የስደተኞች ችግር እና የ«ዩኤንኤችሲአር» ጥሪ | አፍሪቃ | DW | 30.08.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የስደተኞች ችግር እና የ«ዩኤንኤችሲአር» ጥሪ

በጀልባ ወደ አውሮጳ የሚገቡ አፍሪቃውያን ስደተኞችን ችግር ለማቃለል የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች መስሪያ ቤት ለአውሮጳ ኅብረት ጥሪ አቅርቦዋል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች፣ ብዙ አፍሪቃውያን ጭምር በያመቱ ኢጣልያ የባህር ጠረፍ ይደርሳሉ። በየሀገሮቻቸው በፖለቲካ አመለካከታቸው፣ በሀይማኖታቸው ሰበብ የሚደርስባቸውን ክትትል ለማምለጥ ወይም የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ሀገር ለቀው የወጡ ናቸው። የተስፋ ምድር አድርገው ወደሚመለከቷት አውሮጳ በሕገ ወጥ ሰው አሸጋጋሪ ቡድኖች አማካኝነት በሜድትሬንያን ባህር በኩል የሚደርሱበትን ዕቅዳቸውን ለማሳካት በሚያደርጉት ሙከራ ወቅት ብዙዎች ሕይወታቸውን እስከማጣት ደርሰዋል። ባለፈው ሳምንት ብቻ እንኳን ከ300 የሚበልጡ ሰጥመው መሞታቸውን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች መስሪያ ቤት ፣«ዩኤንኤችሲአር» አስታውቋል። በድርጅቱ ዘገባ መሠረት ፣ የአውሮጳውያኑ 2014 ዓም ከገባ ወዲህ በአደገኛው የባህር ጉዞ ከሰሜን አፍሪቃ ሀገራት፣ በተለይ ፣ ከሊቢያ ወደ አውሮጳ ለመግባት ከሞከሩት መካከል 1,900 አፍሪቃውያን የሚጠጉ ሰጥመዋል፣ ከነዚህም መካከል 1,600 ዎቹ የሞቱት ካለፈው ሰኔ ወር ወዲህ ነው።r

ይህ አሳሳቢ ችግር አስቸኳይ መፍትሔ እንደሚያሻው እና አውሮጳውያቱ ሀገራት በሜድትሬንያን ባህር አካባቢ ሀገራትን ለገጠማቸው አሳሳቢው የሰዎች ፍልሰት ችግር መፍትሔ እንዲያፈላልጉ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች መስሪያ ቤት ፣«ዩኤንኤችሲአር» አሳስቦዋል። በሜድትራንያን ባህር ተገን ፈላጊዎች የመስጠም አደጋ እንዳያጋጥማቸው ርዳታ የሚሰጠው «ማሬ ኖስትሮም » ወይም በዘረፋ ትርጉሙ የእኛ ባህር የተሰኘው የኢጣልያ ባህር ኃይል የሚያካሂደውን ተልዕኮ የ«ዩኤንኤችሲአር» ቃል አቀባይ ፍሌሚንግ አሞግሰው ፣ሌሎቹ የኅብረቱ ሀገራት ተልዕኮውን እንዲረዱ ጠይቀዋል።

«አንዳንዶቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊፈፀሙ የሚችሉ ፣ በመጀመሪያ ደረጃ የስደተኞቹን ሕይወት ለማትረፍ የሚረዱ ናቸው። እንደምናየው፣ በየጊዜው ቁጥራቸው በመጨመር ላይ የሚገኙ ግራ የተጋቡ ሰዎች አደገኛውን ጉዞ እያመረጡ ነው። በሰበቡም ብዙዎች ይሞታሉ ። ምንም እንኳን የኢጣልያ ባህር ኃይል የሚደነቅ የማዳን ስራ በማድረግ ላይ ቢገኝም፣ በዚህ ዓመት ብቻ 1,800 ሰው ነው ሜድትሬንያን ባህር ውስጥ ሰጥሞ የቀረው። እና የአውሮጳ ኅብረት ሀገራት የወንዶች፣ ሴቶች እና ሕፃናትን ሞት ለማብቃት ይቻል ዘንድ ኢጣልያን በጀመረችው የስው ሕይወት የማዳን ተግባር ላይ እንዲረዱዋት ጥሪ አቅርበናል። »

«ዩኤንኤችሲአር» እንዳስታወቀው፣ ባለፉት ስምንት ወራት 108,000 የጀልባ ስደተኞች ኢጣልያ ሲገቡ፣ ብዙዎቹን «ማሬ ኖስትሩም» ነበር ከመስመጥ ያዳናቸው።

የስደተኞቹ ጉዳይ ተመልካች መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ፍሌሚንግ እንደሚሉት፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለስደተኞቹ መሰደድ ምክንያት በዚያው በሚነሱባቸው ሀገራት መፍትሔ ሊያፈላልግ ይገባል።

« የችግሩን መንሥዔ ምንጭ መመልከት ይኖርብናል። እነዚህ ስደተኞች በሚመጡባቸው ሀገራት ውስጥ ፈላጭ ቆራጩ ሥርዓት ወይም ውዝግብ እስካለ ድረስ ሰዎች መሸሻቸው አይቀርም። በግልጽ እንደሚታወቀው፣ ዓለም ይህን ሁኔታ ለመቀየር የሚቻለውን ሁሉ እንዲያደርግ ጠይቀናል። ይሁንና፣ ብዙዎቹ ስደተኞች ጉዞው ምን ያህል አደገኛ መሆኑን አሁንም አልተገነዘቡትም። በጨካኞቹ ሰው አሸጋጋሪዎች ፕሮፓጋንዳ እየተታለሉ ነው። በመሆኑም አውሮጳ ለመግባት የሚፈልጉት ስደተኞች ለአደገኛው ጉዞ መተላለፊያ ባደረጉዋቸው መነሻ ቦታዎች ውስጥ ይህንን ሁኔታ ለመቀየር እየሰራን ነው። ስደተኞች ሕይወታቸውን አደጋ ላይ የማይጥሉበትን አማራጭ ለማቅረብ እንሞክራለን። »

ስደተኞቹን ከሞት ለመታደግ የሚያስችል አማራጭ በማቅረቡ ተግባር ላይ አውሮጳውያቱ ሀገራት ድርሻ ሊያበረክቱ እንደሚችሉ ነው ሜሊሳ ፍሌሚንግ ያመለከቱት።

« ስደተኞች በሕይወት ጀርመን ወይም ኔዘርላንድስ ወይም ስዊድንን ወደመሳሰሉ ሀገራት መድረስ ከተሳካላቸው በዚያ ተገን ሊጠይቁ ይችላሉ፣ በተለይ፣ ጦርነት ከሚካሄድባቸው ወይም ክትትል ከበዛባቸው ሀገራት የሚመጡት ማመልከቻቸው ተቀባይነት ሊያገኝላቸው ይችላል። ችግሩ ግን እዚያ መድረሱ ላይ ነው፣ ስለዚህ፣ አውሮጳ ስደተኞቹ ሕይወታቸውን ለአደጋ ሳያጋልጡ እዚያ መድረስ የሚችሉበትን አማራጭ እንድታፈላልግ ጠይቀናል። ብዙዎቹ ስደተኞች አውሮጳ ውስጥ ዘመድ ስላላቸው የአውሮጳ ሀገራት የቤተሰብ ማገናኘት ስራ ሊሰሩ፣ ብሎም፣ በቤተሰብ ማገናኘቱ የምትቀበለውን የውጭ ዜጎች ኮታን ወይም ድርሻን ከፍ ሊያደርጉት እና ስደተኞቹን በሌሎች የዓለም ክፍላት ከሚገኙ ዘመዶቻቸው ጋ ሊገናኙ የሚችሉበትን ዕድል ሊከፍቱ ይችላሉ። ስለዚህ በዚሁ ረገድ አንድ ነገር መታሰብ ይኖርበታል፣ ምክንያቱም ብዙ ሰው ሲሞት እያየን ነው። »

እርግጥ፣ አውሮጳውያት ሀገራት ስደተኞችን እና ተፈናቃዮችን ለመቀበል እና ለመርዳት ብዙ እያደረጉ መሆኑን ፍሌሚንግ ቢያስታውቁም፣ በዓለም ውዝግብ እየተበራከተ በመሄዱ የሚደረገው ርዳታ በቂ እንዳልሆነ ሳያመለክቱ አላለፉም። እንደሚታወቀው፣ በአሁኑ ጊዜ በዓለም በግዳጅ የተፈናቀለው ሰው ቁጥር 50 ሚልዮን ደርሶዋል፣ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወዲህ ይህን ያህል ሲፈናቀል ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ነው። ይሁናና፣ አፍሪቃውያን ስደተኞች አደገኛውን የባህር ጉዞ ከመጀመራቸውም በፊት መተላለፊያ ባደረጉዋቸው ሱዳን፣ የመን ወይም በተለይ ውጊያ በቀጠለባት ሊቢያን በመሳሰሉ ሀገራት የመከራ ሕይወት በማሳለፍ ላይ መሆናቸውን እና የተመድ መስሪያ ቤት አስፈላጊውን ርዳታ እንደማያገኙ በማስታወቅ በየጊዜው ይወቅሳሉ። ይሁንና፣ «ዩኤንኤችሲአር» በተለይ የሊቢያ የፀጥታ ችግር በመባባሱ ስደተኞቹን እንደሚፈለገው የመርዳቱ ስራ እንደከበደው ሜሊሳ ፍሌሚንግ አመልክተዋል።

« በብዙዎቹ ሀገራት ለሚገኙት ስደተኞች መጠለያ እንሰጣለን። ከዚህ በተጨማሪም፣ ለምሳሌ፣ በሊቢያ ከመስሪያ ቤታችን ጋ ግንኙነት ያደረጉ ተገን ጠያቂዎችን ለመርዳት እና ምክር ለመስጠት እንሞክራለን። እንደሚታወቀው ፣ ብዙዎቹ ሱዳን ወይም ሊቢያን ወደመሳሰሉት ሀገራት የሄዱት በፍላጎት አይደለም። ሌላ አማራጭ ስላልነበራቸው ብዙዎች ሊቢያን የመጀመሪያዋ መሸጋገሪያ ሀገር አድርገዋል። ወደ አውሮጳ ለመሄድ የሚፈልጉት እነዚሁ ስደተኞች ግን፣ በተለይ፣ ባለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ውዝግቡ ከተባባሰ ወዲህ ሊቢያን ለቀው ለመውጣት እየሞከሩ ነው። ይሁንና፣ በውዝግቡ የተነሳ ብዙ ስደተኞች መላወሻ አጥተዋል። ውዝግብ በቀጠለባቸው አካባቢ ስደተኞች ባሉበት ቦታ እንዲቆዩ ምክር መስጠቱ ለኛም አዳጋች ሆኖብናል። »

የአውሮጳ ኅብረት የጀልባ ስደተኞችን በመርዳቱ ተግባር ላይ ተጨማሪ ርምጃ እንዲወስድ የተመ የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች መስሪያ ቤት ሀሳብ ካቀረበ በኋላ ሰሞኑን ባደረገው ምክክር ስደተኞች በአውሮጳ በተለይ የመጀመሪያ ያደረጉዋት ኢጣልያ ከኅብረቱ ድጋፍ እንደምታገኝ የኅብረቱ ሀገር አስተዳደር ጉዳይ ኮሚሽነር ሴሲል ማልስትሮም አስታውቀዋል። በዚሁ መሠረት፣ የአውሮጳ ኅብረት ድንበር ጠባቂ ጋድ፣ በምሕፃሩ የ«ፍሮንቴክስ» ን ተልዕኮ በማጠናከር ጓዱ የ«ማሬ ኖስትሩም»ን ተግባር እንዲረዳ ተወስኖዋል። ይኸው የተጠናከረው ተልዕኮም በአባል ሀገራት መዋጮ ላይ ጥገኛ ይሆናል።

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic