የስኳር እና ዘይት ግብይት ችግር | ኤኮኖሚ | DW | 04.01.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የስኳር እና ዘይት ግብይት ችግር

በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች በገበያው ላይ የስኳር እና ዘይት እጥረት መኖሩን እየተናገሩ ነው። የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን በበኩሉ ችግሩ የስርጭት ነው ሲል ይደመጣል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:54
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
09:54 ደቂቃ

ስኳር ከገበያ ጠፍቷል፦ሸማቾች

በግንቦት ወር ጠቅላይ ሚኒሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መርቀው የከፈቱት የአርጆ ዴዴሳ ስኳር ፋብሪካ ወራት ዘግይቶ ባለፈው ሰኞ ምርት ጀምሯል። በምስራቅ ወለጋ፤ኢሉ አባቦራ እና ጅማ ዞኖች በ50,000 ሔክታር መሬት ላይ የሸንኮራ አገዳ እያለማ ስኳር ሊፈጭ ያቀደው ፋብሪካ መጀመሪያ የተመሰረተው አል-ሐበሽ በተሰኘ የፓኪስታን ኩባንያ ነበር። «በአካባቢው የክረምት መራዘም ምክንያት» ከተመረቀበት ጊዜ ዘግይቶ ሥራ እንደጀመረ በኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ኮምዩንኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጋሻው አይችሉህም ተናግረዋል። እንደ አቶ ጋሻው ከሆነ የአርጆ ዴዴሴ የስኳር ፋብሪካ በቀን 8,000 ኩንታል ማምረት እንደሚችል ጨምረው ገልጸዋል።

አርጆ ዴዴሳ ስኳር ፋብሪካ ምርት በጀመረበት በዚህ ሳምንት ግን አዲስ አበባ እና ሐዋሳን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ነዋሪዎች ስኳር ጠፋ ሲሉ ይደመጣል። የሐዋሳ ከተማ ንግድ ፅ/ቤት የሰጣቸውን የመሸመቻ ካርድ ይዘው ወደ ሱቅ ያመሩት አቶ አቶ አብዩ ዳኜ «የለም« ተብለዋል። ራሳቸውን ብላክ ብለው የሚጠሩት የደቡብ ወሎ ነዋሪ ደግሞ  «የስኳር እና የዘይት እጥረት ሕብረተሰቡን እያማረረ ይገኛል።» ሲሉ ተናግረዋል። አያት መሪ በተባለው የአዲስ አበባ ክፍል የሚኖሩት አቶ አወቀ ማለዳ ወደ ሥራቸው ሲያቀኑ ስኳር እና ዘይት ለመሸመት ማልደው በመነሳት የተሰለፉ ነዋሪዎችን ተመልክተዋል። «አያት መንደር ሸማቾች የሚባል የዘይት እና ስኳር አቅራቢ አለ። እሱን በጠየቅን ጊዜ የለንም» ተብለናል የሚሉት አቶ አወቀ ከወረዳ አስራ ሶስት ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማሕበር ስኳር እና ዘይት ያስመጣል ተብሎ ሰዎች መሰለፋቸውንም ተናግረዋል።

 ራሳቸውን ‘ብላክ’ ብለው የሚጠሩት የወልዲያ ነዋሪ የመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች በገበያ ላይ መጥፋት ከጀመሩ ስድስት ወራት መቆጠራቸውን ይናገራሉ። ስኳር እና ዘይት ከሚገኝባቸው ሌሎች አካባቢዎች መግዛት እንኳን ክልክል ነው ሲሉ ይናገራሉ።

ስድስት ፋብሪካዎችን የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ የስኳር ኮርፖሬሽን ግን የአቅርቦት ችግር የለብንም ሲል ይከራከራል። በኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ኮምዩንኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጋሻው አይችሉህም የአገሪቱ ወርኃዊ የስኳር ፍላጎት ወደ 600,000 ኩንታል ቢሆንም ፋብሪካዎቻችን በቀን 25,000 ኩንታል ያመርታሉ ሲሉ ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት በርካታ የስኳር ፋብሪካዎች በመገንባት ችግሩን ለመፍታት የጀመረው እቅድ አልሰመረም። ከ25 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስኳር አምርተው አብዛኛውንም ወደ ውጭ በመላክ እዳቸውን ይመልሳሉ የተባለላቸው ፋብሪካዎች እቅድ አለመሳካቱን የኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎች ለአገሪቱ ምክር ቤት አቤት ብለው ነበር። ኃላፊዎቹ ፋብሪካዎቹን ለመገንባት ውል የገባውን የብረታ ብረት እና ኢንጂኔሪንግ ተቋም ወቅሰዋል። አቶ ጋሻው የኦሞ ቁጥር አንድ እና ቁጥር ሁለት ፋብሪካዎች በቅርቡ ሥራ ይጀምራሉ ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የስኳር ምርት የለም ሲሉ የሚሞግቱት ኃላፊው ችግሩ የስርጭት ነው ባይ ናቸው።

በሰሜን ሸዋ ዞን የበረኸት ወረዳ ነዋሪ ስኳር እና ዘይት በገበያ አለመኖሩ ብቻ አይደለም የቸገራቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ከወረዳው ንግድ ፅ/ቤት ለሸማቾች የታደለው ካርድ በእጃቸው ባለመኖሩ ስኳር እና ዘይት መንግስት ካዘጋጃቸው መደብሮች መሸመት አልቻልኩም ይላሉ።

እንደ በረኸት ወረዳው ነዋሪ ሁሉ የሐዋሳ አቶ አብዩ ዳኜም የመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ለመግዛት በመንግሥት የተዘጋጀውን የመሸመቻ ካርድ መያዝ ግዴታ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ሚኒሥቴር በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጠን በተደጋጋሚ ያደረግንው ሙከራ አልተሳካም። የአዲስ አበባው አቶ አወቀ እና የሐዋሳው አቶ አብዩ የስኳር እና የዘይት እጥረት መቼ እንደሚፈታ በውል አያውቁም። የጠየቋቸውም ጠብቁ የሚል ምላሽ ሰጥተዋቸዋል።

 

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic