የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች ጉባዔ በቪየና | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 27.08.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች ጉባዔ በቪየና

የሰርቢያ እና የመቄዶንያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች የአውሮጳ ህብረት ለምዕራብ ቦልካን ሃገራት የሚሰጠውን ርዳታ ከፍ እንዲያደርግ ዛሬ በኦስትርያ መዲና ቪየና በተከፈተው በስደተኞች ጉዳይ ላይ በሚመክረው የምዕራብ ቦልካን ጉባዔ ላይ ጠየቁ።

በምዕራብ ቦልካን የሚገኙት ሃገራት፣ መቄዶንያ፣ ሰርቢያ፣ ቦዝንያ ሄርሶጎቪና፣ ኮሶቮ፣ አልባኒያ፣ ከመካከለኛ ምሥራቅ፣ አፍሪቃ እና ደቡብ እስያ የሚመጡ ስደተኞች በአሁኑ ጊዜ ወደ አውሮጳ ለመግባት የሚያዘወትሩት ዋነኛ መተላለፊያ ናቸው። የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር የአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት ወደ አውሮጳ የሚመጡትን እጅግ ብዙ ስደተኞች ፍትሓዊ በሆነ መንገድ እንዲከፋፈሉ የስደተኞቹ ጎርፍ በአህጉሩ ያስከተለውን ቀውስ መነሻ በማድረግ ጠየቁ። አውሮጳውያኑ መንግሥታት ይህን ካላደረጉ በወቅቱ ብዙዎቹን ስደተኞች በመቀበል ላይ ባሉት ሃገራት ውስጥ አለመረጋጋት የሚፈጠርበት ስጋት መደቀኑን በማስታወቅ ስደተኞቹ በትውልድ አገራቸው ሊቆዩ የሚችሉበትን ሁኔታ እንዲነቃቃ ስድስት የምዕራብ ቦልካን ሃገራት እና የአውሮጳ ህብረት መሪዎች የተገኙበት የምዕራብ ቦልካን ጉባዔ ሊጀመር ጥቂት ጊዜ ሲቀረው ሀሳብ አቅርበዋል። የስደተኞቹን ክፍፍል በተመለከተ ከሽታይንማየር ጋር የሚመሳሰል ሀሳብ የሰነዘሩት የኦስትርያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰባስቲያን ኩርስ የአውሮጳ ህብረት አንድ ልዩ ጉባዔ እንዲጠራ ጠይቀዋል።

« ለዚሁ ጉዳይ ጠቃሚ ይሆናሉ ብለን ያሰብናቸውን አምስት ነጥቦችን አቅርበናል። የመጀመሪያው የስደት ምክንያቶችን፣ በመቀጠልም፣ በ«አይ ኤስ» አንፃር ትግሉን ማጠናከር፣ በዚያው በሃገራቸው ከለላ የሚያገኙበት ሥፍራ ማዘጋጀትን ይመለከታል። ምክንያቱም፣ የኛ የአውሮጳውያኑ የጋራ ዓላማ ስደተኞቹ ወደ አውሮጳ ህብረት ጉዞ እንዳይጀምሩ በዚያው በትውልድ ሃገራቸው አስፈላጊው ርዳታ ማቅረብ መሆን አለበት ብየ ነው የማምነው። እዚህ አውሮጳ ውስጥ ደግሞ በግሪክ ለሚታየው ችግር መፍትሔ ማግኘት አለብን፣ ምክንያቱም፣ ግሪክ ስደተኞቹ ወደ ሌላ ሃገራት ሲጓዙ እያየች ርምጃ እስካልወሰደች ድረስ፣ በጀርመን፣ ኦስትርያ እና ስዊድን ውስጥ የስደተኛው ቁጥር ከፍ ማለቱ አይቀርም፣ ይህን ደግሞ ለዘለቄታው ልንቋቋመው አንችልም። »

እአአ በጥር እና በሀምሌ 2015 ዓም መካከል 102,000 ስደተኞች በምዕራብ ቦልካን ሃገራት በኩል አድርገው ወደ አውሮጳ ህብረት ሃገራት መግባታቸውን ፍሮንቴክስ የተባለው የህብረቱ ድንበር ጠባቂ ድርጅት አስታውቋል።

አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ