የስራ እድልና የፋብሪካዎች ሁኔታ በሰበታ ከተማ | ኢትዮጵያ | DW | 13.02.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የስራ እድልና የፋብሪካዎች ሁኔታ በሰበታ ከተማ

በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ተቃውሞ በተካሄደበት ወቅት በተጣሉ ጥቃቶች በልዩ ልዩ የልማት ተቋማት እና የውጭ ኩባንያዎች ንብረት ላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል። የጥቃቱ መንስኤ ከሚባሉት መካከል መንግሥት እና ኩባንያዎቹ  ለማህበረሰቡ የገቡትን ቃል አለማክበራቸው አንዱ መሆኑ ተሰምቷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 02:16

ስራ እድል

አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት፣ የትምሕርት ቤቶች፣ መንገዶች እና የጤና ተቋማት ግንባታዎች አለመሟላታቸው፣ የልማት ተቋማቱም ሆኑ ኩባንያዎቹ የአካባቢውን የተማረ የሰው ኃይል ከመቅጠር ይልቅ  ከሌላ ቦታ የሚመጡ ሰዎችን መቅጠራቸው በሕዝቡ ዘንድ ቅሬታ ፈጥሯል።

ከአዲስ አበባ ወደ 20 ኪሎሜትር ርቃ በምትገኘዉ የሰበታ ከተማ  ውስጥ ወደ 714 ፋብሪካዎች ለሰፋፊ ኢንቬስትመንት ቦታ ተሰጥቷቸው ነበር። ከነዚህም መካከል እንቅስቃሴ የጀመሩት ወደ 400 የሚሆኑት  ከ50,000 በላይ ለሚሆኑ የአከባቢው ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር እንደቻሉ የከተማዋ የኮሙኒኬሼን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፍ አቶ ወርቁ ደበሌ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል።  ይህ ጥሩ ሂደት ቢሆንም፣ ከተማዋ ለአዲስ አበባ ቅርብ በመሆኗ ለመሬት ብዝበዛ የተጋለጠችበት ሁኔታ በኢንቬስትመንት ላይ ትልቅ ጉዳት ማስከተሉን ኃላፊው ጠቅሰዋል።

«የተጎዱት ፋብሪካዎች ቁጥር 13 ነዉ።  የጨርቃ ጨርቅ እና የማኑፋክቸርንግ ፋብሪካዎች፣ እንዲሁም፣ የአበበ እርሻ ይገኙበታል። 13 ቱ ፋብሪካዎች በጠቅላላ ተቃጥለው አልወደሙም። አንድ አንዱ ላይ ሙከራ ብቻ ነዉ የተደረገዉ፣ አንዳንዶቹ ላይ ደግሞ ቀለል ያለ ጉዳት ነዉ የደረሰዉ። ሙሉ በሙሉ ተቃጠለ የምንለዉ አንድ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ሲሆን፣ እሱም ከፋብሪካዉ ባህር ወይም በቀላሉ የሚቀጣጠሉ ልብሶች ስለሚገኝበት ተቃጥሏል።»

ይህ ክስተትም ወደ 4, 227 የሚጠጉ ሰዎችን ስራ አጥ እንዳደረጋቸዉ አቶ ወርቁ አስታውሰው፣  በወቅቱ 12 ፋብሪካዎች እንደገና ወደ ስራ መመለሳቸዉን ይናገራሉ። አዳዲስ ፋብሪካዎችም እየተገነቡ ስለሆነ ወጣቶቹን በዚያ ለመቅጠር እቅድ እንዳለም አክለው ተናግረዋል።

ፋብሪካዎቹ ከ50,000 በላይ ለሆኑ ሰዎች የስራ እድል መፍጠራቸውን ያስታወቁት አቶ ወርቁ አብዛኞቹ ወጣቶችና ሴቶች መሆናቸዉን ይናገራሉ። የፋብሪካዎቹ ተቀጣሪዎች ከየት እንደሆኑ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ወርቁ ሲመልሱ፣ «እነዚህ ወጣቶች የተቀጠሩት ከኦሮሚያ ነዉ። ከዉጭ አገር ወይም ከሌሎች ክልሎች ከመጡ የተወሰኑ ባለሙያዎች በስተቀር ፣ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ወጣቶች ናቸዉ። እነዚህ ወጣቶች የሚከፈላቸዉን ደሞዝ በቂ ሆኖ ባያገኙትም፣  ፋብሪካዉ ይዞ የመጣዉን የቴክኖሎጂ እዉቀት እየቀሰሙ ነዉ። በተጨባጭ ማሽኖችን በማንቀሳቅስ ከቻይና እና ከፓክስታን የመጡ ፋብሪካዎች ዉስጥ እየሰሩ ይገኛሉ።»

መንግስት በሰበታ ከተማ ከ12,000 በላይ ለሆኑ ስራ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ወደ 300 ሚልዮን ብር የተመደበላቸው 101 ፕሮጄክቶች ማዘጋጀቱን የኮሙኒኬሼን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፍ አቶ ወርቁ ለዶይቼ ቬሌ ገልጸዋል።

መርጋ ዮናስ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic