የስደተኞች እጣ ፈንታ በእስራኤል | ዓለም | DW | 14.03.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የስደተኞች እጣ ፈንታ በእስራኤል

የእስራኤል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ህገወጥ ስደተኞች ካለፍርድ ለሶስት ዓመታት እንዲታሠሩ መንግስት ያወጣዉን ህግ በመቃወም ላቀረቡት አቤቱታ እስከ ሚያዝያ 22ቀን 2005 ድረስ ምላሽ እንዲሰጥ ጠየቀ። በዚህ ህግ መሠረት ከታሠሩት

አብዛኞቹ ኤርትራዉያንና ሱዳናዉያን ስደተኞች ናቸዉ። እስራኤል የሲና በረሃን አቋርጠዉ ድንበሯን አልፈዉ የሚገቡ አፍሪቃዉያን ስደተኞችን ለመግታት የተለያዩ ጥረቶችን ማድረጓ እየታየ ነዉ። በተለይ ባለፈዉ ጥር ወር ለዓመታት ስትዝት ቆይታ በኤሌክትሮኒክስ የሚታገዝ አጥር ከግብፅ ጋ በሚያዋስናት ድንበር ላይ መትከሏ የጀመረችዉን ስደተኞች የማገድ ጥረት በግልፅ አመላክቷል። እስራኤል ከዉጭ የሚመጡባትን በአጥር ከመከላከል አልፋም ለፀጥታዬ ያሰጉኛል የምትላቸዉን ለማጣራት በሚል የደነገገችዉ ህግ እዚያ የገቡ ጥገኝነት ጠያቂዎቹን ለችግር መዳረጉ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎችን አሳስቧል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾቹ ፊርማ በማሰባሰብ ህጉ ጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ ያስከትላል ያሉትን ጉዳት ፍርድ ቤት እንዲያየዉ አቅርበዋል። የሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ዛሬ የእስራኤል መንግስት እስከ ሚያዝያ ወር ማለቂያ ድረስ በዚህ ላይ ምላሹን እንዲሰጥ ጠይቋል።

የእስራኤል መንግስት በጎርጎሮሳዊዉ 1954ዓ,ም ደንግጎት የነበረዉን ሰርጎገብ የአረብ ሚሊሻዎችን ለመከላከል ያለመ ህግ ከአፍሪቃ ድንበር አቋርጠዉ የሚገቡ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ቁጥር ለመቀነስ እንዲረዳ በዚሁ ወር ዳግም በምክር ቤቱ አፀድቋል። በዚህ መሠረትም ባለፉት ጥቂት ወራት ወደእስራኤል የገቡ ወደሁለት ሺህ የሚገመቱ ጥገኝነት ጠያቂዎች ታስረዋል። እስራኤል ለደህንነቷ የምትወስደዉን ርምጃ እንደማይቃወሙ የሚገልፁት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ህጉ ጥገኝነት ጠያቂዎችን እንዳያጠቃልል ጠይቀዋል።

በእስራኤል የሲቪል መብቶች ማኅበር እንደሚለዉም ከታሰሩት አብዛኞቹም የኤርትራ እና ሱዳን ዜጎች ናቸዉ። ዓለም ዓቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት ሂዉማን ራይትስ ዎች በበኩሉ ካለፈዉ ታህሳስ ወር አጋማሽ ወዲህ ብቻ በደረሰባቸዉ ጫና ተገደዉ 50 የሚሆኑ ኤርትራዉያን ስደተኞች ወደዑጋንዳ ለመሻገር መስማማታቸዉን አመልክቷል። ኤርትራዉያኑም ሆኑ ሱዳናዉያን ስደተኞች ወደሀገራቸዉ የመመለስ እጣ ቢገጥማቸዉ ለችግር ሊዳረጉ እንደሚችሉ ነዉ የተገለፀዉ። በተለይም በሱዳን ህግ እስራኤልን የጎበኘ ዜጋ እስከ አስር ዓመት በሚደርስ እስራት እንደሚቀጣ ተደንግጓል።

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic