የስደት ተመላሽ ኬንያውያን ሚና | አፍሪቃ | DW | 06.02.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የስደት ተመላሽ ኬንያውያን ሚና

የተለያየ ሙያ ቀስመው ወደ ሀገራቸው የሚገቡ ከስደት ተመላሽ ኬንያውያን ባለሙያዎች በሃገሪቱ የምጣኔ ሃብት ዕድገት ላይ ቁልፍ ሚና እንዳላቸው ተገለጸ። ባለሙያዎቹ በሰለጠኑበት ሙያ ላለፉት 15 ዓመታት የኬንያን ምጣኔ ሃብት በአመት አምስት በመቶ እድገት እንዲያስመዘግብ አድርገዋል። ለበርካታ ኬንያውያንም የስራ ዕድልን መፍጠራቸው ታውቋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:19

ተመላሾቹ ለኬንያ ዕድገት ቁልፍ ሚና አላቸው ተብሏል

በዓለም ዙሪያ የተበተኑ አፍሪቃውያን ስደተኞች በውጭው ዓለም የሚቀሰሙት ሙያ እና መዋዕለ ንዋያቸው የትውልድ ሃገራቸውን በልማት እና በማሳደግ ረገድ እጅግ የላቀ ሚና እንደሚኖረው ይታመናል። ኬንያውያንም በዚህ ረገድ በተለይም ሃገራቸውን በማልማት እና በኢንቨስትመንት ከማሳደጉ ጎን ለጎን አዳዲስ የቴክኖሎጂ ሽግግሮችን በማስተዋወቅ  በኩል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ብዙ እየሰሩበት ይገኛሉ። 

ከእነዚህ በርካታ የሙያ ስኬት ባለቤቶች መካከል ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ለ20 ዓመታት የኖሩት ዩኔ ኦዶንጎ ተጠቃሽ ናቸው። በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስፔሻሊስት እና የቢዝነስ አማካሪ ሙያ ምሩቅ ኦዶንግ ወደ ትውልድ ሃገራቸው ኬንያ ከተመለሱ ዓመታትን አስቆጥረዋል። ከሁለት የሙያ አጋሮቻቸው ጋር ዋና መዲናይቱ ናይሮቢ አቅራቢያ ሁርሊንግ ሃም ከሚገኝ አንድ አፓርትመንት ውስጥ የራሳቸውን የንግድ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ከፍተው እንቅስቃሴ ጀምረዋል።

በአሁኑ ወቅት ኬንያ ውስጥ ፈርጀ ብዙ አገልግሎት የሚሰጠው የሴንጋ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የትራንስፖርት እና የሎጂስቲክ ድርጅት ሃላፊ የሆኑት ኦዶንጎ በጥረታቸው ለዘመናት ሲያልሙት የኖሩትን የህይወት ስኬት ማግኘታቸውን ይገልጻሉ። ምንም እንኳ በሙያቸው በውጭው ዓለም ብዙ ጥቅም ያገኙ የነበረ ቢሆንም ለሃገራቸው ማገልገላቸው የመንፈስ እርካታን ሰቷቸዋል።

"በዩናይትድ ስቴትስ ስኖር ከፍተኛ ደመወዝ ነበር በሙያዬ የሚከፈለኝ። በአመት ከ 185 ሺህ ዶላር በላይ መደበኛ ገቢ ነበረኝ። ልዩ ልዩ የአበል ክፍያዎችን ጨምሮ ማለት ነው። ይሄ ግን ቤቴ ነው። እናም ለትውልድ ሃገሬ ማገልገሌ ያስደስተኛል" ይላሉ ኦዶንጎ።  

አዳዲስ እና ዘመናዊ ሶፍትዌሮችን  በመጠቀም ለልዩ ልዩ የምርት ግብዓቶች የሚያገለግሉ የጨረር ቴክኖሎጂዎችን የቀለም የማጣበቂያ የኬሚካል ውሁዶችን የፕላስቲክ ምርቶችን የፖሊመር ማይክሮ ፓውደር እና የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶችን የሚያመርተውና ከውጭ አስገብቶ የሚያከፋፍለው የሴንጋ ቴክኖሎጂ ካምፓኒ በኢንቨስትመንቱ መስክ የተሳካለት በአገልግሎቱም ዘርፍ በርካታ ደንበኞችን ያፈራ በፍጥነት እያደገ ያለ ድርጅት ነው ይላሉ ኦዶንግ። 

"በአሁኑ ወቅት እኛ ትልቅ የምንባል አይደለንም። ሆኖም ትንሹ ኩባንያችን ከሚጠበቀው በላይ በፍጥነት እድገትን እያስመዘገበ ነው። አሁን ማለት የምችለው ብዙዎች መቶ በመቶ ማለት ይቻላል ደንበኞቻችን ሆነዋል። በገበያው ላይ ተፈላጊነትን ለማግኘት በምርቶቻችን ላይ ከፍተኛ እና ተመጣጣኝ ቅናሽ አድርገናል። ደንበኞቻችንም በምርቶቻችን እና አገልግሎቶቻችን ደስተኛ በመሆናቸው ተመልሰው ወደ እኛ ይመጣሉ" ሲሉ ያብራራሉ።

የኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ እና አውራ መንገዶቿ በዩናይትድስቴስ ውስጥ እንደሚታዩ አንዳንድ ከተሞች በከፍተኛ ፍጥነት ዘመናዊነትን እና እድገትን እየተላበሱ ነው። ከውጭ የስደት ኑሮ ተመልሰው ዕውቀታችውን እና ገንዘባቸውን ጥቅም ላይ ያዋሉ እንደ ኦዶንግ ያሉ ባለሃብቶች እና ሌሎችም ዜጎቿ ለዚህ እድገቷ ትልቅ ድርሻ አላቸው። በውጭው ዓለም በሰለጠኑበት ሙያ ከፍተኛ ዓመታዊ ገቢ የነበራቸው ኦዶንግ ከዛ ይልቅ ዛሬ ህዝቤን እና ሃገሬን ማገልገሌ የበለጥ ያስደስተኛል ነው የሚሉት። ቀኑን ሙሉ ጊዜያቸውን ለስራቸው መስዋዕት ማድረጋቸውም ከወጭ ቁጠባ አንጻር ብዙ ጠቅሞኛል ሲሉ ይገልጸሉ። 

Destination Europe – Kapitel-Nr. 7

"ለማንኛውም እኔ  ብዙዎች ለዘመናት በህይወት ዘመናቸው የሚያልሙትን የኑሮ ስኬት አግኝቻለሁ። ቢሮዋችን የተሟላ አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ ስለሚያቀርብ ለሱፐርማርኬት የማወጣቸው ብዙ ውጭዎቼ ቀንሰዋል። ራሴንም በስራ በመጥመዴ ምክንያት ዛሬ 20 ዶላር እንኳ በወር አላባክንም" ሲሉ ያስረዳሉ።

በዩናይትድ ስቴትስ በሙያቸው ይሰሩ ስለነበር ኦዶንግ የተሳካ ህይወት ነበራቸው። ሆኖም ኬንያ ከዚህ የተለየ ነው። ሁላችንም ለሃገራችን አቅማችን የሚፈቅደውን ሁሉ ማበርከት አለብን ሲሉ ይመክራሉ። ዛሬ በኬንያ በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን ለበርካታ የሃገሪቱ ዜጎችም የስራ ዕድልን የፈጠረው የሴንጋ ቴክኖሎጂ ድርጅት በመርከቦች በአውሮፕላን ካርጎ እና በትላልቅ ተሽከርካሪዎች ጭምር የተለያዩ ምርቶችን ወደ ሃገር ውስጥ በማስገባት እና ተመጣጣኝ አገልግሎት ለህብረተሰቡ በመስጠት መጠነ ሰፊ ተግባር እያከናወነ ይገኛል። ያም ቢሆን በሃገሪቱ የሚታየው የቢሮክራሲያዊ ውጣውረድ አልፎ አልፎ በስራቸው ላይ እንቅፋት መፍጠሩን ኦዶንግ አልሸሸጉም። 

በኬንያ በውጭው ዓለም የተለያየ ሙያ ቀስመው ከስደት የሚመለሱ ከፍተኛ ባለሙያዎች በዓመት ሃገሪቱ የ 5 በመቶ የምጣኔ ሃብት እድገት እንድታስመዘገብ ትልቅ እገዛ እያበረከቱ ነው።

እንዳልካቸው ፈቃደ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic