የስደተኞች ሕልም ከመሊያ ባሻገር | አፍሪቃ | DW | 02.04.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የስደተኞች ሕልም ከመሊያ ባሻገር

የሰሃራን ምድረ በዳ አቋርጠው በጀልባ አውሮፓ ለመግባት የሚጥሩ አያሌ ወጣቶችና ጎልማሶች በየጊዜው ስለሚያጋጥሟቸው አያሌ ሕልውና ተፈታታኝ ተግዳሮቶች ያልተነገረበት ጊዜ የለም። ቀደም ባሉት ጊዜያት ከሰሜን ምዕራብ አፍሪቃ በጀልባዎች ወደ ካናሪ ደሴቶች

በመሻገር እስፓኝ ግዛት ለመግባት ጥረት ይደረግ የነበረበት ጊዜ አይዘነጋም ። በመኻል እየሰመጡ ሕይወታቸውን ያጡ ጥቂቶች አይደሉም። ከሊቢያና ከቱኒሲያ በኩል በላምፔዱዛ ደሴት በኩል ወደ ማልታም ሆነ ሲሲሊ የሚደረገው የባህር ላይ ጉዞ አልቆመም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በጂብርላታር የባህር ሠርጥ በኩል ሞሮኮን ከሚያዋስኑት የአስፓኝ ወሽመጣዊ ግዛቶች ሜሊያና ሴውታ ለመግባት አደገኛውን ትብትብ የሽቦና የብረት አጥር እያለፉ የሚገቡ አሉ። ይህ ሁሉ ኑሮን ለማሻሻል ካለ ህልም ጋር ተያይዞ የሚካሄድ ጉዳይ ነው። የዶቸ ቨለው አሌክሳንደር ገኧበል ያቀረበውን ዘገባ ተክሌ የኋላ እንደሚከተለው ያቀርበዋል።

«በቀጥታ ድንበሩ አጥር ላይ በቻይና ሠፈር በአይሮፕላን ማረፊያው መካከል ነው የቆምነው። እዚህም ላይ ነው ስደተኞች አጥሩን ጥሰው ለመግባት ጥረት የሚያደርጉት። የከተማው አስተዳደር ፣ በመኻሉም ፣ የ NATO ን ትብትብ የሽቦና የብረት አጥር ተንጠላጥሎ ለመግባት ለሚሞክሩ አዳጋች እንዲሆን አጥሩ ተ,ጥግጦቆሟል።»

ሆሴ ፓላዞን 6 ሜትር ከፍታ ካለው የድንበር አጥር ጥግ ከሚያልፈው መንገድ ዳር ቆመዋል። መምህር ናቸው። ለስደተኞች በመቆርቆር የተቻላቸውን ሁሉ ሲያደርጉ ዓመታትት አልፈዋል። ከአንድ ዓመት በፊት ፣ ሽቦው አጥር ምንም ያህል ከፍታ ይኑረው፣ ስደተኞቹ፣ በመንጠላጠል፤ ጥሰው መግባታቸው አይቀርም ብለውኝ ነበር። አልተሳሳቱም። በዚህ ዓመት እንሆ በዛ ያሉ ናቸው ፣ በህገ ወጥ መንገድ መሊያ ውስጥ የገቡት። ስደተኞች መqw,በያው በር CETI ከብረት አጥሩ ጥቂት ሜትሮች ራቅ ብሎ ስደተኞችና ረዳቶቻቸው ሲተራመሱ ይታያሉ።

«በአሁኑ ጊዜ በዚህ በ«ሴቲ« ያለነው ሁኔታው ከአቅም በላይ ሆኖብናል። በአሁኑ ጊዜ ቁጥራቸው ከ3 እጥፍ በላይ የሆነ ስደተኞችን ነው የምናስተናግደው። ይሁንና በዚህ የሚሠሩ ሁሉ በታቻለ መጠን ለመርዳታ ነው ሲጣጣሩ የሚታዩት።»

ላውራ አራንዳ የህግ ጠበቃ ናቸው። ሴቲ ላይ ስደተኞችን በተገን ጥየቃ ረገድ ያማክራሉ። ተቀባይነት የማግኘት ዕድል ያላቸው እጅግ ጥቂቶቹ ናቸው

«እጅግ ጥቂቶች! ምንጊዜም በጣም አስቸጋሪ ነው፤ ተገን ጠያቂዎቹ እንደሚሳደዱ ማስረጃ ለማግኘት። ከምንፈልገው እጅግ ያነሰ ቁጥር ያላቸው ናቸው ተቀባይነት የሚያገኙት። »

የቻድ ተወላጅ የሆነው፣ ጀርሚ የተባለው የ 21 ዓመት ወጣት ፣ በትውልድ ሃገሩ ፍጹም መረጋጋት ባይኖርም የእርስ በርሱ ጦርነት ካከተመ ቆይቷል ። ተቀባይነት የማግኘት ዕድሉ የመነመነ ነው። ጀርሚ የ 18 ዓመት ወጣት ሆኖ ነው ወደ ቀውሮፓ ጉዞ የጀመረው። ከመሊያ አቅራቢያ ጉርጉ ኮረብታ ላይ 2 ዓመት ተቀምጧል። የሽቦውን አጥር ተንጠላጥሎ ለማለፍ ሲሞክር ቆስሎ እጁ ላይ የቁስሉ ጠባሳ ይታያል። ከ 6 ሳምንት በፊት ግን ሌላው ሙከራው ተሳክቶለታል።

« ከሌሊቱ 11 ሰዓት ላይ ጸሎት ጨርሰን ነበረ ወደ አጥሩ የገሠገሥን። በ 12 ሰዓት የሽቦና ብረት አጥሩን ለማለፍ ትግሉን ተያያዝነው። በየቦታው የሞሮኮ ፖሊሶች ስለነበሩ በሩጫ ነው አጥሩ ጋር ደርሰን መወጣጣት የጀመርን። የምንሰማው ፍጠኑ! የሚል ድምፅ ነበረ። ከጓደኞቼ በመጀመሪያው ረድፍ የነበሩት ዘለው እስፓኝ ምድር ገቡ፤ እኔ ዕጣዬ ሆኖ አጥሩ ጋ ተጣብቄ ቀረሁ። የቀይ መስቀል ሠራተኞች ከሽቦው አጥር አላቀው ወደ እስፓኝ ምድር ሳልጎዳ እንድወርድ አገዙኝ።»

በስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ጀርሚ መጠጊያ ቤት፣ ምግብና የአስፓኝ ቋንቋ ትምህርት ይሰጠዋል። ይሁንና በዚያም ሆኖ የሚያሳስበው ጉዳይ አላጣም።

«በየዕለቱ ከጉሩጉ ኮረብታ ፀሐይ በመሊያ በኩል እንዴት እንደምትጠልቅ ፤ ማታም ከባህር ዳር የተተከለ መብራት እንዴት ያለ ብርሃን እንደሚሰጥ እንታዘብ ነበር። አሁን ግን እዚህ ሆኜ፣ ማዶ ወደ ጉሩጉ ኮረብታ ነው የምመለከተው። የማስበው ስለወንድሜ ነው። ከማዶ በጉሩጉ ኮረብታ ስለሚገኘው።!»

የስደተኞች መጠለያ ጣቢያው ለ 500 ሰዎች ታስቦ የተዘጋጀ ነው። አልፎ አልፎ ፣ በዚህ ወር እንደታየው 2000 ያህል ሰዎች ናቸው የተሰበሰቡት። በየሳምንቱም ወደ ማጎሪያ ጣቢያ የሚወሰዱ ስደተኞች ጥቁቂቶች አይደሉም። ወደመጡበት እስኪሸኙ ፣ የተገን ጥያቄአቸው ታይቶ ምላሽ እስኪያገኙ ድረስ!

አንዳች ወረቀት የሌለው ከየት ሀገር እንደመጣም መረጃ የሌለው በአስፓኝ ህግ ከ 60 ቀናት በኋላ ነጻ ይለቀቃል። ጀርሚ አሁን ስለዚያ አይደለም የሚያስበው። መሊያ በመግባቱ ነው የሚደሰተው። አንድ ህልም እንዳለውም እንዲህ ሲል ተናግሯል።

«መደበኛ የእግር ኳስ ተጫዋች መሆን ነው ህልሜ! እግዚአብሔር ብርታቱን እንዲሰጠኝ ነው የምጸልየው። ከተሳካልኝ፤ እታወቃለሁ፤ ምናልባት በማድሪድ ለሪያል ክለብ እጫወት ይሆናል። ወይም ለባየርን ሙዑንሸን! ማንም ይሁን ችግር አይደለም። አምላክ ከረዳኝ እዚያ ይሆናል መድረሻዬ!»

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic