የስደተኞች ይዞታ በኢጣልያ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 13.10.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የስደተኞች ይዞታ በኢጣልያ

ስደተኞችን የማሻገሩ ሥራ ቱኒዝያ ወደ ሚገኙ ወንጀለኞች ተዛውሯል ይላሉ። እንደ አቃቤ ሕጉ በአጭር ጊዜ ውስጥ በዚህ መንገድ በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች አውሮጳ ገብተዋል።ይህ ሊሆን የቻለውም ከቱኒዝያዎቹ ከስፋክስ ወይም ከሞናስቲር ወደ ሲሲሊ ወይም ወደ ላምፔዱዛ አሳ አጥማጅ ጀልባዎች ስደተኞችን ደብቀው እየጫኑ በመምጣታቸው ነው እንደ አቃቤ ሕጉ። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:00

የስደተኞች ይዞታ በኢጣልያ

ካለፈው ጥር ማለትም ከጎርጎሮሳዊው 2020 ዓም መጀመሪያ አንስቶ እስካሁን ኢጣልያ የገበት ስደተኞች ቁጥር ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ጊዜ ኢጣልያ ከገቡት ጋር ሲነፃጸር በአራት እጥፍ ይበልጣል።በአሁኑ ጊዜ በሃገሪቱ የሚገኙት የስደተኞች መቀበያ ማዕከላት ከመጠን በላይ በስደተኞች ተጨናንቀዋል።ክርስቲን አወርባህ ስደተኞች በብዛት ወደ አውሮጳ ከጎረፉበት ከዛሬ አምስት ወዲህ በኢጣልያ ያለውን ሁኔታ በቃኘችበት ዘገባዋ በኮሮና የተያዙና ሊያዙ የሚችሉ ስደተኞች ጉዳይም ያሰጋል።ከዚሁ ጋርም ከጀርመን በግዳጅ ወደ ኢጣልያ የተመለሱና ሌሎችም ስደተኞች  ኢጣልያ የሚገኙ ስደተኞች ይዞታም አሳሳቢ ነው። 
ከምሽቱ አንድ ሰዓት ተኩል ሆኗል።አንድሪያ ኮስታ በአንድ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ 70 ለሚሆኑ ከሱዳን ከኤርትራ ከሶማሊያ ከጋምቢያ ከጋና እንዲሁም ከሰሜን አፍሪቃ ለመጡ ስደተኞች እራት ያከፋፍላል።አንድሪያና ሌሎች መሰል በጎ ፈቃደኞች ባኦባብ የተባለው ድርጅት ለስደተኞች የሚያቀርበውን ምግብ ያከፋፍላሉ።ስደተኞቹ ሮም በሚገኘው በቲቡርቲና ባቡር ጣቢያ ጀርባ መሪት ላይ  ካርቶን አንጥፈው ነው የሚተኙት።
«እዚህ ወደ ሌሎች ሃገራት በጀልባ የመጡ አዳዲስ ስደተኞችን እንረዳለን።እዚህ ከመጡ አንድ ሁለት ሳምንት ሆኗቸዋል።ሌሎች ደግሞ ወራት አስቆጥረዋል።ከመጡ ጀምሮ ጎዳና ላይ ነው የሚያድሩት።ከመካከላቸው አብዛኛዎቹ በስደተኖች ማዕከላት ውስጥ ነበር የሚኖሩት።ሆኖም ሳልቪኒ ኢጣልያ የምትቀበላቸውን ስደተኞች ቁጥር ካሳነሱ በኋላ አብዛኛዎቹ ጎዳና ላይ

ወድቀዋል።ይህን መሰሉ ኑሮ ስደተኞቹን እያብከነከናቸው ነው። አንዳንዶቹም ዐዕምሮአቸውን ስተዋል።»
ማትዮ ሳልቪኒ ስደተኞች ኢጣልያ እንዳይገቡ ጥብቅ ክልከላ የጣሉት ከጎርጎሮሳዊው ሰኔ 2018 እስከ መስከረም 2019 የኢጣልያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ነበሩ።ስደተኞቹ የወደቁበት ስፍራ የአምቡላንስና የሞተር ቢስኪሌት ድምጽ የማይለው በጥቅሉ ጸጥታ የሌለው ቦታ ነው።በስፍራው ጥላ የሚሆን ነገርም የለም።በበጋ ወራት ሙቀቱ ቀን ብቻ አይደለም ማታም ጭምር   እንደ ፉርኖ ቤት ይጋረፋል።ቀድሞም እምብዛም ያልነበሩት የኢጣልያ የስደተኞች መቀበያ ቦታዎች፣«ሌጋ ኖርድ»የተባለው የኢጣልያ ቀኝ ክንፍ ፓርቲ መሪ ሳልቪኒ  የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሲሆኑ አብዛኛዎቹ ተዘጉ።በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ደግሞ የስደተኞች ጉዳይ ትኩረት በማጣቱ በጀልባ ወደ ኢጣልያ የሚሰደዱት ቁጥር አሻቀበ። ምፔዱዛ እና ሲሲሊ የሚገኙት የስደተኞች መቀበያ ማዕከላት ተስፋ በሚያስቆርጥ ሁኔታ በስደተኞች ተጨናንቀዋል። አብዛኛዎቹ ጀልባዎች ደግሞ የስራ አጡ ቁጥር ከጨመረበትና በኮሮና ተህዋሲ ምክንያት በተወሰዱ እርምጃዎች ኤኮኖሚዋ ክፉኛ ከተጎዳው ከቱኒዝያ ነው የሚመጡት።ሆኖም ከቱኒዝያ የሚመጡት የጀልባ ስደተኞች ቱኒዝያውያን ብቻ አይደሉም ይላሉ  የደቡብ ሲሲሊ አቃቤ ሕግ ቢሮ ሃላፊ

ሉዊጂ ፓትሮናጆ።በፓትሮናጆ አባባል አሁን ሌላ የስደት መስመር ተከፍቷል።
«እንደመርማሪዎች አዲስ የስደት መስመር ተከፍቷል የሚል እምነት አለን።ስደተኞች በእቅድ ከሊቢያ እና ከግብጽ ወደ ቱኒዝያ ይወሰዳሉ።» 
ፓትሮናጆ በኢጣልያ ከፀረ ማፍያ ታዋቂ መርማሪዎች አንዱ ናቸው።አሁን የሚያዩት ግና ከስደት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ነው።ይበልጥ የታወቁትም ከቀድሞው የኢጣልያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ማቴዮ ሳልቪኒን አቋም በተቃራኒ ስደተኞችን የጫኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መርከቦች ሲሲሊ መልህቃቸውን እንዲጥሉ በመፍቀዳቸው ነው።
ፓትሮናጀ እንደሚሉት የጀልባዎቹ መነሻ ከሊቢያ ወደ ቱኒዝያ የመሸጋገሩ ምክንያት የሊቢያ ሚሊሽያዎች በርስ በርሱ ጦርነት መጠመዳቸው ነው። አሁን ስደተኞችን የማሻገሩ ሥራ ቱኒዝያ ወደ ሚገኙ ወንጀለኞች ተዛውሯል ይላሉ። እንደ አቃቤ ሕጉ በአጭር ጊዜ ውስጥ  በዚህ መንገድ በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች አውሮጳ ገብተዋል።ይህ ሊሆን የቻለውም ከቱኒዝያዎቹ ከስፋክስ ወይም ከሞናስቲር ወደ ሲሲሊ ወይም ወደ ላምፔዱዛ አሳ አጥማጅ ጀልባዎች ስደተኞችን ደብቀው እየጫኑ በመምጣታቸው ነው ይላሉ አቃቤ ሕጉ። 
«ተቀይሯል፤ ገና የሊቢያን የውሐ ክልል ለቀው እንደወጡ የሚሟሽሹት ከጎማ የተሰሩት የቻይና ጀልባዎች አይደሉም ስደተኞቹን የሚያመጡት።ከቱኒዝያ የሚነሱ የአሣ ማጥመጃ ጀልባዎች በሜዴትራንያን ባህር ላይ ያን ያህል ትኩረት የሚስቡ አይደሉም።እነዚህን ጀልባዎች ከጉምሩክ ፖሊስ እና ከድንበር ጠባቂው ከፍሮንቴክስ አውሮፕላኖች በቀላሉ መለየት አይቻልም።»
ስደተኞቹ ራቅ ወዳሉ የባህር ዳርቻዎች ወርደው ጉዞአቸውን ይቀጥላሉ።አብዛኛዎቹ ግን በፖሊስ ይያዛሉ።አሁን የኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ነውና ወደ ለይቶ ማቆያ ነው የሚወሰዱት።እነዚህ ማቆያዎችም በሰዎች የተጨናነቁ ናቸው።በጣም ትንሽ ጠባብ እና በጣም የሚሞቁ ናቸው። ባለፉት ጊዜያት በመላው ኢጣልያ ስደተኞች በተደጋጋሚ ከለይቶ ማቆያዎች ጠፍተዋል።በዚህ የተነሳም የለይቶ ማቆያዎቹ የጠባቂዎቹ ቁጥር እንዲጨምር ሲደረግ አንድ መርከብም በተጨማሪ በለይቶ ማቆያነት እያገለገለ ነው። ፓትሮናጆ እንደሚሉት አዲሱ የስደት መስመር ተጨማሪ

ችግር እየፈጠረ ነው።  
«በአንድ በኩል ከሰሃራ በስተደቡብ ከሚገኙ ሃገራት ሊቢያ ወይም ግብጽ የተሰደዱ አul።በሌላ በኩል  ከኢጣልያ የተባረሩና የወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው ቱኒዝያውያን አሉ። በሕገ ወጥ መንገድ ኢጣልያ በመግባት የታሰሩ ብዙ ስደተኞች አሉ።»      
የኢጣልያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ ኢጣልያ በብዙ ትግል በኮሮና የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ የምታደርገው ጥረት በስደተኞች እምቢተኝነት እንዲሰናከል እንደማይፈቅዱ ነው ያሳሰቡት።
«ስደተኞች በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ኢጣልያ አንዲሰደዱ አንፈቅድም።ኢጣልያኖች ከኮሮና ተህዋሲ ጋር ባደረጉት ትግል የከፈሉት መስዋዕትነት የህክምና ቁጥጥርን በሚጥሱ ስደተኞች መና እንዲቀር አንፈልግም።ጠንካራና ጨካኝ መሆን አለብን። ስደተኞችን ወደመጡበት መመለስ ተጠናክሮ ይቀጥላል። »
ከዚህ ሌላ ሮም፣የአውሮጳ ሕብረት አባል ሃገራት ስደተኞች እንዲከፋፈሉ ድጋፍ እንዲያደርግ ዳግም ጥሪ አድርጋለች። ምንም እንኳን ሃገራቱ በ2019ኙ የማልታ ስምምነት ስደተኞች ለመቀበል እሺታቸውን ቢገልጹም እስካሁን ተግባራዊ አልሆነም። ፓትሮናጆ ግን ወደ አውሮጳ የሚሰደዱት ሰዎች ሃገራት ህዝብ ሕይወት እንዲለወጥ አውሮጳ ከአሁኑ የበለጠ እንዲሰራ ነው የሚያሳስቡት።እርሳቸው እንደሚሉት ከሰራ በስተደቡብ ከሚገኙ ሃገራት የሚመጡ ስደተኞች ወደ 2ሺህ ዩዩሮ እየከፈሉ በአዲሱ የስደት መስመር ኢጣልያ የሚገቡት።ቱኒዝያውያን ደግሞ አንድ ሺህ ዩሮ ይከፍላሉ።ይህን ለመግታት ደግሞ ቁጥጥር ያስፈልጋል።ቁጥጥሩ ሕገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪዎቹ ላይ ሊሆን  ይገባልም ይላሉ።

የባኦባቡ የእርዳታ ድርጅት በጎ ፈቃደኛ ሃላፊ አንድሪያ ኮስታ ደግሞ ኢጣልያ የሚገኙ ወንጀለኛ ድርጅቶችም ሊተኮርባቸው ይገባል ይላሉ።እነዚህ ድርጅቶች ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን ስደተኖች በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች በፍራፍሬና በአትክልት ማሳዎች ላይ በማሰራት ብዙ ገንዘብ ያተርፋሉ ይላሉ። 
«ይህ ከባርነት ጋር የሚስተካከል ነው።12 ሰዓታት ቲማቲም ሲለቅሙ ውለው 8 ዩሮ ነው የሚከፈላቸው።እነርሱ በርካሽ ጉልበት በሰበሰቡት ቲማቲም የተሰራውን ፒሳ ደግሞ እኛ እንበላለን።»
በቱኒዝያ በኩል ስለሚመጡት ስደተኞች ብዙ እየተነገረ ቢሆንም ምንም አልተደረገም።ብዙዎች ደግሞ ከጀርመን ወደ ኢጣልያ እየተጠረዙ መሆኑን የባኦባብ ባልደረባ ጁልያ ሮምፔል ያስረዳሉ
«ከጀርመን የተጠረዙ በርካታ ስደተኞች እዚህ መኖሪያ የላቸውም ፤የሥራ እድል አላገኙም ፤ምንም የላቸውም ጎዳና ላይ ነው ያሉት።»
ከመካከላቸው ጀርመንኛ አቀላጥፈው የሚናገሩ ይገኙበታል። 4 ዓመት ደቡብ ጀርመን የኖረ ና የሰራ ስደተኛ አንድ ነው።አሁን ኢጣልያ ጎዳና ላይ ወድቋል።ለብዙዎቹ ስደተኞች ኢጣልያ መሸጋገሪያቸው ናት።ይሁንና በደብሊኑ ስምምነት መሠረት ከኢጣልያ ወደ ሌሎች የአውሮጳ ሃገራት የሄዱ ሕገ ወጥ የሚባሉ ስደተኞችን መጀመሪያ ወደገቡበት ሃገር ነው የሚመልሷቸው።አሁን አሁን በኢጣልያ ስደተኞች ላይ የተጫኑ ሕግጋት እየላሉ ነው።ይህም ባኦባብን ለመሳሰሉ ስደተኞችን ለሚረዱ ድርጅቶች ሥራቸውን ቀላል እያደረገላቸው ነው።በአንድሪያ ኮስታ አመለካከት ስደተኞች ችግር አይደሉም ።ችግር የሚሆኑት ግን በአግባቡ ካልተያዙ ነው።

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ 
 

Audios and videos on the topic