የስቅለት በዓል አከባበር | ባህል | DW | 18.04.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

የስቅለት በዓል አከባበር

የእየሱስ ክርስቶስ ስቅለት የሚታስበበት የስቅለት በዓል ዛሬ በመላው አለም በሚገኙ ክርስቲያኖች በሙሉ ተከብሮ ዋለ ። በዓሉ በተለይም በሺህዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች በተገኙበት በእየሩሳሌም ክርስቶስ መስቀል ተሸክሞ እንደተጓዘበትና ስቃይና መከራ እንደተቀበለበት በሚታመንበት መንገድ መስቀል ተሸክሞ በመጓዝ ተከብሯል ።

የምሥራቅና የምዕራብ አብያተ ክርስቲያን የትንሳኤ በዓል ዘንድሮ አንድ ቀን ላይ በመዋሉ በእየሩሳሌም የተገኘው ምዕመን ቁጥር ከፍተኛ ነው ።የትንሣዔን በዓል አስታኮ እዚህ ጀርመን ሀገር ከዛሬ ዓርብ ስቅለት አንስቶ እስከ ሰኞ ድረስ ሁሉ ነገር ቀዝቀዝ ይላል። መሥሪያ ቤቶች እና ሱቆች ዝግ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን በተለይ የዛሬው ዕለት በዝምታና በፀሎት ታስቦ የሚውል ቀን ነው።አብዛኞቹ ጀርመናውያን የክርስትና እምነት ተከታዮች ቢሆኑም ወደ ቤተ ክርስትያን የሚሄደው ወጣት ቁጥር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል። እንዲያም ቢሆን ግን፣ የዛሬውን የስቅለት በዓል ወደ ቤተ ክርስትያን ሄደው የሚያከብሩም አልጠፉም። ከነዚህ አንዱ የዶይቸ ቬለ ባልደረባ ጀርመናዊው ዳኒኤል ፒልስ ነው። ስለጀርመን የስቅለት በዓል አከባበር ሲያስረዳ፣ «ዕለቱ ፀጥ ያለ ነው። ሰዎች እቤት ከቤተሰቦቻቸው ጋ የሚቆዩበት ቀን ነው። የስቅለት ዕለት ብዙ ሰዎች ይፆማሉ፣ ያ ማለት ደግሞ አንድም ምንም ሳይበሉ ይውላሉ ወይም ትንሽ ሾርባ ይጠጣሉ፣ አልያም ቁራጭ ዳቦ ይበላሉ። በአብዛኞቹ የክርስትና እምነት ተከታዮችም ቤት ስጋ አይበላም። »

ይህ ብቻ አይደለም። ብዙዎች ከቻሉ በዛሬው ዕለት ለፀሎት ወደ ቤተክርስትያን ይሄዳሉ። «ጀርመን ውስጥ በተለይ በማውቀው በካቶሊክ እና በፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ዘንድ ከሰዓት በኋላ ዘጠኝ ሰዓት ላይ እየሱስ ክርስቶስ ነፍሱን የሰዋበት ሰዓት ይታሰባል። ቤተ ክርስትያን ይኬድና ከመፅሀፍ ቅዱስ ውስጥ፤ እየሱስ ክርስቶስ እስከ ተሰቀለበት ጊዜ ያለው ታሪክ ይነበባል። ፀሎት ይደረጋል፣ መዝሙር ይዘመራል። በዚህ አጋጣሚ የእየሱስ ክርስቶስ ሞት ብቻ ሳይሆን የራሳችን ህይወትም አንድ ቀን ማለቂያ እንዳለው እናስታውሳለን።»

እንደ ዳንኤል ሁሉ በጀርመን ሙኒክ ከተማ የሚኖረው የስነ መለኮት እና የፍልስፍና ተማሪ ድልባየህ ሳህለ ድንግልም ቤተ ክርስትያን ይሄዳል። የካቶሊክ ቤተክርስትያን የምዕራባዊያን ስርዓተ-አምልኮ ድልባየህ ኢትዮጵያ ከሚያውቀው በምን እንደሚለይ ገልፆልናል።

ምዕራፍ ደምሳሽ ደግሞ ጀርመን ሀገር ተወልዳ ያደገችው ወጣትና የኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታይ ናት። እሷም የስቅለትን በዓል ታከብራለች።

እዚህ ጀርመን ሀገር የዛሬዋን ቀን እምነቱ የማይመለከታቸውም ሰዎች የሚፈልጉትን ነገር ከማድረግ በመጠኑ ይቆጠባሉ። ለምሳሌ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ሙዚቃ ጮክ አድርጎ ማጫወት አይፈቀድም። ይህ ብቻ አይደለም እንደውም በአብዛኞቹ የጀርመን ግዛቶች ጭፈራ ቤቶች ፣ ሲኒማ እና ቲያትር ቤቶች በሕግ እንዲዘጉ ተደንጎጎዋል። ይኸው ህግ ዳንኤልን ረብሾት ያውቅ እንደው ጠይቄዋለሁ። « በፍፁም። አስተዳደጌ በክርስትና እምነት ተከታዮች ስር ስለነበር ዕለቱን በተለየ ሁኔታ ማሳለፍ እንዳለብን የተለመደ ነበር። ግን እኔን ይረብሸኝ የነበረው እኛ ቤት በዚህ ቀን ስጋ አንበላም ነበር። እኔ ደግሞ ስጋ መብላት እወድ ስለነበር በጣም ቅር ይለኝ ነበር። እና ትንሽ እያለሁ ስቅለት ስለሆነ ብቻ እኔ ቀኑን ሙሉ አይብ የምበላበት ምክንያት አልገባኝም ነበር።»

አሁን ግን የዳንኤል አመለካከት ተቀይሯል። በዛሬው ቀን ጨርሶ ስጋ አይበላም። «ይህንንም የማደርገው አምኜበት ነው» ይላል። ዛሬ ምሽት ጭፈራ ቤት መሄድ አለመቻላቸው ያላስደሰታቸው ወጣቶች ይህ ህግ ከዘመኑ ጋር የማይሄድ ነው በማለት ይወቅሳሉ። ወጣት ምዕራፍ ግን በዚህ አትስማማም። ጀርመናዊው ዳንኤልም ቢሆን ምንም እንኳን በጀርመን በርካታ ሀይማኖትን የማያጠብቁ ወጣቶች ቁጥር ቢጨምርም ይህ ቀን እንዳለ ተጠብቆ እንዲቆይ ይፈልጋል።

« የስቅለት ቀን በዓል ሆኖ እንዲቆይ እመኛለሁ። አንደኛ እኔ ራሴ ክርስትያን በመሆኔ እና አስፈላጊ ነው ብዬ ስለማስብ፣ 2ኛ ደግሞ ለክርስትያኖች ክብር ሲባል በዓመት አንዴ ለሚመጣ ቀን ሁሉ ነገር ፀጥ ቢል እመርጣለሁ። ሌላው የምመኘው ነገር ክርስትያን ያልሆኑ ሰዎች ይህንን ቀን እንደ አንድ አጋጣሚ እንዲጠቀሙበት ነው። ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ ህይወታቸው በጥድፊያ የተሞላ እንደሆነ የሚናገሩ ሰዎች ይገጥሙኛል። ምናልባት ይህ ቀን የሚያርፉበት እና ሁሉም ረጋ ብለው ሊሰሩት ስለሚፈልጉት ነገር ረጋ ብለው የሚያስቡበት ቀን ሊያደርጉት ይችላሉ። እንደዚህ አይነት ፀጥ ያለ ቀን ለሁሉም ሰው ጥሩ አጋጣሚ ነው ብዬ አስባለሁ። »

ሙሉ ዝግጅቱን ከድምፅ ዘገባው ያገኙታል።

ልደት አበበ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic