የሴኔጋላዊ ህልምና ፋንታ ዲላሎ | አፍሪቃ | DW | 04.08.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የሴኔጋላዊ ህልምና ፋንታ ዲላሎ

በየወሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሴኔጋላውያን የተሻለ ኑሩ ፍለጋ አገራቸውን ጥለው ወደ አዉሮጳ ይሰደዳሉ። በአውሮጳ የሚያልሙትን የተሻለ ኑሮ ከማግኘታቸዉ በፊት ግን ህይወታቸውን የሚያጥቱ ቁጥር ቀላል አይደለም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:20
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:20 ደቂቃ

የሴኔጋላዊ ህልምና ፋንታ ዲላሎ

በዋና ከተማ ዳካር ለተሻለ ኑሮ ስደትን የሚመርጡ ወገኖቿን በማሳመን ሃሳባቸዉን እንዲለዉጡ የሚጥር ድርጅት ያቋቋመችዉን ፋንታ ዲላሎ ግን ሴኔጋል ለዜጎችዋ ብዙ ዕድል አላት ባይ ናት።

ለፋንታ ዲላሎ ዳካር የበርካታ እድሎች ገበታ ናት። አገሯ ብሩህ ተስፋ እንዳላትም ታምናለች። ይህን በራስ መተማመኗን ለአገሯ ልጆች ለማካፈል ታልማለች። ለዛም ነው የ31 አመቷ ፋንታ ከአገራቸው ይልቅ በአውሮጳ ሥራ ለማግኘት የሚያልሙ ወጣት አፍሪቃውያን ላይ አተኩሮ የሚቀሳቀሰዉን «የሴኔጋላዊ ህልም» የተሰኘዉን ድርጅት ያቋቋመችው።

«ከሌሎች ሴኔጋላውያን ይልቅ ተምሯል። ቢሆንም ግን ሥራ ማግኘት አልቻለም። ስለዚህ ምን ማድረግ ትችላለህ? መሰደድ? ነው ወይስ በጀርባህ ለጥ ብለህ መተኛት? አይደለም። በየቀኑ ማለዳ እየተነሳህ የምትችለውን መሥራት አለብህ።»

ፋንታ የቡና መሸጫ ሱቅ እንዲከፍት የረዳችው ጎረቤቷ ቦካ እንዲህ አይነት ሰው ነው።

Bouka Sy

ፋንታ የቡና መሸጫ ሱቅ እንዲከፍት የረዳችው ጎረቤቷ ቦካ

«ሁሉንም ነገር በወረቀት ላይ አሰፈርኩ እና አሳየኋቸው። ሥራው ስኬታማ እንዲሆን ምን ማድረግ እንዳለብኝ አማከሩኝ። የምሠራበት ቦታም አገኙልኝ።»

በየወሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የተማሩ ሴኔጋላውያን ስራ ፍለጋ አገራቸውን ጥለው ይወጣሉ። ብዙዎቹ የሜድትራኒያን ባህርን በጀልባ ለማቋረጥ ሲሞክሩ ህይወታቸውን አደጋ ላይ ይጥላሉ። እንደ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ከሆነ ካለፈው ጥር እስከ መጋቢት የጣሊያን የባህር ጠረፍ ከደረሱት ስደተኞች መካከል 1,200 ሴኔጋላውያን ይገኙበታል። «የሴኔጋላዉያን ህልም» የተሰኘዉ ድርጅት ቦኮ የመሰደድ ሃሳቡን እንዲቀይር በማሳመን የሥራ ፈቃድ እንዲያገኝና ስለሚሠራዉ ነገር ዕቅድ እንዲያወጣ አግዞታል።

በመላ አገሪቱ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ፋንታ ከወጣቶች ጋር ትሠራለች። ለእሷ አሁን ላለው የሥራ አጥ መብዛት ቀዉስ መፍትሄው የንግድ ዘርፍ እና ግብርና ናቸው። ሌላዉ ቀርቶ በየሳምንቱ ማለቂያ ቀናት ሁሉ በርካታ ወጣቶች ሊያደምጧት ወደ እሷ ይመጣሉ።

«ሰዎች በራሳችን አገር ከመሥራት ይልቅ የአምስተርዳምን ጎዳናዎች፤ የበርሊንን መንገዶች ወይም የባርሴሎናን መንገዶች መጥረግን ይመርጣሉ። ምክንያቱም ይህ ስኬት እንደሆነ ያስባሉ። ውድ ልብሶች ለብሰዉ ወደዳካር ተመልሰዉ ከአውሮፕላን ሲወርዱ፤ ዘመዶቻቸው ሻንጣዎቻቸውን ይሸከማሉ። ወደአውሮጳ መሄድ ስለቻሉ ቆንጆዋን መርጠው ያገባሉ። ከአንድ ወር በኋላ በርሊን ተመልሰው ጎዳና ይጠርጋሉ።»

የፋንታ የሕይወት ታሪክ በራሱ ጥሩ ምሳሌ ነው። ከደህና ቤተሰብ የተገኘች በመሆኗ ወላጆቿ ወደ ፈረንሳይ ሄዳ እንድትሠራ ቢፈልጉም ትምህርቷን መርጣ ዩኒቨርሲቲ ገባች። የጀርመኑ ኮንራድ አደናዎር የተሰኘዉ ተቋምም ነፃ የትምህርት ዕድል ሰጣት። በዚህ መካከልም የዳካር ከተማ ምክትል ከንቲባ ሆናም ነበር። ለእርሷ ግን ትምህርት የሁሉ ነገር ቁልፍ ነው። ይህች ተማሪም ትስማማለች።

«ፋንታ የእኔ አርአያ ነች። ትምህርቴን ሳጠናቅቅ እንደ እሷ መሆን እፈልጋለሁ።»

ማማዱ ማክታር ግን ፋንታ በምትለዉ አይስማማም። ቢማርም ለዓመታት ሴኔጋል ዉስጥ ሥራ ማግኘት አልቻለም። ግራ የተጋባው የ35 ዓመቱ ማማዱ በጀልባ ተሳፍሮ ጉዞ ጀመረ። ነገር ግን የስፔን የባህር ጠባቂዎች ከጉዞዉ አስቀሩት። ሆኖም ለልጁ ሲል ድጋሚ የመሞከር ሃሳብ አለው።

«ልጄ ብሩህ መፃኤ ዕድል እንዲኖረዉ እፈልጋለሁ። እንደ እኔ እንዲኖር አልሻም። እዚህ በመቆየት ህልሜን አሳካለሁ የሚል እምነት የለኝም።»

እንዲህ አይነት ታሪኮች ነዉ በየዕለቱ ፋንታ የምትጋፈጠዉ። እንዲያም ሆኖ ወደ አውሮጳ የሚደረገው ጉዞ ሴኔጋላውያንንም ሆነ አገራቸውን አልጠቀመም።

ስቴፋን ሞህል/እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic