነት 112 የአረብ ሠፈሮችን ወይም 500 ስኩየር ማይል ሥትቆጣጠር ጦርነት እንዴት አልተነሳም።አይነት-ጥያቄ።

በጦርነቱ ወቅት በዩናይትድ ስቴትስ የእስራኤል አምባሳደር የነበሩት ማይክል ቤ. ኦሬን የስድስቱ ቀን ጦርነት ባሉት መፅሐፋቸዉ «እስራኤል ከአሜሪካ ያገኘችዉም ሆነ ራሷ ያሰባሰበችዉ መረጃ  የግብፁ ፕሬዝደንት ገማል አብድናስር ደም መፋሰሱን እንደማይፈልጉት የሚያረጋግጥ ነበር።»ይላሉ።

በቅርቡ ይፋ የሆነ ሰነድ እንደሚያመለክተዉ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ሌቪ ኤሽኮልም

Sechstagekrieg

ጦርነቱን አይፈልጉትም ነበር።የአሜሪካዉ ፕሬዝደንት ሊንደን ጆንሰንም ሆኑ የሶቬት ሕብረቱ መሪ ሊዮንድ ብሬዥኔቭ በዚያን ወቅት ጦርነት መለኮሶን አልፈለጉትም።ጦር እያደራጁ ጦርነት አንፈልግም፤ ተፋላሚዎችን እስካፍንጫቸዉ እያስታጠቁ ዉጊያ እንዳይጫር አሳሰቡ ብሎ ነገር በርግጥ ግራ አጋቢ ነዉ።

ከሁሉም በላይ ሥር የሰደደዉ የአረብ-አይሁድ መጠላላትን እያባባሱ ጦርነት አያስፈልግም ማለት ከእዉነታዉ ጋር መላተም ነዉ።ዮርዳኖስ ትቆጣጠረዉ የነበረዉን ምዕራባዊ እየሩሳሌምን የማረከዉ  የእስራኤል ጦር ባልደረባ የነበሩት ዮራም ዛሞሽ እንደሚሉት ግን ጦርነቱ ለእስራኤል አስፈላጊ እና ጠቃሚ ነበር።

                              

«እስከዚያ ጊዜ ድረስ እኛ የተበደልን ሕዝብ ነበርን።ደካሞች ነበርን።በአይሁድ ታሪክ እጅግ መጥፎ ከሆነዉ ከሆሎኮስት ትቢያ ገና ብቅ ማለታችን ነበር።የአይሁድ ሕዝብ ከናትሲ ጭፍጨፋ ከ25 ዓመት በኋላ ዳግም ያንሰራራበት ነበር።»

የጦርነቱን መጀመር አጥብቀዉ የፈለጉት የያኔዉ የእስራኤል  መከላከያ ሚንስትር ጄኔራል ሞሼ ደያን ቀድመን ማጥቃት አለብን አሉ።ጠቅላይ ሚንስትር ኤሽኮል «ወታደራዊ ድል የመጨረሻዉ ሊሆን አይችልም» በማለት የመከላከያ ሚንስትራቸዉን ሐሳብ ለማስቀየር ሞክረዉ ነበር።ግን የደያን ቃል ፀና። ቀድሞ ማጥቃት።

ሰኔ አምስት ጧት ሳይረኑ አጓራ። ከ200ዉ የአስራኤል ጄቶች አስራ-ሁለቱ ሲቀሩ የተቀሩት ሽቅብ ከነፉ።ወደ ሜድትራኒያን ባሕር። ባሕሩጋ ሲደርሱ ቀልበስ-ወደ ግብፅ።ከዚያ በየሆዳቸዉ ያጨቁትን ቦምብ በግብፅ የጦር ሠፈሮች ላይ ዘረገፉት።እያንዳዱ ጄት በየሰባት ደቂቃ ከሰላሳ ሴኮንዶ መሬት አርፎ፤ ነዳጅ ሞልቶ፤ ቦምብ አጭቆ ይበራል።ግብፅ፤ ዮርዳኖስ እና ሶሪያ ላይ አረብን ያረባያል።ስድስት ቀን።

ከ10ሺሕ እስከ 15ሺሕ የሚደርስ ግብፃዊ፤ ስድስት ሺሕ ዮርዳኖሳዊ፤ ሁለት ሺሕ ሶሪያዊ  ተገደለ።ከአራት ሺሕ በላይ ተማረከ።ከአራት መቶ በላይ የአረብ ጄቶች ንቅንቅ ሳይሉ ከሰሉ።«አናቀሽ» ይል ገባ አረብ-ድቀት እንደማለት።እስራኤሎች 776 ሰዉ ተገደለባት።አራት ሺሕ አምስት መቶ ቆሰለ።አስራ-አምስት ተማረኩ።46 አዉሮፕላኖች ጋዩባት።ዩናይትድ ስቴትስ 32 የዩናይትድ ስቴትስ የባሕር ኃይል ባልደረቦች ተገደሉ።

                                      

«የ1967ትን

ሐምሌና ነሐሴን ብትመለከት ለእስራኤል በጣም ትልቅ ድል ነዉ።እስራኤል ከመጥፋት አፋፍ ላይ ነበረች።በስድስት ቀናት ዉስጥ ግን ልክ በስድስት ቀን እንደመፈጠር የምትገዛዉ አካባቢ በሰወስት እጥፍ ጨመረ።

ይላሉ የታሪክ ተመራማሪ ጉይ ላሮን።በርግጥም የሲና በረሐ፤ጋዛ ሠርጥ፤ መላዉ እየሩሳሌም፤ምዕራባዊ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ፤ የጎላን ኮረብታ ደቡባዊ ሊባኖስ፤ በእስራኤል ቁጥጥር ስር ዋለ።ለእስራኤል ታላቅ ድል።«ከአንድ ዓመት በኋላ ግን ነገሩ በጣም የተወሳሰበ መሆኑን ሰዎች መረዳት ጀመሩ።በርግጥም ይሕ የመጨረሻዉ አልነበረም።ጠቡ አልተወገደም።»

ዉጊያዉ እንጂ ጦርነቱ አላባራም።በ1973 ሌላ ጦርነት ነበር።ከዚያ በኋላም የሊባኖስ እና የእስራኤል ጦርነት፤ የፍልስጤምና የእስራኤል ጦርነት፤ የሺዓ ሚሊሺያና የእስራኤል ጦርነት፤ የሐማስና የእስራኤል ጦርነት።ቀጥሏል። 

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ

 

 

 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች