የስደተኞች የወሲብ ጥቃትና የኢትዮጵያዉያን አስተያየት | ባህል | DW | 14.01.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

የስደተኞች የወሲብ ጥቃትና የኢትዮጵያዉያን አስተያየት

« በአሁኑ ጊዜ ጥላቻ መንፈስ እንዳይነሳ በተለይ ኒዮ ናዚ የሚባሉት ቡድኖች ይህን አማካይ መንገድ በመጥቀስ ሆነ ብለዉ ለራሳቸዉ እንዲመቻቸዉ እንዳይጠቀሙበት የዉጭ አገር ሰዎች የሆነዉ ሁሉ ተጠንቅቀን ሥነ-ስርዓት አክብረን የተሰጠንን ሕግ ተጠቅመን ብንኖርበት ጥሩ ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 16:25

የስደተኞች የወሲብ ጥቃትና የኢትዮጵያዉያን አስተያየት

ለኢትዮጵያዉያንም የምመክረዉ ይሄንን ነዉ። ቶሎ ብላችሁ ራሳችሁን ቻሉ፤ ተማሩ ራሳችሁን አዘጋጁ፤ በጥገኝነት ብቻ መኖር አትሞክሩ፤ በርዳታ ለመኖር ብቻ አታስቡ፤ ምክንያቱም ይህ በረጅሙ ሲታይ ለራስ ጉዳት ነዉ። አንድ ሰዉ ራሱ እኔ ምን አድርጌ የትደረስኩ የሚለዉ መንፈስ ለራሱ አርኪ መንፈስ ስለሆነ ያንን እድል እድሉም ስላለ፤ ተጠቀሙበት»


በኮለኝና በሌሎች የጀርመን ከተሞች በጎርጎረሳዉያኑ 2016 ዓ,ም ዋዜማ አዲስ ዓመትን ለመቀበል በወጡ ሴቶች ላይ የተለያዩ ጥቃቶች መድረሳቸዉን በተመለከተ ሲስተር መሰረት አለፈለገሰላም የሰጡን አስተያየት ነዉ። የዛሬ አስራ አምስት ቀን በተለይ እዚህ ራድዮ ጣቢያችን በሚገኝበት ቦን ከተማ አቅራብያ በሚገኘዉ ኮለኝ ከተማ በተካሄደዉ የአዲስ ዓመት መቀበያ ሥነ-ስርዓት ላይ በሴቶች ላይ ወሲባዊ ጥቃትና ትንኮሳ እንዲሁም ዝርፍያ መፈፀሙ የጀርመንን ሕዝብ አስደንግጦአል። ጉዳዩ የፖለቲከኞች የብዙኃን መገናኛዎች መነጋገርያ ርዕስም ሆኖ ነዉ የሰነበተዉ። ዜጎች በእንግድነትም ሆነ በጥገኝነት በሚኖሩባቸዉ ሀገሮች ሥለሚኖሩት ማኅበረሰብ ባህልና አኗኗር የማወቅ አክብሮ የመኖር ሰብዓዊ ግዴታቸዉ አይደለምን? ይህ ከባህል ከልምድ አኳያስ እንዴት ይታያል?

በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ዋዜማ ኮለኝና በሌሎች የጀርመን ትላልቅ ከተሞች በሴቶች ላይ የተቃጣዉ ጥቃትና ወሲባዊ ትንኮሳ እንዲሁም ዝርፍያ ጀርመናዉያን ብሎም ሌሎች አዉሮጳዉያን አገሮች ለስደተኞች እና ለተገን ጠያቂዎች

ያላቸዉን አመለካከት እንዲቀይሩ ያስገደደ ይመስላል። ተገን ጠያቂዎች ከሰሜን ምሥራቅ ከመካከለኛዉ ምሥራቅና ከሌሎች አንዳንድ የእስያ አገሮች ወደ መሃል አዉሮጳ በሚጎርፉበት በአሁኑ ወቅት በሴቶች ላይ ጥቃት መፈፀሙ ነዋሪዉ ላይ ፀረ-ስደተኝነት ስሜት እንዳያጠናክር ስጋት አሳድሮአል። ስደተኞችን በመቃወም ሰልፈኞች አደባባይ ለሰልፍ ሲወጡ ሌሎች በአንጻሩ ለመቻቻል ለመግባባት በሚል መፈክር ይዘዉ ሲወጡና ስደተኞችን የሚቃወሙትን ሲቃወሙ ይታያል። እዚሁ በኖርድዝ ራይን ዌስት ፋልያ ግዛት፤ ከራድዮ ጣብያችን እንብዛም ሳይርቅ አንድ ግዙፍ የአዛዉንቶች መጦርያን የሚያስተዳድሩት፤ ሲስተር መሠረት አለፈለገሰላም በጀርመን ሲኖሩ ከ 30 ዓመት በላይ ሆኗቿዋል። ሲስተር መሠረት አለፈለገሰላም እንደሚሉት እኔ ራሴ በጥገኝነት ስለምኖር ባህላቸዉን ሕጋቸዉን አክብሪ ነዉ ሲሉ ይናገራሉ።

« እኔ ራሴ እነሱ ራሳቸዉ ኢሚግራንት በለዉ ከሚጠሩዋቸዉ ሰዎች መካከል አንዷ ነኝ። ኢሚግራንት ማለት የነሱን ስርዓትና ወግና ሕግ አክብሮ በአኗኗራቸዉን አክብሮና ተቀብሎ ስርዓት ይዞ የሚኖር ማለት ነዉ። ስደተኞች ዉጥረትና ችግር ካሉባቸዉ ሃገራት እየጎረፈ ሲመጣ በመራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል አማካኝነት በደስታ እድል ሰጥተዉ ተቀብሉዋቸዉ። ይህ በእዉነት ማንም አገር ያልታየ ደግነት ነዉ። እነዚህ ስደተኞች ሕግ በመጣስ የመጨረሻዉን ብልግና ሥራ በመስራት፤ እንደዉም አገዘችን እች ሰዉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ጭቅጭቅን ችላ ተቀበለችን፤ በአገሯ ካሉ ፖለቲከኞ ጋር ያለዉን ሁሉ ዉጣ ዉረድ ተሸክማ በርዋን ከፍታ ተቀብላናለች ብሎ አክሮ ያገኙትን እድል በመጠቀም የሚጠበቅባቸዉን ነገር እንደመስራት እና ተመስገን ብሎ እንደመኖር እንዲህ አይነት አስነዋሪ ስራ መፈፀማቸዉ የሚያሳዝን ነዉ። »


ሌላዉ በጀርመን ሲኖሩ ከ ሁለት አስርተ ዓመታት በላይ የሆናቸዉ የኢትዮጵያ አርቲስቶች ማኅበር የጀርመን ተጠሪ አቶ ተፈሪ ፈቃደ ፤ እንደሚሉት ተገን ጠያቂዎቹ የፈፀሙት ድርጊት ከአገሩ ዉጭ የሚኖር ተገን ጠያቂ ሁሉ ያፈረበትን ሥራ ነዉ ሲሉ ተናግረዋል። አቶ ተፈሪ እንደተናገሩት በተለይ አሁን አሁን በስደተኝነት የሚመጡ ኢትዮጵያዉያን ወጣቶች በድግስ ላይ ወይም ኢትዮጵያዉያን በሚዘጋጁት የመገናኛ መድረክ ላይ አንድ ቢራ ጠጥተዉ መደባደብ ሲቀናቸዉ ይታያል። ይህ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነዉ። በዉች የሚገኙ የኢትዮጵያ የቪክ ማኅበራትና የኃይማኖት ተቋማት ትምህርትና ምክር ሊሰጡዋቸዉ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።


ማንኛችንም ቢሆን የምንኖርበትን ሀገር ሕግጋትና ባህልን አክብረን መኖር ግዴታችን ነዉ ያሉን በቤት እንስሳ ሕክምና የዶክትሪት ማዕረጋቸዉን እዚሁ በጀርመን ያገኙትና በዘርፉ ሥራ ላይ ተሰማርተዉ የሚገኙት ዶክተር ፍስሃ አያና በበኩላቸዉ፤ በኮለኝ ከተማ የዉጭ አገር ዜጎች በሴቶች ላይ የፈፀሙት ተግባር የጀርመንን ሕዝብ አሳዝኖአል። በዉጭ አገር ዜጋ ሰበብ በአገሪቱ የሚገኙ የዉጭ ሃገር ዜጎች ላይ ጥላቻ እንዲነሳ የሚያደርግ ተግባር ነዉ የፈፀሙት።
በበርሊን ነዋሪ የሆኑትና የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን እዚሁ በጀርመን ያጠናቀቁት አቶ ኤልያስ ይመር በሰጡን አስተያየት፤ በጀርመን በሚታየዉ ከፍተኛ ጥበቃ ጥቃት አዳራሾቹ እዝያዉ ቦታ ላይ አለመያዛቸዉ የሚገርም ነዉ።
ቃለ-ምልልሱን የሰጡንን በዶቼ ቬለ እያመሰገንን ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማድመጫዉን ማዕቀፍ በማጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ


ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic