የስደተኞች አቀባበል በአፍሪቃ | አፍሪቃ | DW | 20.05.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የስደተኞች አቀባበል በአፍሪቃ

ዓለም አቀፉ የሰዉ መብት ተከራካሪ አምነስት ኢንቴርናሽናል ስደተኞች ስለመቀበል የሚያመለክተዉን Refugees Welcome Index ይፋ ሲያደርግ የመጀመሪያ ነዉ። ጥናቱን ያከናወነዉ GlobeScan የተባለዉ ነፃ የስልት አማካሪ ተቋም ሲሆን፣ በጥናቱ መንግሥታት ስደትን በሚመለከት የያዙት መመሪያ ዜጎች ከያዙት አቋም ጋር እንደማይመጣጠን ያትታል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:09

ስደተኞችን ማስተናገድ

ከአፍሪቃ አራት አገሮች በጥናቱ ተካተዋል። የአገራቱ ዜጎችም ስድተኞችን በአገራቸዉ፣ በከተሞቻቸዉ፣ በጎረቤቶቻቸዉ እና በቤታቸዉ ተቀብለዉ ለማስተናገድ ፍቃደኛ መሆናቸዉንም ያሳያል። ለምሳሌ በናይጄርያ 85 በመቶ በጥናቱ የተሳተፉት ሰዎች በጦርነት፣ በሃይማኖት፣ በዘር ወይም በፖለቲካ ምክንያት ከተቃጣባቸዉ ግድያ የሚሸሹትን እንደሚቀበሉ፣ መንግሥታቸም ስደተኞችን እንደሚረዳ፤ በተመሰሳይም በኬንያ 65 በመቶዉ ሕዝብ ስደተኞችን እጁን ዘርግቶ እንደሚቀበል ጥናቱ ያትታል።


ይህ ቁጥር የሚያሳየዉ ስድተኞችን የሚያጥላላ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ከኅብረተሰቡ አስተያየት ጋር እንደሚጋጭ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዋና ጸሐፊ ሳሊሊ ሼት ይናገራሉ። <<ኅብረተሰቡ ስድተኞችን ለመቀበል ዝግጁ ነዉ፣ ይሁን እንጂ የስድተኞችን ቀዉስ በተመለከተ መንግሥታት የሚሰጡት ምላሽ ዜጎች ከያዙት አቋም ጋር አይሄድም፥>> ይላሉ ዋና ጸሐፊዉ።


ባሳለፍነዉ ሳምንት የኬንያ መንግስት ዳዳብን ጨምሮ ሌሎች የስድተኞች መጠለያ በገንዘብ እና በደንነት ምክንያት ለመዝጋት ማቀዱ ተናግሯል። ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብም የሰብአዊ ርዳታ ለስደተኞቹ ለማድረግ ኃላፍነቱን እንዲወስድም አሳስቦ ነበር። አምነስቲ ኢንተርናሽናል የኬንያ ጽሕፈት ቤት ቪክቶር ኛሞር የኬንያን አቅም እንዲህ ይተቻሉ፣ <<ሰዎች ለሰዎች ጠንካራ ስሜት አላቸዉ። ስድተኞቹ ከሀገራቸዉ ተሰደዉ መጠጊያ የሚፈልጉ ከሆነ እንደሰብዓዊ ፍጡር ይህ ይሰማናል። ይሁን እንጂ እጅግ ጥቂት ሰዎች ሊቃወሙ ይችላሉ። ኬንያን ካየን 62 በመቶ የሚሆነዉ ሕዝብ መንግሥት ለስድተኞቹ ከለላ እንዲሰጥ ይጠይቃሉ። ያም ሆኖ ግን የተወሰኑ ሰዎች እና ፖለቲከኞች ደግሞ ስለስድተኞች አሉታዊ ንግግር ሲያሰሙ ይታያል፤ ይህ ደግሞ ትክክል አይደለም። መንግሥት ስለፀጥታ ጉዳይ ይናገራል፤ ስድተኞች የደህንነት ስጋት መሆናቸዉን የሚያሳይ ማስረጃ ግን የላቸዉም።>>


ደቡብ አፍሪቃ በዚህ ጥናት የተካተተች ሲሆን መንግሥታት የስደተኞችን ፍራቻ በማኅበረሰቡ ቢፈጥሩም አብዛኛዉ ዜጎች ስደተኞችን ተቀብለዉ እንደሚያስተግዱ ዋና ጸሐፊዋ ሼት ጠቁመዋል። ቪክቶርም ጥናቱ ይላሉ፣ <<ደቡብ አፍቃን ብንወስድ ወደ 24 በመቶ የሚሆኑ ዜጎች ጦርነት እና ክስን ሸሽተዉ ለተሰደዱ ወገኖች ከለላ ለመስጠት ሀገራቸዉ የተሻለ ማድረግ እንዳለባት ያሳስባሉ። በዚያም ላይ 41 በመቶዎቹ በዚህ ጉዳይከመንግሥት ጋር ይስማማሉ። ይሁን እንጂ 16 በመቶ የሚሆኑት ሀገራቸዉ ስደተኞችን መቀበሏን አጥብቀዉ እንደሚቃወሙ ጥናቱ ያመለክታል።»


ሰሞኑን የተመ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን UNHCR እንዳመለከተዉ በተለያዩ ሃገራት የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጥገኝነት ፋላጊ ስደተኞች በቂ ገንዘብ ባለመኖሩ ጎዳናዎች ላይ መኖር ተገደዋል። ድርጅቱ «ማንም ዉጭ አይጣልም» በሚል በጀመረዉ ዓለም አቀፍ ዘመቻም እንደ ሊባኖስ፣ ሜክሲኮ እና ታንዛኒያ ባሉ ሃገራት በቂ መጠለያ ለሌላቸዉ ስደተኞች መርጃ የሚሆን ገንዘብ ለማሰባሰብ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ተሰምቷል።

ታንዛኒያ ዉስጥ የኪጎማ ነዋሪ የሆነችዉ ዲያና ሩባንጉካ በአገሯ ስላለዉ የስደተኞች አቀባበል እንዲህ ትላለች፣ <<እኔ የምለዉ ስደተኞችን በቤቴ ወይም በከተማዬ አልቀበልም አይደለም። ነገር ግን ሕጋችን እነሱ ካልተመዘገቡ በስተቀር ከእኛ ጋር እንዲኖሩ አይፈቅድም። ሆኖም አንድ ስደተኛ መስፈርቱን ካሟላ ልቀበለዉ ወይም ልቀበላት ዝግጁ ነኝ። ይህን እንደ ችግር አላየዉም፣ ምክንያቱም ወደ እኛ የመጡት በአገራቸዉ በገጠማቸዉ ችግር ምክንያት ነዉ።>>

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic