የሴኔጋል ወታደሮች ወደየመን ይላካሉ | አፍሪቃ | DW | 07.05.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የሴኔጋል ወታደሮች ወደየመን ይላካሉ

አፍሪቃዊቱ ሀገር ሴኔጋል የእርስበር ጦርነትና የዉጭ ኃይሎች የአዉሮፕላን ድብደባ ወደሚያወድማት ድሀ የአረብ ሀገር የመን ወታደሮች ለመላክ ወስናለች። የመንግሥት ዉሳኔ ግን የአብዛኛዉን ዜጋ ድጋፍ ያገኘ አይመስልም።

በዉሳኔዉ መሠረትም ሴኔጋል ከሁለት ሺ የሚበልጡ ወታደሮችን ወደየመን ትልካለች። በትዊተር የተሰራጩ መልዕክቶች ማንነታቸዉ ያልተገለፀ የምክር ቤት አባላትና በርከት ያሉ ዜጎች ይህን የሚቃወሙ ሃሳቦችን ጽፈዉ መመልከቷን የዶቼ ቬለዋ ሳራ ሽቴፋን በዘገባዋ ጠቅሳለች።

ከሴኔጋል ዋና ከተማ ዳካር ሐዋ ባ በትዊተር ያሰፈረችዉ መልዕክት« በሳዉዲ የሚመራዉን የመን ላይ የሚካሄድ ዘመቻ ለማገዝ ሴኔጋል ወታደሮች ለመላክ መወሰኗ ተቀባይነት የለዉም፤ ዜጎችና የምክር ቤት አባላት ተቃዉመዉታል፤» የሚል ነዉ። ሌላዉ ቦካር ቦኩም የተሰኘዉ ፀሐፊ ደግሞ፣ «የምንነጋገዉ ስለሴኔጋል ወታደሮች እንጂ ከፍተኛ ዋጋ ለሚከፍሉ በነፍሰ ገዳይነት ስለሚቀጠር ተዋጊ አይደለም። ይላል። ሌላዉ የዳካር ኗሪ ማማዱ ናዲየ በበኩሉ፤ «ናይጀሪያ ቦኮሃራምን እንዲዋጉላት የሴኔጋል ወታደሮችን መቅጠር ይኖርባታል፤ እናም ነዳጅ ትክፈላቸዉ፤ ጉዳዩ ዞሮዞሮ የገንዘብ አይደል?»

እንደመንግሥት እቅድ ከሆነ በስዑድ አረቢያ ፊት አዉራሪነት በየመን ሁቲ አማፅያን ላይ ለተከፈተዉ የጦር ዘመቻ ሴኔጋል 2,100 ወታደሮችን ታዋጣለች። ለዚህም የሴኔጋል ፕሬዝደንት ማኪ ሳል ከሳዉዲ ንጉሥ ጥያቄ እንደቀረበላቸዉ የሀገሪቱ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለምክር ቤቱ ገልጸዋል። በሎንዶን የቻተም ሀዉስ የአፍሪቃ ጉዳይ ፖለቲካ ተንታኝ ፖል ሜሊ አገላለፅ ለሴኔጋል እንዲህ ባለዉ ዓለም ዓቀፍ ዘመቻ መሳተፍ ትርጉም አለዉ።

«ለሴኔጋል መካከለኛ ወታደራዊ ኃይል እንዳለዉ አፍሪቃዊ ሀገር፤ 2,000 ወታደሮችን በዓለም አቀፍ ዘመቻ ማሳተፍ ትልቅ ቁርጠንነት ነዉ። ይህም ማለት ለምሳሌ በተመድ ሥር ማሊ ዉስጥ ሰላም ለማስከበር ካሰማሩት ኃይል ይህ እጅግ ይበልጣል።»

ሳዉዲ ከመጋቢት ወር ጀምራ የመን ዉስጥ ስልጣን ለመቆናጠጥ እየገሰገሱ በነበሩት የሁቲ አማፅያን ላይ በአየር ጥቃት ስታደርስ ቆይታለች። ሁቲዎች ሺያቶች ናቸዉ። አብዛኛዉ ሱኔጋላዊ ደግሞ እንደብዙሃኑ የሳዉዲ ዜጋ ሱኒ ሙስሊም ነዉ። እና የሴኔጋል መንግሥት የሁቲ አማፅያኑ ግስጋሴ «ወዳጅ» ብሎ ለሚጠራት ስዑድ አረቢያ አሳሳቢ አደጋ ነዉ። በሎንዶኑ ቻተም ሀዉስ የአፍሪቃ ጉዳይ ተንታኝ ፖል ሜሊ አስተያየት ግን ሁቲዎች ያን ያህል ለሴኔጋልም ሆነ ሳዉዲ ያሰጋሉ የሚባሉ ኃይሎች አይደሉም።

«ከሴኔጋል ፀጥታና ደህንነት ጋ የሚገናኝ አለ ብዬ አላስብም። ሁቲዎችም ቢሆኑ የዓለም አቀፍ ጂሃዳዉያን መረብ አካል ወይም ደግሞ የፅንፈኝነት አጀንዳ ያላቸዉ ቡድኖች ባህሪም የላቸዉም።»

እሳቸዉ እንደሚሉትም የሁቲ አማፅያኑ እንቅስቃሴም ሆነ ትኩረት ከመካና መዲና እጅግ የራቀ ነዉ። ዋና ትኩረቱ ገንዘብና የአካባቢ ተፅዕኖን ከፍ ማድረግ ላይ ያደረገ መሆኑንም ያስረዳሉ።

«ገንዘቡ በአብዛኛዉ ከሳዉዲ ወይም ከሌሎች ኅብረት ከፈጠሩ የአረብ ሃገራት እንደሚመጣ ይገመታል፤ ይህ ደግሞ በሴኔጋል መንግሥት ዘንድ የሚፈለግ ነዉ። ሆኖም ግን ፕሬዝደንት ማኪ ሳል ማሳየት የፈለጉት ከባህረ ሰላጤዉ ሃገራት ጋ ያላቸዉ ግንኙነት እየጠነከረ መሄዱንም ጭምር ነዉ። ከእሳቸዉ አስቀድመዉ ስልጣን ላይ የነበሩት አብዱላይ ዋድ ከአረብ ሃገራት ጋ ያላቸዉን ግንኙነት በጥሩ ሁኔታ አሳድገዉ ነበር።»

የሳዉዲ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀገራቸዉ የመን ዉስጥ የምታካሂደዉን የአየር ጥቃት ለሰብዓዊ እርዳታ እንቅስቃሴ ስትል ለተወሰነ ጊዜ ፋታ እንደምትሰጥ ቢናገሩም፤ ሴኔጋል ወታደሮቿን እንደምትልክ መገለፁ እግረኛ ጦር ለማሰለፍ መዘጋጀቷን እንደሚያመላክት ተዘግቧል። የሴኔጋል ወታደሮች ግን ወደስፍራዉ መቼ እንደሚሄዱ ከመንግሥት በኩል አልተገለፀም። ሴኔጋል ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ነፃነቷን ከተቀዳጀች ወዲህ 25 ሺህ የሚሆኑ ወታደሮቿ በ20 የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች መሳተፋቸዉ ተመዝግቧል።

ሳራ ሽቴፋን/ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic