መቋጫ ያላገኘው የስነጾታዊ ጥቃት ማብቂያው መች ይሆን?
ማክሰኞ፣ ኅዳር 17 2017በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን ለማክተም በሚል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዓለም አቀፍ መታሰቢያ ቀን ሰኞ ኅዳር 16 ቀን፣ 2017 ዓ.ም ውሏል ። የሰብአዊ መብቶች ቀን ማክሰኞ ታኅሣሥ 1 ቀን፣ 2017 ዓ.ም እስከሚውልበት ድረስም በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ጾታዊ ጥቃት የማስቆም ዘመቻው እንቅስቃሴ ይቀጥላል ። ይህን ተከትሎም በተለይም ከትናት ጀምሮ በአውሮጳ እና በርካታ አገራት ማኅበረሰብን ማንቃት ላይ ያተኮሩ የጸረ-ስነጾታዊ ጥቃት እንቅስቃሴዎች በስፋት እየተከናወኑ ይገኛሉ ። በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ ያልተሰሙ እና እንግዳ የሆኑ አዳዲስ የጥቃት አይነቶችም ሲስተጋቡ መስማት እየተለመደ የመጣ ጉዳይ ሆኗል ። ለመሆኑ ስለችግሩ መንስኤና መፍትሄ በባለሞያዎች የተከናወኑ ጥናቶች ምን ያሳያሉ?
የስነጾታዊ ጥቃት ምንነት
ፋናዬ ገብረሕይወት በሞያቸው የሕግ ባለሞያ ሲሆኑ በኋላም በስነጾታ ላይ አተኩረው ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በስርዓተጾታ ላይ አተኩሮ ከሚሠራው አንድ ዓለማቀፍ ድርጅት ጋር የኢትዮጵያ ተወካይ ሆነው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ እሳቸው አስተያየታቸውን የጀመሩት ስርዓተ ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት ምንነትን በማብራራት ነው፡፡
«ስርዓተ ጾታ ማንም ቢሆን ወንድም ሆነ ሴት ጾታቸውን መሰረት አድርጎ በጾታቸው ምክንያት የሚደርስባቸው ጥቃት ነው፡፡ በዓለማቀፍ ደረጃ ሲታይ ደግሞ ይህ ጥቃት በብዛት ሴቶች ላይ አተኩሮ የሚከሰት ስለሆነ ፤ ሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት ተብሎ እንዲተረጎም ሆኗል፡፡ ይህ ጥቃት ለሞት የሚያበቃ፣ አካላዊ አሊያም ስነልቦናዊ ሊሆን እንደሚችል» ባለሞያዋ አስረድተዋል፡፡
የሴቶች መብት አንቂዎች ኖቬምበር 25 ወይም ኅዳር 16 በየዓመቱ ጸረ-ስነጾታዊ ጥቃት ቀን ሆኖ እንዲሰየም በማድርግ ከጎርጎሪዮሱ 1981 ጀምሮ በእለቱና በቀጣይ ሳምንታት በሙሉ ጥቃቱን የሚወግዙ የተለያዩ ንቅንቄዎችን ይከውናሉ፡፡ እለቱም የተመረጠው በ1960 የሚራባል እህትማቾች የተባሉ ሦስት ንቁ ፖለቲከኞች በዶሚኒካ ሪፐብሊክ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ የተገደሉበትን እለት ለማስታወስ ነው፡፡
የጥቃቱ ከዘመናት ጋር መልኩን መቀያየር
ያኔ የተጀመረው የጸረ-ስነጾታዊ ጥቃት ውግዘት እንቅስቃሴዎች እስካሁንም የተፈለገውን ውጤት ለማምጣቱ ግን በርካቶች ይጠረጥራሉ፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ ከታዳጊ ህጻናት ጀምሮ በአስገድዶ መድፈርና ብዙ መልክ ያላቸው ስነጾታዊ ጥቃቶች በቅርቡም በአሰቃቂ ገጽታው ተሰምቷል፡፡ የስነጾታ ባለሙያዋ ፋናዬ ገብረሕይወት በአገሪቱ እየተስተዋለ ያለው ግጭት ለዚህ አይነተኛ ሚና እንዳለው ያስረዳሉ፡፡ "ጾታዊ ጥቃት እንደ ማህበረሰብ ለውት መልኩን እየቀያየረ የሚመጣ ነው” የሚሉት ባለሙያዋ በተሌም በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተስፋፋው ጦርነት ግጭት ለዚህ አባባሽ መንስኤ ሆኖ መቅረቡን አመልክተዋል፡፡ "የሴቶችን ጥቃት ለጦር መሳሪያነት መጠቀም በጉልህ ተስተውሏልም” የሚሉት ባለሙያው የስራ አጥነቱ እና ግጭት አባባሽ የጥቃቱ መንስኤ ነው ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል መምህርት እና ብዙ ጥናቶታቸውን በስነጾታ ላይ የሰሩ ተባባሪ ፕሮፈሰር ሜሮን ዘለቀ በፊናቸው "በፊት በፊት የማንሰማቸው አይነት ጥቃቶች ከህጻናት መደፈር ጀምሮ እስከ የቡድን ደፈራ፤ ከዚያም አልፎ ያንኑን አስነዋሪ ተግባር በማህበራዊ ሚዲያ መልቀቅ እያስተዋልን ነው” በማለት የጥቃቱ ባህሪያት መለቃወጥ አንስተዋል፡፡
የስነጾታዊ ጥቃት መንስኤዎች
ተባባሪ ፕሮፌሰር ሜሮን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ምክንያት ተብለው በጥናት ስለተለዩ የስነጾታ ጥቃት መንስኤዎች ይህን ብለዋል፡፡ "በቅርብ ጊዜ ከአንድ የዴንማርክ ተቋም ጋር ለአራት ዓመታት ሰርተን ያጠናቀቅነው ጥናት ለስነጾታዊ ጥቃት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ለመበራከታቸው የግጭት አውድ መስፋት፣ የጥብቅ ህግጋት አለመኖር እና የሲቪል ሶሳይቲ ድርጅቶች አለመጠናከር እንደ አበይት ምክንያቶች የሚቀርቡ ናቸው” ብለዋል፡፡
የመፍትሄ ሀሳብ
ባለሞያዎቹ መፍትሄ ነው ያሉትን ሲያስቀምጡም፤ "የማኅበረሰብ ለውጥ ማምጣትና የሲቪክ ማኅበረሰብን ማጠናከር” እንደ መሰረታዊ እና ዘላቂ ለውጥ አምጪ ተነስቷል፡፡ እምነት ተቋማት፣ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለጉዳዩ በቁምነገር የሚሰጡት ትኩረትም ሌላኛው እልባት ሆኖ ሊቀርብ እንደሚችል ተነስቷል፡፡ የመገናኛ ብዙኃን ጉዳዩን ክስተት ተኮር ከማድረግ ይልቅ በዘላቂነት የማኅበረሰብ ለውጥ ለማምታት ሊሰሩበት እንደሚገባም ተጠቁሟል፡፡ የሕግ ክፍተቶችን መጠገን ደግሞ ሌላውና ወሳኙ እንደሆነም በመፍትሄነት ተጠቁሟል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ፀሐይ ጫኔ