1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አወዛጋቢው የኢጣልያ እርምጃ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 14 2011

የኢጣልያ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ማቴዮ ሳልቪኒ 27 ህጻናት ስደተኞች ብቻ እንዲገቡ በመፍቀድ የተቀሩት ወደ ስፓኝ ይሂዱ በሚለው ግትር አቋማቸው መጽናታቸው ግራ እንዳጋባ ነው።በዚህ መካከል መርከቧ ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ለመቆየት የተገደዱት ስደተኞች ለተለያዩ አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ችግሮች መዳረጋቸውን  የመርከቧ ሠራተኞች ይናገራሉ።

https://p.dw.com/p/3OE6V
Italien Rettungsschiff Open Arms vor Lampedusa
ምስል picture-alliance/dpa/F. Bungert

ስደተኞች እና አወዛጋቢው የኢጣልያ እርምጃ

ስደተኞችን ከመስጠም አድኖ ባለፈው ሳምንት የኢጣልያዋ ደሴት ላምፔዱዛ አቅራቢያ መልህቁን የጣለው «ኦፕን አርምስ» የተባለው የስፓኝ የእርዳታ ድርጅት መርከብ ጉዳይ ማወዛገቡ ቀጥሏል።ምንም እንኳን 6 የአውሮጳ ሃገራት ስደተኞቹን ለመቀበል ፈቃደኝነታቸውን ቢያሳውቁም ከመርከቡ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘው ኢጣልያ ግን ዛሬም እንደጨከነችባቸው ነው።ስፓኝ ለመርከቧ ማረፊያ ሁለት አማራጭ ወደቦችን ብትፈቅድም ባለቤቶቿ በርቀታቸው ምክንያት አልተስማሙም።በዚህ መሀል መርከቧ የጫነቻቸው ስደተኞች እየተንገላቱ ነው።
ከሊቢያ የባህር ዳርቻ ከተነሱ ቀናት አልፈዋል፤የሜዴትራንያንን ባህር አቋርጠው አውሮጳ መድረስ ዋነኛው ዓላማቸው ነበር።በአነስተኛ እና ለንቋሳ ጀልባ ሲጓዙ ፣የአውሮጳ ደቡባዊ ድንበር በሆነችው በኢጣልያ የውሐ ክልል አቅራቢያ ፣በስፓኝ በጎ አድራጊ ድርጅት መርከብ ከመስጠም የዳኑት አፍሪቃውያን ስደተኞች።እነዚሁ ስደተኞች በስፓኙ«ፕሮአክቲቫ ኦፕን አርምስ »በተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት ስር በሚንቀሳቀሰው «ኦፕን አርምስ» መርከብ ላይ መዋል ማደር ከጀመሩ ዛሬ 19 ቀን ሆናቸው።ባለፈው ሳምንት መርከቢቱ በኢጣልያዋ ደሴት ላምፔዱዛ አቅራቢያ መልህቅዋን እንድትጥል ኢጣልያ መፍቀዷ፣6 የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራትም ስደተኞቹን ለመውሰድ ፈቃደኝነታቸውን መግለፃቸው ሲሰማ ለጊዜውም ቢሆን እፎይታ አስገኝቶ ነበር።ይሁን እና የኢጣልያ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ማቴዮ ሳልቪኒ 27 ህጻናት ስደተኞች ብቻ እንዲገቡ በመፍቀድ የተቀሩት ወደ ስፓኝ ይሂዱ በሚለው ግትር አቋማቸው መጽናታቸው ግራ እንዳጋባ ነው።በዚህ መካከል መርከቧ ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ለመቆየት የተገደዱት ስደተኞች ለተለያዩ አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ችግሮች መዳረጋቸውን  የመርከቧ ሠራተኞች ይናገራሉ።የኦፕን አርምስ መርከብ የባላይ ሃላፊ አናቤል ሞንትስሚር ትናንት እንዳሉት ጭንቀት እና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ያሉት ደግሞ ራሳቸውን ወደ ባህር እየወረሩ ነው። 
«ዛሬ ነሐሴ 13 ነው።ያ ማለት ባህር ላይ 18 ቀናት ሆነን ማለት ነው።ስደተኞቹ የትውልድ ስፍራቸውን ለቀው ብዙ ውጣ ውረድ አሳልፈው ፣በባህር ላይ ህይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው ከጭካኔም ተርፈው እዚህ ከደርሱ 19 ቀናት ሆነ።በዚህ ጊዜ ውስጥም ያልሆነ ነገር የለም።ከባድ ማዕበል፣ራስ ምታት ማስመለስ፣አለመረጋጋት፣ፍርሃት ስጋት ድንጋጤ ውጥረት ደርሶ አይተናል።ተስፋ ቆርጠው ራሳቸውን ወደ ባህር የወረወሩም አሉ።ከዚህ ሌላ ምን እንዲሆን ትፈልጋላችሁ? ምን ሊሆንስ ይችላል?»
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባህር ዘለው ከገቡት ሌላ ዛሬም ሌሎች ስደተኞች ተመሳሳይ ሙከራ ማድረጋቸውን ኦፕን አርምስ አስታውቋል።አውሮጳ መድረስ ተመኝተው ጫፍዋ የተጠጉትን ኦፕን አርምስ መርከብ ውስጥ ተፋፍገው ለሚገኙ 107 ስደተኞች ኢጣልያ አፈሯን የመርገጥ እድል አልሰጠቻቸውም።የኢጣልያ ጭካኔ ሲበረታ ስፓኝ ብትርቅም መርከቧን ፣ወደቦቿ ለማሳረፍ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ እሺታዋን ገለጻ ነበር።በመጀመሪያ ደቡብ ምዕራብ ወደቧ አልጀሲራስን ነበር የፈቀደችው።የመርከቧ ባለቤት «ፕሮአክቲቫ ኦፕን አርምስ» እጅግ ሩቅ ነው ሲል ሳይቀበለው ቀርቷል።ስፓኝ በዚህ ሳትወሰን ሌላ አማራጭም አቅርባ ነበር። ከላምፔዱዛ በስተምዕራብ አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደ ሚገኘው ማዮካ እንዲሄድ።ይህ አማራጭም በፕሮአክቲቫ ተቀባይነት አላገኘም።ግብረ ሰናዩ ድርጅት በዋና ሊደረስ በሚችል ርቀት ላይ ያለችው ኢጣልያ አጠገብ ሆነን ለምን በአስቸጋሪ የአየር ጸባይ ቀናት የሚወስድ ጉዞ እናደርጋለን ሲል ሞግቷል።የኦፕን አርምስ መርከብ የባላይ ሃላፊ አናቤል ሞንትስሚር ጉዞው አስቸጋሪ ለስደተኞቹ ከባድ እንደሚሆን አሳስበው ስደተኞቹ በሰብዓዊነት ኢጣልያ እንዲገቡ እንዲፈቀድላቸው ጥሪ አቅርበዋል። 
«አሁን በሰብዓዊ ደረጃ ጥሪ አቀርባለሁ፤ስለ ህጋዊው ጉዳይ አይደለም የምናገረው።እነዚህ ሰዎች በሙሉ ደህንነቱ በተጠበቀው 800 ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ወደብ ነው መውረድ ያለባቸው።ከ19 ቀናት በኋላ ከነዚህ ሰዎች ጋር ተጨማሪ 5 ቀናት በመርከብ ተጓዙ ነው የምትሉን?በሰብዓዊነት ጥሪ አቀርባለሁ።ተጨማሪ 5 ቀናት መቆየት አይችሉም። መሬት መርገጥ አለባቸው።ሰዎች ናቸው።»
ኦፕን አርምስ ይህን ሰብዓዊ ጥሪውን ቢያስተላልፍም ኢጣልያ በእምቢተኝነቷ እንደጸናች ነው።የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ ማቴዮ ሳልቪኒ ስደተኞቹ ላምፔዱዛ እንዳይወርዱ ለምን እምቢ ይላሉ  ተብለው ሲጠየቁ ሞኝ መሰልናችሁ ወይ ሲሉ ነበር የመለሱት።  
«በፍጹም አልፈቅድም።ይገርመኛል ሁሉም ለምን ኢጣልያ፣ኢጣልያ ብቻ እንደሚሉ፤የፈረንሳይ የስፖኝ ጀርመን ኖርዌይ የእንግሊዝ የስፓኝ ወደቦች ክፍት ናቸው ጥሩ እና ደጎች ናቸው።ሆኖም የለም ሁሉንም ህጻናት ያልሆኑ ህጻናቶች ያልታመሙ ተመዋል እያሉ ኢጣልያ ያመጣሉ።ጥሩዎች ነን ቸር  ክርስቲያንም ነን። ግን ሞኞች አይደለንም»
ሳልቪኒ ኦፕን አርምስ የስፓኝ ወደቦች ላለመሄድ ርቀታቸውን ምክንያት ማድረጉንም አልተቀበሉም።  
«ባህር ላይ 18 ቀናት ለቆየው ለዚህ የስፓኝ መርከብ ስፓኝ ክፍት ወደብ አላት።ለምን ስፓኝ አይሄዱም?ጠርቻሁ አናግሯቸው ለምን ስፓኝ እንደማይሄዱ። ምክንያቱ ይህ የፖለቲካ ትግል ነው።ታውቃለህ 18 ቀናት ኢቢዛ እና ፎርሜንታራ ቢያንስ 3 ጊዜ ሄደው መመለስ ይችሉ ነበር።» 
ሁለት ወደቦቿን ሜዴትራንያን ባህር ላይ ለ19 ቀናት ለመቆም ለተገደደው ለኦፕን አርምስ መርከብ ክፍት ማድረጓን ያሳወቀችው ስፓኝ  ስደተኞቹ ኢጣልያ እንዳይገቡ በጽኑ የከለከሉትን ማትዮ ሳልቪኒን በእጅጉ ኮንናለች።የስፓኝ ተጠባባቂ መከላከያ ሚኒስትር ማርጋሬታ ሮቤልስ የሳልቪኒን እርምጃ አሳፋሪ ብለውታል።
«ኦፕን አርምስን በተመለከተ ማለት የምችለው የተለያዩ የአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት ኦፕን አርምስ መርከብ ላይ የሚገኙትን ስደተኞች ለመቀበል ከተስማሙ እና የኢጣልያም ፍርድ ቤቶች መርከቧ በኢጣልያ ወደቦች ሰዎቹን እንድታወርድ ከወሰኑ በኋላ ሚስተር ሳልቪኒ በተለይ ለምርጫ ምክንያታቸው ሲሉ በጣም ቀላሉን የአውሮጳ ህብረትን የጋራ አሰራር ጥሰዋል።በዚህም የሰዎችን ህይወት ለአደጋ አጋልጠዋል።እንደሚመስለኝ ሳልቪኒ በኦፕን አርምስ ላይ የፈጸሙት ለሰብዓዊ ፍጡር በአጠቃላይ አሳፋሪ ነው።»
መርከቧም ሆነች ስደተኞቹ ስፓኝ መሄድ አይችሉም ያለው ኦፕን አርምስ ከዚህ ቀደም ጀርመናዊቲ የመርከብ ካፕቴን እንዳደረገችው የላምፔዱዛን ኬላ በኃይል ጥሶ ማለፍ ምናልባት የመጨረሻው አማራጭ ሊሆን ይችላል እስከ ማለት ደርሶም ነበር ።107 ስደተኞችን ያሳፈረችው የስፓኙ የኦፕን አርምስ መርከብ ኢጣልያ ወደብ ላምፔዱዛ እንዳትደርስ መከልከሏን ክፉኛ ከተቹት መካከል የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን በምህጻሩ UNHCR ይገኝበታል።የድርጅቱ ቃል አቀባይ አንድሬ ማሄኪክ ችግሩ እዚህ ደረጃ ሊደርስ ባልተገባም ነበር ሲሉ ወቅሰዋል።
«ከመስጠም የዳኑ ሰዎች የፖለቲካ ነጥብ ለማስመዝገብ ለማግኘት ሲባል ሊታገቱ አይገባም።አሁን ሁኔታው አሳዛኝ ነው።እዚህ ደረጃ ላይ ሊደርስም አይገባም።ከመስጠም የዳኑት ሰዎች ለበርካታ ወራት ሊቢያ በቆዩበት ወቅት አሰቃቂ በደሎች ተፈጽመውባቸዋል።6 የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት እነርሱ ከመርከቢቱ ከወረዱ በኋላ ለመቀበል ፈቃደኝነታቸውን ገልጸዋል።አሁን ቀላሉ ነገር እነርሱን በደህንነት ወደ የብስ ማምጣት ነው። »
ስደተኞችን አላስገባም በማለታቸው ትችት የተፈራረቀባቸው ሳልቪኒ ዛሬ ማምሻውን ሥልጣናቸውን እንደሚለቁ ካሳወቁት ከኢጣልያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴም በኩል ሌላ ወቀሳ ቀርቦባቸዋል።በፖለቲካ ቀውስ ውስጥ የምትገኘው የኢጣልያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኮንቴ ዛሬ ለኢጣልያ ምክር ቤት ሥልጣን የሚለቁት የተጣማሪው መንግሥት አካል የሆነው የቀኝ ክንፉ የሊግ ፓርቲ መሪ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማትዮ ሳልቪኒ ጥምረቱን በማኮሰሳቸው እና ለግል የፖለቲካ ጥቅማቸው ሲሉ የሃገሪቱን ምጣኔ ሃብት አደጋ ላይ በመጣላቸው ነው ብለዋል።ውሳኔዎቻቸውም ሃገሪቱን አደጋ ላይ እየጣሉ የፖለቲካ እና የፋይናንስ አለመረጋጋትንም ሊያስከትሉ የሚችሉ ናቸው ሲሉም በምሬት ተናግረዋል።ኢጣልያን የሚመሩት ተጣማሪ ፓርቲዎች አባል ያልሆኑት ኮንቴ ዛሬ ማምሻውን የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ለሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ሰርጂዮ ማታሬላ ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።ማታሬላም ኮንቴ በሥልጣናቸው ላይ እንዲቆዩ ይጠይቋቸዋል ተብሎ ይገመታል።ወይም መልቀቂያቸውን ተቀብለው ሌላ መሪ አማራጭ ጥምረት ይዞ መቅረብ መቻል አለመቻሉን ይመረምራሉ።ይህ ሁሉ ካልተሳካ ግን ማታሬላ ፓርላማውን በትነው የፊታችን ጥቅምት አጠቃላይ ምርጫ ይጠራሉ ተብሎ ይጠበቃል።የኢጣልያ የፖለቲካ ቀውስ እዚህ ደረጃ ላይ በደረሰበት በዛሬው እለት ከዚህ ቀደም ስደተኞችን ለጫነው ለኦፕን አርምስ አጃቢ መርከብም እልካለሁ ያለችው ስፓኝ አዲስ ተስፋ ሰጥታለች። ስደተኞቹን አሳፍራ የምትወስድበት የባህር ኃይል ተቆጣጣሪ ጀልባ ማምሻውን ወደ ላምፔዱዛ ልትልክ መሆኑ ተሰምቷል። ጀልባው ከ3 ቀናት ጉዞ በኋላ ላምፔዱዛ ይደርሳል ተብሏል። ይህ ለስደተኞቹ የመጨረሻው አማራጭ መፍትሄ ይሆን?አብረን የምናየው ይሆናል።

Italien Premierminister Giuseppe Conte im Oberhaus
ምስል picture-alliance/AP Photo/G. Borgia
Italien Lampedusa | Rettungsschiff Open Arms | Ankunft Minderjährige
ምስል Reuters/G. Mangiapane
Italien Lampedusa | Rettungsschiff Open Arms | Ankunft Minderjährige
ምስል Reuters/G. Mangiapane
Italien Rettungsschiff Open Arms vor Lampedusa
ምስል picture-alliance/dpa/F. Bungert

ኂሩት መለሰ 

አዜብ ታደሰ