የስደተኞች ጎርፍ በዮርዳኖስ | ዓለም | DW | 12.11.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የስደተኞች ጎርፍ በዮርዳኖስ

ባለፉት ዓመታት ዮርዳኖስ ከአካባቢዉ ሃገራት ወደ ሃገርዋ የሚገቡትን በርካታ ስደተኞች ስትቀበል ቆይታለች። ወደ ዮርዳኖስ የሚገቡት ስደተኞች በመጀመርያ ከፍልስጤም ከዝያ ከኢራቅ ነበር አሁን ደግሞ ከሶርያ በርካታ ስደተኞች በመፍለስ ላይ ናቸዉ። ይህች በንጉሳዊ አስተዳደር የምትመራ ትንሽ ሀገር የስደተኛ ጉዳይ ከባድ ፈተና ሆኖባታል።

በዩርዳኖስ እስካሁን ግማሽ ሚሊዮን የሶርያ ስደተኞች ተመዝግበዉ እንደሚገኙ ተመልክቶአል። በዮርዳኖስ በረሃማዉ ሜዳ ላይ በሚገኘዉ የስደተኞች መጠለያ ቦታ፤ የብረት ሰንዱቆች «ኮንቴይነር» ከጫፍ እስከጫፍ ተደርድሮ ከአድማስ እስከ አድማስ ይታያል። በነዚ በኮንቴይነሮች የተጨናነቀዉ ሰፊ መጠለያ ጣብያ«አዝረቅ» በሚል መጠርያ የሚታወቀዉ ሲሆን ከርስ በርስ ጦርነት ሸሽተዉ የተሰደዱ 13 ሺ የሶርያ ስደተኞች መኖርያ ነዉ። ወይዘሮ ሳይራ የአምስት ልጆች እናት ናቸዉ፤
« እራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ ከሚጠራዉ ቡድን ሸሽተን ነዉ የተሰደድነዉ። የአሰድ መንግሥትም እስካሁን ድረስ ያደረገልን ምንም ነገር የለም።

Syrische Flüchtlinge bei Suruc Türkei 02.10.2014

የሶርያ ስደተኞች

ልጆቻንን ልብ ላይ ፍርሃትን ብቻ ነዉ ያነገሰዉ። ልጆች ባይኖሩን ኖሮ ቤታችን ዉስጥ ቆልፈን ተደብቀን እዚያዉ እንቀር ነበር። አሁን ግን እራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ ከሚጠራዉ ሚሊሽያ መሸሽ ስለነበረብን ነዉ ሶርያን የለቀቅነዉ»
ወ/ሮ ሳይራ ይኖሩ የነበሩት በምስራቃዊ ሶርያ ዳይር አዝ ዞር ከተማ ዉስጥ ነበር። ሳይራና ልጆቻቸዉ በአሁኑ ጊዜ በአዝራቅ የስደተኞች መጠለያ ደህንነታቸዉ የተረጋገጠ ቢሆንም ወደ ዮርዳኖስ ለመግባት ድንበር ላይ ጥበቃ ላይ ስላሉት ቤተ-ዘመዶቻቸዉ ደህንነት መስማት ይሻሉ ይጨነቃሉም። የዮርዳኖስ ድንበር ለማንኛዉም ክፍት መሆኑ ነበር የሚታወቀዉ፤ ግን ከጥቂት ሳምንታት ጀምሮ ድንበርን አቋርጦ የገባ ሰዉ የለም ሲሉ ወ/ሮ ሳይራ ይገልፃሉ፤
« ዋናዉ አሁን ድንበሩን አቋርጦ ወደዚህ መግባት ቢፈቀድ ነበር ጥሩ የሚሆነዉ። ሶርያ መልሳ የምኖርባት ሃገሪ ትሆናለች የሚል ተስፋም አለኝ። ሁሉ ነገር በሶርያ ይሻላል ጥሩ ነዉ። የሶርያ መሪትዋ አፈርዋ ሁሉ ዉድ ነዉ»
የአምስት ልጆች እናት ስለአገራቸዉ ስለ ሶርያ ሲያስቡ እንባ ይቀድማቸዋል። ሶስት ዓመት ጦርነት ከዝያ ደግሞ ስደት ብዙ አስከፊና ዘግናኝ ህይወትን እንዳሳለፉ ይናገራሉ። በመጠለያ ጣብያዉ እጅግ ጠባብ በሆነ ኮንቴይነር ዉስጥ አንድ ሁለት ብርድ ልብስና የማብሰያ የጋዝ ምድጃ ተሰጥቶአቸዉ እየኖሩ ነዉ።
ሶርያ ድንበር ዮርዳኖስ በረሃ ላይ የተገነባዉ የአዝራቅ የስደተኞች መጠለያ ጣብያ ስራዉን የጀመረዉ ባለፈዉ መጋቢት። ከሶርያ ወደ ዮርዳኖስ የሚገባ ስደተኛ ሁሉ በአዝራቅ የስደተኞች መጠለያ ይመዘገብና ኑሮን ይጀምራል። መጠለያ ጣብያዉ በድንኳን መኖርያ ምትክ አራት መዓዘን የሆኑት ከብረት የተሰሩት ኮንቴነሮች ድንጋያማዉ የበረሃዉ ወለል ላይ ተደርድረዉ ቆመዋል። እንድያም ሆኖ አዝራቅ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በሰሜናዊ ዮርዳኖስ ከሚገኘዉና በተገን ጠያቂዎች ከተጨናነቀዉ « ዛታሪ» መጠለያ ጣብያ በተሻለ መልኩ ዘርዘር ብሎ የተገገነባ መሆኑ ነዉ የተመለከተዉ።

Türkei - Syrische Flüchtlinge aus der Stadt Kobane

የሶርያ ተገን ጠያቂ እናት

በአዝራቅ በርካታ የዓለማቀፍ ርዳታ ሰጭዎች መጠለያ ጣብያዉ ለክረምት ወራት መኖራያ የተመቻቸ እንዲሆን በከፍተኛ ፍጥነት እና ዉጥረት እየሰሩ ይገኛሉ። በጣብያዉ እጅግም ያልነበረዉን መፀዳጃ ቦታ የጀርመን የርዳታ ሰጭ ተቋም« THW »በተሻለ ሁኔታ ገንብቶአል። ጣብያዉ ከፀኃይ ሃይል የሚሰበሰበዉን የኤሌትሪክ ሃይል በመጠቀም ማታ ማታ አነስተኛ የመብራት ኃይል ጥቅም ላይ ቢዉልም፤ እስካሁን ይሄ ነዉ የሚባል ትክክለኛ የኤሌትሪክ አገልግሎት አልተዘረጋም። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) ባልደረባና የአዝራቅ የስደተኞች ጣብያ ተጠሪ ቤርናዴት ካስትል ሆሊንግስቮርዝ ነገሩ እጅግ እንደሚያሳስባቸዉ ይገልፃሉ።
«በርካታ ስደተኞች የሚገኙበትና ሰብዓዊ ቀዉስ ያለበት አካባቢ ነዉ፤ ቢሆንም ዓለም ትኩረቱን በማድረግ ፊቱን ያዞረዉ ወደሌላ አቅጣጫ ነዉ ማለት ይቻላል። ዓለማቀፉን ማኅበረሰብ የምንጠይቀዉ ግን እዚህ አካባቢ ለሚገኙት የሶርያ ስደተኞችና ለዮርዳኖስ መንግሥት የርዳታ በማድረግ እጁን እንዲዘረጋ ነዉ። »


ከሶርያ ወደ ሊባኖስ የገባዉና የተመዘገበዉ ስደተኛ ቁጥር 613 ሺ ደርሶአል። ያልተመዘገበዉ ተገን ጠያቂ ቁጥር ደግሞ በስደተኝነት ከተመዘገበዉ ስደተኛ እንደሚበልጥ ነዉ- የሚገመተዉ። በሳታሪ አልያም አዝራቅ መጠለያ ጣብያ ከ 100 ሺ በላይ ተገን ጠያቂዎች ይገኛሉ። ሌሎች የሶርያ ስደተኞች በድንበር ከተማዎች አልያም መዲና አማን ያለምንም ምዝገባ ይኖራሉ። በባህልም ሆነ በኤኮኖሚ እጅግ ቅርበት ያላቸዉ ጎረቤታሞቹ ሶርያና ዮርዳኖስ፤ በሶርያዉ የርስ በርስ ጦርነትና የህዝብ ፍልሰት ምክንያት ያላቸዉ የጠበቀ ግንኙነት ሻክሯል። በሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ላይ የተደቀነዉን ይህን ቀዉስ ለመቅረፍ የሚቻለዉ የሶርያን ጦርነትና በጦርነቱ የሚደርሰዉን ቀዉስ ማስቆም ከተቻለ ብቻ ነዉ። በዮርዳኖስ በሚገኘዉ የስደተኞች ጣብያ የሚኖሩ ሶርያዉያን፤ጦርነቱ እስከቀጠለ ድረስ ለችግሩ መፍትሄ የማፈላለጉ ሂደት እጅግ ከባድና ዉስብስብ ይሆናል ሲሉ አስተያየታቸዉን ይሰጣሉ።

ታንያ ክሪመር / አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሃመድ

Audios and videos on the topic