የስደተኞች ዕልቂት ይቆም ይሆን? | ኢትዮጵያ | DW | 25.04.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የስደተኞች ዕልቂት ይቆም ይሆን?

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስከሬን ይቆጥራል።በድርጅቱ ዘገባ መሠረት የበቀደሙ አደጋ ከመድረሱ በፊት ከጥር ወዲሕ ብቻ ከሰባት መቶ በላይ ስደተኞች ሜድትራኒያን ባሕር ዉስጥ ሰምጠዉ ሞተዋል።የበቀደሞቹ ሲጨመሩ ቁጥራቸዉ ከ1200 ይበልጣል።ወጣቶቹ-አለቁ፤ አለፉ። ቀጣዩ ተረኛ ማን ይሆን?

አምና ይሔኔ-ኢትዮጵያዉያንን ያሳዘነ-ያስቆጨ፤ ከአዲስ አበባ እስከ ዋሽግተኝ ለሠልፍ ያሳደመዉ እራሱን እስላማዊ መንግሥት (ISIS) ብሎ የሚጠራዉ አሸባሪ ቡድን ኢትዮጵያዉን ስደተኞችን ሊቢያ ዉስጥ መረሸን-መቅላቱ ነበር።ከዓምና እስከ ዘንድሮ ከታንዛኒያ እስከ ሠሐራ በረሐ፤ ከአደን እስከ ሜድትራንያን ባሕር ያለቁ ኢትዮጵያዉን ስደተኞችን የዘከረ-ቀርቶ ብዛትና ማንነትን በዉል የሚያዉቀዉ የየሟቹ ቤት ብቻ ነዉ።ዘንድሮ ጋምቤላ ዉስጥ መቶዎች መገደል፤ መቁሰል፤ መታገታቸዉ አስተክዞ ሳያበቃ፤ መቶዎች ሜድትራኒያን ባሕር ዉስጥ የመሰመጣቸዉ መርዶ ተሰማ።ኢትዮጵያዊዉ የመብት ተሟጋች ከሐዘን አትዉጡ የተባልን ይመስል-ይላሉ።ሙታኑን ግን እንደ አምናዉ በአደባባይ የዘከራቸዉ የለም።ሐዘን ሰልችቶን ይሆን? ወይስ ለመድነዉ?

ሜድትራኒያን ባሕር ላይ የምትቀዝፈዉ ፍራንክፉርተር አም ማይን የተሰኘችዉ የጀርመን የጦር መርከብ ዘመቻ ሶፊያ የተሰኘዉ የአዉሮጳ ሕብረት ተልዕኮ አካል ናት።የመርከቢቱ ባልደረቦች ስደተኞችን ያሳፈሩ መርከብ፤ ጀልባዎችንና ሰዉ አሸጋጋሪዎችን ለመቆጣጠር፤ አደጋ ያጋጣማቸዉን ስደተኞችን ፈጥኖ ለመርዳት ያን ግዙፍ ባሕር መዓልት-ወሌት ይጠብቃሉ።«በጣም ንቁ እና ተጠራጣሪ መሆን አለብሕ።ምክንያቱም አንዳዴ በተለይ ሌሊት እኒያን ትናንሽ ጀልባዎች አታያቸዉም።ድምፅ ግን ልትሰማ ትችላለሕ።ባካባቢያችን ትናንሾቹ ጀልባዎች መኖራቸዉን የምናዉቀዉና አስፈላጊ ከሆነም ልንረዳቸዉ የምንችለዉ፤ በሌሊቱ የአራት ሰዓት ቅኝት ቡድኑ በንቃት እንዲጠብቅ ማድረግ ስናደርግ ብቻ ነዉ።»

ይላሉ-የጓድ መሪ ማርቲን ካ.። ባለፈዉ ዓመት ከሠባት መቶ በላይ ስደተኞች ሜድትራኒያን ባሕር ላይ ካለቁ ወዲሕ የአዉሮጳ ሕብረት ሰደተኛ አሸጋጋሪዎችን የሚያድኑና ስደተኞችን ከአደጋ የሚያድኑ ያላቸዉን በርካታ መርከቦችና ጀልባዎችን ሜድትራኒያን ባሕር ላይ አስፍሯል።

ከያ-ሥምንቱ የሕብረቱ አባል ሐገራት አስራ-አራቱ ያዘመቱት የጦር መርከብና ጀልባ ፤ ጀርመናዊዉ የባሕር ሐይል መኮንን እንዳሉት፤ ነቅቶ ይጠብቃል።ኢትዮጵያዊዉ ወጣት ሙአዝ መሐመድ እና ብጤዎቹ የተሳፈሩባት ጀልባ ተበላሽታ ድፍን ሰወስት ቀን ያለ ምግብና መጠጥ ሜድትራኒያን ባሕር ላይ ከሞት ጋር ሲተናነቁ ግን የደረሰላቸዉ የለም።

ኢትዮጵያዊዉ የፖለቲካ አቀንቃኝ ጀዋር መሐመድ እንደሚሉት ስደተኞቹ ጀልባቸዉ ተበላሽታ ባሕር ላይ በነበሩበት ወቅት ርዳታ እንዲደረግላቸዉ የተለያዩ የአዉሮጳ መንግሥታት ጠረፍ ጠባቂዎችን በሥልክ ጠይቀዉ ነበር።በአራተኛዉ ቀን በሌሎች ስደተኞች የተጨናነቅች ሌላ ጀልባ ወይም መርከብ ደረሰች።እንደ ሙዓዝ ከመዓቱ ከተረፉ አርባ ስደተኞች አንዱ ሶማሊያዊዉ ወጣት ለአልጀዚራ ቴሌቪዥን እንደነገረዉ በተበላሸችዉ ጀልባ ላይ የነበሩት ስደተኞች አዲስ ወደመጣችዉ ለመዛወር ይራኮቱ ገቡ።

«ሰዎቹ አንድ በአንድ አልሔዱም።25 እና ሠላሳ የሚሆኑት እየተጣደፉ ወደ መርከቢቱ ሲሻገሩ መርከቧ ሚዛኗን ሳተች።»ከዚያ የድረሱልኝ፤ ዋይታ፤ ጩኸት፤ የመጨረሻ ሕቅታ እና እልቂት።«አይናችን እያየ ሞቱ» ይላል ሌላዉ ሶማሊያዊ ወጣት።«አምስት መቶ ሰዎች አጠገባችን ሞቱ።እናያቸዋለን።ድረሱልኝ፤ እርዱኝ ሲሉ ድምፃቸዉን እንሰማለን።»እየጮኹ፤ እያለቀሱ፤ ቁል ቁል ወደ ባሕሩ ከርስ ከወረዱ። አንዷ የሙዓዝ ባለቤት፤ ሁለተኛዉ የሁለት ወር ሕፃን ልጁ፤ ሰወስተኛዉ አማቹ ነበር።

«ሚስቴና ልጄ ሔዱ፤ ባጠቃላይ ሰወስት ቤተሰቦቼ ሞቱ።»

አንዳድ ምንጮች እንደዘገቡት በአደጋዉ ከአለቁት ስደተኞች አብዛኞቹ ኢትዮጵያዉያን ናቸዉ። ተፈጥሮም፤ ፈጣሪም፤ሰዉም፤ ዕድልም ጨከነባቸዉ። «ከሐዘን አትዉጡ የተባልን ይመስል» ይላሉ በቅርቡ የተመሠረተዉ የሰብአዊ መብት ማሕበር ለኢትዮጵያ (Association for HR in Ethiopia) ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ሐይለማርያም።

ጀዋር መሐመድ እንደሚሉት ደግሞ ከሟቾቹ 80 በመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያዉን ናቸዉ።ከኢትዮጵያዉኑ መካከል ደግሞ አብዛኞቹ የኦሮሞ ተወላጆች እና በኦሮሞዉ አመፅ ይሳተፉ የነበሩ ናቸዉ።ኢትዮጵያ ሠላምና መረጋጋት የሠፈነባት መባል ከጀመረች ሐያ-አምስት አመቷ። ከራሷ አልፋ በአካባቢዉ ሠላም ለማስፈን እጅግ ጠቃሚነቷ፤አማላይ የምጣኔ ሐብት ዕድገቷ-ሲነገር፤ ሲመሰከር ዓመታት አለፉ።ሠላም፤ ዕድገት ብልፅግናዉ በተመሰከረ ቁጥር ዜጎችዋን ለሞት ለሚያጋልጥ ስደት የሚገፋፋዉ ምክንያትም እንዳጠያየቀ ነዉ።ዛሬም ይጠየቃል።

አቶ ያሬድ ምሳሌ ጠቀስ መልስ አላቸዉ።የአፍሪቃ፤ የአዉሮጳ ይሁን የአሜሪካ መንግሥታት ብዙ ጊዜ እንደሚሉት ኢትዮጵያን የመሳሰሉ ጦርነት የማይደረግባቸዉ ሐገራት ዜጎች የሚሰደዱት ከድሕነት ለማምለጥ ነዉ፤-«የተሻለ ኑሮ ፍለጋ» በተለመደዉ ቋንቋ።እንደ ሁለተኛ ምክንያት የሚጠቀሰዉ ሰዎች በተለይ ወጣቶቹ የሚሰደዱት በሕገ-ወጥ አሸጋጋሪዎች ወይም ደላሎች እየተታሉ ነዉ-የሚለዉ መላምት ነዉ።

ሌላ ቀርቶ ስደተኞችን እንዲረዳ ተመሥርቶ የስደተኞች «ጌታ» የሆነዉ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር (UNHCR) ባለሥልጣናት ሳይቀሩ ኢትዮጵያዉያኑን ስደተኞች ብዙ ጊዜ የኢኮኖሚ እና በአሸጋጋሪ ደላሎች የተታለሉ እያለ ይፈርጃቸዋል።

ከሳምንት በፊት ሜድትራኒን ባሕር ላይ ካለቁት ስደተኞች የሚያዉቋቸዉ እንደሚሉት ብዙዎቹ፤ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፤ ወይም ከዩኒቨርስቲ ተመርቀዉ በተለያዩ ቢሮዎች ይሰሩ የነበሩ ናቸዉ።እነዚሕ ወጣቶች ኑሮ አስመርሯቸዉ ተሰደዱ ማለት ያሳስታል።እንዚሕ ወጣቶች በደላሎች ሰበካ ይታለላሉ ማለት ጅልነት ነዉ።

እንዲያዉም አቶ ያሬድ እንደሚሉት ከሟቾቹ መሐል አምና ሊቢያ ዉስጥ ስደተኛ ወገኖቻቸዉ መታረዳቸዉ በማዉገዝ አደባባይ የወጡም አሉባቸዉ።ዘንድሮ እነሱዉ ተረኛ ሆኑ።ጀዋር መሐመድ ያክሉበታል።ሰሞኑን ሜድትራኒያን ባሕር ላይ ያለቁት ኢትዮጵያዉያን አምና እንደተገደሉት የመንግሥትንም፤ የአምናዉ ሠልፍ፤ ዘመቻና ሥርዓተ-ሐዘን ያዘጋጁትን ኢትዮጵያዉያንንም ትኩረት ያልሳበበት ምክንያትም በርግጥ አነጋጋሪ ነዉ።ኢትዮጵያዉያን ወጣቶቻቸዉን ገሚሱን ለበረሐ፤ ሌላዉን ለባሕር የሚገብሩት እስከ መቼ ነዉ ብሎ ጥያቄ ደግሞ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም እየተጠየቀ ነዉ።

መልስ አልባ ጥያቄ።

የአዉሮጳ ሕብረት ለአዉሮጶች የሚሆን መልስ አለዉ።የአፍሪቃ ስደተኞች ወደ አዉሮጳ እንዳይሻገሩ ድንበሩን በጦር ሐይል ከማስጠበቅ ጋር አፍሪቃዉያን ከየሐገራቸዉ እንዳይወጡ ለኢትዮጵያ ጨምሮ ለተለያዩ የአፍሪቃ መንግሥታት ጠቅም ያለ ገንዘብ ለመስጠት ተስማምቷል።ገንዘቡ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ይዉላል ነዉ የተባለዉ።

ለአፍሪቃ በጣሙን ለኢትዮጵያ ግን፤ አቶ ያሬድ ሐይለማርያም እንደሚሉት፤ የብራስልሶች መልስ-ትክክልም፤ዘላቂም አይደለም።አቶ ጅዋር ደግሞ በተለይ ያሁኖቹ ስደተኞች መቼ ሥራ-አጡና ይሉናል።የሚያሰራ ነፃነት እንጂ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስከሬን ይቆጥራል።በድርጅቱ ዘገባ መሠረት የበቀደሙ አደጋ ከመድረሱ በፊት ከጥር ወዲሕ ብቻ ከሰባት መቶ በላይ ስደተኞች ሜድትራኒያን ባሕር ዉስጥ ሰምጠዉ ሞተዋል።የበቀደሞቹ ሲጨመሩ ቁጥራቸዉ ከ1200 ይበልጣል።ወጣቶቹ-አለቁ፤ አለፉ። ቀጣዩ ተረኛ ማን ይሆን?

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠ

Audios and videos on the topic