የስደተኞች ሁኔታ በግሪክ የኮስ ደሴት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 01.09.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የስደተኞች ሁኔታ በግሪክ የኮስ ደሴት

ግሪክ በምሥራቁ የሀገሯ አካባቢ ወደሚገኙት ደሴቶችዋ የመጡት ስደተኞች ቁጥር ላይ ባለፉት 24 ሰዓታት ጉልህ ጭማሪ መመዝገቡን አስታወቀች። የመንግሥት መዘርዝሮች እንዳሳዩት፣ ባለፈው ሰኞ እና ማክሰኞ መካከል ብቻ 462 ስደተኞች ከቱርክ በሕገ ወጥ ሰው አሸጋጋሪዎች ጀልባዎች ሌስቦስ፣ ኮስ እና ሮዶስ ደሴቶች ደርሰዋል። ባለፈው ሳምንት 499 ነበሩ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:15

ኮስ እና ስደተኞ

እጎአ በ2015 ዓም ከቱርክ ወደ ግሪክ የገቡት ስደተኞች ቁጥር 857,000 ነው። የዶይቸ ቬለው ቮልፍጋንግ ላንድሜሰር በኮስ ደሴት አንድ የስደተኞችን ማዕከል ከአንድ ዓመት በኋላ እንደገና ጎብኝቶዋል።

የአውሮጳ ህብረት ስደተኞች ከቱርክ በግሪክ በኩል እያደረጉ ወደ ሰሜናውያቱ የአህጉሩ ሀገራት ለመግባት የሚያደርጉትን ጥረት ለማስቆም ከቱርክ ጋር ባለፈው መጋቢት ወር ስምምነት ከደረሰ ወዲህ በየወሩ አውሮጳ የገቡት ስደተኞች ቁጥር በጉልህ ቀንሶ ቢቆይም፣ የነሀሴ ወር ከገባ ጀምሮ ቁጥሩ ከፍ እያለ መሄድ ጀምሮዋል። ሀንጋሪን የመሳሰሉ አውሮጳውያት ሀገራት ድንበሮቻቸውን ከዘጉ ወዲህ ወደ 59,000 የሚጠጉ ስደተኞች በግሪክ ደሴቶች መቆየት ተገደዋል።

በኮስ ደሴት ከተቋቋሙት የስደተኞች ማስተናገጃ ጣቢያዎች መካከል አንዱን የጎበኘው የዶይቸ ቬለ ባልደረባ ቮልፍጋንግ ላንድሜሰር በአራት ፖሊሶች ጥበቃ ስር የሚገኙ ከሶስት ቀናት በፊት ኮስ የገቡ ወደ 30 የሚጠጉ ወንዶች ስደተኞችን አነጋግሮ ነበር። ከስደተኞቹ አንዱ የሆነው የፓኪስታን ተወላጅ አብዱል ለተገን ማመልከቻቸው ምላሽ እየጠበቁ መሆናቸውን ገልጾዋል።
« የምዝገባውን ሂደት አጠናቀናል። እና የመታወቂያ ወረቀታችንን በመጠባበቅ ላይ ነን። »
መጠለያ ጣቢያው የተቋቋመው ከደሴቲቱ ዋና ከተማ 15 ኪሎሜትር ርቆ በሚገኝ ኮረብታማ አካባቢ ነው። የተሰራው ባለፉት የፀደይ ወራት ሲሆን፣ በግሪክ ደሴቶች ከተቋቋሙትአምስት የመቀበያ ማዕከላት አንዱ ነው።

ወደ ኮስ የሚገቡ ስደተኞች ሁሉ ወደዚሁ ማዕከል ይወሰዳሉ። በመሆኑም ከአንድ ወር ተኩል አንስቶ በጣቢያው እንደሚገኘው ሌላው ፓኪስታናዊ አሊ የቦታ ጥበት ችግር አለ።
« የመጠለያ ጣቢያው ክፍሎች ሞልተዋል፣ በመሆኑም፣ ስደተኞቹ ውጭ መተኛት ተገደዋል። »
የ24 ዓመቱ አሊ እና ጓደኞቹም መስራት ይችሉ ዘንድ እንደ ብዙዎቹ ወረቀቶቻቸውን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ነው የገለጸው።
«ተገን ማግኘት እፈልጋለሁ። ምክንያቱም ግሪክ ውስጥ መስራት እና መቆየት ነው የምፈልገው። »
ይሁንና፣ የተገን ማመልከቻው ሂደት ተጓታች መሆኑ እና የተገን ማመልከቻቸው ተቀባይነት የማያገኝላቸው ስደተኞች ወደ ቱርክ መመለስ የሚገደዱበት አሰራር ሁኔታውን አዳጋች እንዳደረጉት ስደተኞቹ ይናገራሉ። በተለይ እንደ ኤኮኖሚ ስደተኞች ለሚታዩት ፓኪስታናዊውን አሊን ለመሳሰሉት ስደተኞች ሁኔታዎች ምቹ አይደሉም፣ ከዚህ ሌላ ደግሞ የስደተኞቹ በኮስ መቆየት ከነዋሪዎቹ ዘንድ ተቃውሞ አስነስቶ እንደነበር የፒሊ ነዋሪ የሆኑት የአንድ ቡና ቤት ባለቤት ካታሪና ድሮሱ ያስታውሳሉ። ለነገሩ በፒሊ መንደር አንድም ስደተኛ አይታይም ያሉት ድሩሱ አምና ስደተኞች በብዛት የገቡበት ሁኔታ በንግዱ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ቢያሳርፍም፣ ያ ሁሉ ግን አሁን መሻሻሉን አመልክተዋል።


« እዚህ ከስደተኞቹ ጋር ችግር የለም። እርግጥ ነው አምና የስደተኞቹ መጠለያ ጣቢያዎች በተገነቡበት ድርጊት አንፃር ተቃውሞ ነበር። ብዙዎች የጣቢያዎቹን መቋቋም በመቃወም አደባባይ ወጥተዋል። በጣም አስከፊው ባለፈው ዓመት የተፈጠረው ሁኔታ ነበር። ያኔ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች የኮስ ወደብን ባጨናነቁበት ጊዜ አለመረጋጋት አስከትሎ ነበር። አሁን ግን ሁሉ ነገር ጥሩ ነው ያለው። »
ለዚህም፣ እንደ ግሪክ የደሴቶቹ ነዋሪዎች አስተያየት፣ ምንም እንኳን ካለፉት ጥቂት ሳምንታት ወዲህ ወደ ግሪክ ደሴቶች በመምጣት ላይ ባሉት የአዲስ ስደተኞች ቁጥር ጭማሪ ቢታይበትም፣ የአውሮጳ ህብረት ከቱርክ ጋር የደረሰው ስምምነት ወደ ደሴቶቹ የሚመጡትን አዳዲስ ስደተኞች ቁጥር በመቀነሱ ረገድ ድርሻ ሳያበረክት አልቀረም።

ቮልፍጋንግ ላንድሜሰር/አርያም ተክሌ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic