የስደተኞች ቤተሰቦችን ወደ ጀርመን ማምጣት ይገድባል የተባለው ረቂቅ ህግ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 11.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የስደተኞች ቤተሰቦችን ወደ ጀርመን ማምጣት ይገድባል የተባለው ረቂቅ ህግ

አዲሱ የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ጀርመን የሚገኙ እና ወደ ጀርመን የሚመጡ ስደተኞችን በሚመለከት ተግባራዊ ሊደረጉ ያሰቧቸው እቅዶች እያወዛገቡ ነው። ከመካከላቸው ቤተሰቦቻቸውን ወደ ጀርመን ማምጣት በሚፈልጉ ስደተኞች ላይ ሊጣሉ የታሰቡ ገደቦች ይገኙበታል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:43

የስደተኞች ቤተሰቦችን ወደ ጀርመን ማምጣት ይገድባል የተባለው አዲስ ረቂቅ

ስደተኞች በብዛት ጀርመን ከገቡበት ከጎርጎሮሳዊው 2015 ወዲህ የስደተኞች ጉዳይ በየአጋጣሚው ተደጋግሞ የሚነሳ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኖል። ሰሞኑንም የአዲሱ የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር የኽርስት ዜሆፈር ስደተኞችን የሚመለከት አዲስ እቅድ ማነጋገር ይዟል። ይኽው በጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በሌሎች የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ውይይት የሚካሄድባት ረቂቅ ህግ የስደተኞች ቤተሰብ አባላት ጀርመን ሊመጡ የሚችሉበትን አሠራር የሚያጠብቅ መሆኑ ተነግሯል። ረቂቁ ጀርመን ሊመጡ የሚችሉ የቤተሰብ አባላትን ከመገደብ በተጨማሪ እዚህ ያለው ስደተኛው ቤተሰቦቹን ለማምጣት ከዚህ ቀደም ያልነበረ አዲስ ቅድመ ግዴታ እንዲገባ ሊያስገድድ ይችላል ተብሏል። በነዚህ አዳዲስ ገደቦች ሰበብ ትችት የሚቀርብበት አዲሱ ረቂቅ ግን ሁሉንም ስደተኞች እንደማይመለከት ጀርመን ፍራንክፈርት ነዋሪ የሆኑት የህግ ባለሞያ እና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ ተናግረዋል። ዶክተር ለማ እንደሚያስረዱት በጀርመን አራት የስደተኛ እውቅና አሰጣጥ ነው ያለው።

በአዲሱ ረቂቅ ህግ ቤተሰቦቻቸውን የማምጣት ገደብ ሊጣልባቸው የሚችለው ጀርመን በሰብዓዊነት እውቅና የሰጠቻቸው ስደተኞች ናቸው ይላሉ ዶክተር ለማ። እነዚህ ስደተኞች ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት  እንደ ሌሎቹ ስደተኞች ቤተሰቦቻቸውን ማምጣት ይችሉ ነበር። ሆኖም ጦርነት ሸሽተው የመጡ ከ800 ሺህ በላይ የሶሪያ እና የአፍጋኒስታን እንዲሁም የሌሎች አገራት ዜጎች ጀርመን ከገቡ በኋላ ጀርመን በሰብዓዊነት ያስገባቻቸውን የነዚህን ስደተኞች ቤተሰቦች ማምጣቱ በ2016 እንዲቆም ተደርጓል።ምክንያቱን ዶክተር ለማ ወደ ኋላ መለስ ብለው ያስታውሳሉ።

ባለፈው መስከረም ምርጫ ከተካሄደ በኋላ ይኽው ጉዳይ በአዲሱ የጀርመን ጥምር መንግሥት ምሥረታ ድርድር ላይ ንግግር ከተካሄደባቸው እና ውሳኔ ላይ ከተደረሰባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ነበር። ውሳኔው ግን አሁንም አከራካሪ ነው።

ይህ አከራክሮ ሳያበቃ ነው አዲሱ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር እና የቀድሞ የደቡብ ጀርመንዋ የባቫርያ ፌደራዊ ክፍለ ሀገር ጠቅላይ ሚኒስትር ዜሆፈር ጀርመን በሰብዓዊነት የተቀበለባቸው ቤተሰቦች ላይ ተጨማሪ ገደቦችን ያካተተ አዲስ ሃሳብ ያቀረቡት። ዶክተር ለማ እንደሚሉት በአዲሱ ሃሳብ ላይ ቅድመ ሁኔታዎች ተካተዋል። እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች በጥምር መንግስቱ ውል ላይ ውይይት አልተደረገባቸውም።

ኤርትራውያን ስደተኞች ጀርመን ውስጥ እውቅና የማግኘት ችግር ባይኖርባቸውም ቤተሰቦቻቸውን ወደዚህ የማምጣቱ ሂደት ግን አስቸጋሪ መሆኑን  ለስደተኞች እገዛ በሚያደርገው የፍራንክፈርት አካባቢ ወንጌላውያን ቤተ ክርስቲያን ለስደተኞች የማህበራዊ ምክር  አገልግሎት የሚሰጡት ያሉት አቶ  አቶ መሐሪ ደንፉእ ይናገራሉ። አተ መሐሪ እንደሚሉት ዋናው ችግር የሚሰጣቸው የጊዜ ገደብ ማጠር ነው። በዚህ የተነሳም ድርጅታቸው ስደተኞች ማመልከቻ የሚያስገቡበትን ጊዜ እንዲያዘገዩ ይመክራል። 

ለ30 ዓመታት ስደተኞች ሲያማክሩ የቆዩት አቶ መሐሪ እንደሚሉት ስደተኞች ቤተሰቦቻቸው ጀርመን እስኪመጡ ድረስ ብዙ ገንዘብ እንዲያወጡ ይገደዳሉ። ለመረጃ ልውውጥ አስፈላጊ የሆኑትን ዘመናዊ የእጅ ስልኮች ለቤተሰብ መላክ ግድ ነው።ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪዎች ያደርጋሉ። የቤተሰቦቻቸውን መሰረታዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ገንዘብ ማውጣት አለባቸው። ከዚህ ሁሉ ወጭ ጥበቃ እና ጥረት በኋላ ደግሞ ቤተሰቦቻቸው ሳይመጡ የቀረባቸው ጥቂት የሚባሉ አይደሉም እንደ አቶ መሐሪ። 

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ 

 

Audios and videos on the topic