የስደተኞች ብዛትና የባህር ላይ እልቂት | አፍሪቃ | DW | 09.12.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የስደተኞች ብዛትና የባህር ላይ እልቂት

ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ቅዳሜ በአል-ማካ የወደብ ከተማ አካባቢ ስደተኞችን የጫነች ጀልባ መስመጧን እና 70 ኢትዮጵያውያን መሞታቸውን የየመን አገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በድረ-ገፁ አስታውቆ ነበር። ይህ መረጃ እስካሁን አልተረጋገጠም

default

ከየመን የወደብ ከተማ አቅራቢያ ስደተኞችን ባሳፈረ ጀልባ ላይ በደረሰ አደጋ ቢያንስ 21 ሰዎች ሞቱ። በዚሁ በየመን ወደብ አካባቢ በዓመቱ በባህር ላይ የሞቱ ስደተኞች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ማሻቀቡን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን አስታውቋል። እሸቴ በቀለ ተጨማሪ አለው።

ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ቅዳሜ በአል-ማካ የወደብ ከተማ አካባቢ ስደተኞችን የጫነች ጀልባ መስመጧን እና 70 ኢትዮጵያውያን መሞታቸውን የየመን አገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በድረ-ገፁ አስታውቆ ነበር። ይህ መረጃ እስካሁን አልተረጋገጠም። በጀልባዋ የተሳፈሩ ሰዎች ብዛት ባይታወቅም እስካሁን 21 ሰዎች መሞታቸውን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን የየመን ቢሮ ቃል-አቀባይ ዛይድ አል-አሊያ ተናግረዋል።

«በታኢዝ አል-ማካ ወደብ አቅራቢያ በየመን የባህር ክልል ውስጥ አንድ ጀልባ በመስመጧ ወደ 21 የሚደርሱ ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸውን በአካባቢው ከሚሰሩ አጋሮቻችን አረጋግጠናል። የሞቱት ሰዎች 70 ሳይሆኑ 21 ናቸው። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን አሁን ያለን ቁጥር ይህ ነው። በጀልባዋ ላይ ስንት ሰዎች ተሳፍረው እንደነበር በትክክል አናውቅም። አሁንም ጉዳዩን እየተከታተልን ነው።»

ዛይድ አል-አሊያ በባህር ላይ ህይወታቸውን ያጡት 21 ስደተኞች ዜግነት አሁን አለመታወቁን ነገር ግን ከጅቡቲ ወደብ የተነሱ የኢትዮጵያ፤ሶማሊያ እና ኤርትራ ስደተኞች ሊሆኑ እንደሚችሉ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ወደ አረብ ሃገራት የሚሄዱ ሰራተኞች ላይ የሚደርሰውን ችግርና እንግልት ለማስቀረት ጉዞውን በጊዜያዊነት ብታግድም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስራ ፈላጊዎች በህገ-ወጥ መንገድ ወደ የመን እየተጓዙ መሆኑን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን በጥቅምት ወር ባወጣው ዘገባ አስታውቋል። ይኸው ተቋም ባወጣው ዘገባ በዚህ ዓመት መስከረም ወር ብቻ ከ12,700 በላይ ስደተኞች በጀልባ የመን እንደገቡ ገልጿል።አብዛኞቹ ደግሞ ድርቅ፤የርስ በርስ ግጭትን የሚሸሹ እንዲሁም የተሻለ የኑሮ ሁኔታ የሚፈልጉ የሶማሊያ፤ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ዜጎች ናቸው።ይህ የጀልባ ጉዞ ግን አልጋ ባልጋ አይደለም። በአነስተኛ ጀልባዎች የኤደን ባህረሰላጤን በማቋረጥ የመን ለመግባት በሚሞክሩ ስደተኞች ላይ የሚከሰተው አደጋና ሞት በዚህ ዓመት በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ዛይድ አል-አሊያ ይናገራሉ።

«በዚህ ዓመት በባህር ላይ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል። አሁን እስከተፈጠረው ድረስ በዚህ ዓመት ብቻ ከ240 በላይ ሰዎች ሞተዋል። ከ71,000 በላይ አዳዲስ ስደተኞች እና ተገን ጠያቂዎች በየመን ተመዝግበው ይገኛሉ። ይህ

ጉዳይ አሳሳቢ ችግር ነው። የመን የምትገኘው እጅግ በጣም ሃብታም እና እጅግ ደሃ በሆኑ ሃገራት መካከል ነው። ሶማሊያ እና ኢትዮጵያን ከመሳሰሉ የአፍሪቃ ቀንድ ሃገራት የሚመጡ ስደተኞች በየመን ጥገኝነት ይጠይቃሉ። ነገር ግን ብዙ ጊዜ እንደ ኢትዮጵያ ካሉ ሃገራት የሚመጡት የተሻለ የኑሮ ሁኔታ እና የስራ እድል የሚፈልጉ የኤኮኖሚ ስደተኞች የመንን እንደ መሸጋገሪያነት በመጠቀም እንደ ሳኡዲ አረቢያ እና ኩዌት ወደ መሳሰሉ ሃገራት ይሄዳሉ።»

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን መረጃ መሰረት በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ ከሚገኙ ስደተኞች 95 ከመቶው ሶማሊያውያን፣ አብዛኞቹ ጥገኝነት ጠያቂዎች ደግሞ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፣ በየመን ከ246,000 በላይ ስደተኞች ይገኛሉ።

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ

 

Audios and videos on the topic