የሴቶች የፓለቲካ ተሳትፎ | የጋዜጦች አምድ | DW | 07.03.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

የሴቶች የፓለቲካ ተሳትፎ

ሩዋንዳ ስሟን በአለም መድረክ ካጎደፈዉ ከነበረችበት የእርስ በርስ ግጭት ወጥታ ባደረገችዉ ጥረት በአገሪቱ የሴቶችን መብት በማክበር የፓለቲካ ተሳትፏቸዉን ከፍ ያደረገች ግንባር ቀደም በማደግ ላይ ያለች አገር ተባለች።

30 በመቶ የሚሆነዉን የፓርላማ መቀመጫ በሴቶች እንዲያዝ በማድረግ በፃታ እኩልነት ረገድ በማደግ ላይ ያሉ 17 አገራት ከፍተኛ ዉጤት ማስመዝገባቸዉ ነዉ ባለፈዉ ሳምንት ማለቂያ አካባቢ ይፋ የሆነዉ።
በአለም የሴቶችን የፓለቲካ ተሳትፎ በሚያሳየዉ የዘንድሮዉ የአለም ካርታ መሰረትም በግንባር ቀደምትነት ስማቸዉ የተጠቀሰዉ ሰባቱ አገራት ሩዋንዳ፤ ኩባ፤ ኮስታሪካ፤ ሞዛምቢክ፤ አርጀንቲና፤ ደቡብ አፍሪካና ጉያና ናቸዉ።
ከ11 አመት በፊት በ13 ሳምንታት ጊዜ ዉስጥ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ ምናልባትም አብዛኛዉ የቱትሲ ጎሳ ያለቀባት ሩዋንዳ የሰዉ ዘር የተጨፈጨፈባት አሰቃቂ ቦታ ተደርጋ ትታይ ነበር።
ሆኖም ከዚያ ከከፋ የእርስ በርስ እልቂት በኋላ በአገሪቱ የመልሶ ማቋቋም ሂደት በየቀበሌዉ አስተዳዳሪነት ከፍተኛ ሚና የተጫወቱት ሴቶች ነበሩ።
በአገሪቱ የነበረዉ የሽግግር ዘመን ህገመንግስት የተረቀቀበት ወቅት ሲሆን መሪዎቹ የህግ ምሁራንን በማሳተፍ ከፃታ ጉዳዮች አንፃር እንዲያዩት አድርገዋል።
በዚያን ወቅትም ሴቶችን ለምርጫ እንዲዘጋጁ የሚረዳ ተደጋጋሚ ስልጠና በመስጠት ተሳትፏቸዉ እንዲጨምር ለማድረግ ጥረዋል።
በወቅቱ የወጣዉ ህገ መንግስትም በአገሪቱ ፓርላማና በሃላፊነት ቦታዎች ላይ ቢያንስ 30 በመቶ የሚሆነዉ በሴቶች መያዝ እንዳለበት ያዝዛል።
ባለፈዉ አመት ምርጫ ካካሄዱ 58 አገራት መካከል 49 የሚሆኑት በፓርላማ ዉስጥ የሚሳተፉትን ሴቶች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደጋቸዉ ተመዝግቧል።
ከየት እንደተነሳ ሲታይ በመንግስት አስተዳደር የሚገኙ የሴቶች ቁጥር እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም የሚሉት ታዛቢ አሁን በሁሉም አካባቢዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ከ15 በመቶ በላይ በልጦ መታየቱን ነዉ የሚናገሩት።
ከአምስት አመት ወዲህ በተደረገዉ ጥናት መሰረትም የሴት የፓርላማ አባላት ቁጥር ከ13.4 በመቶ ወደ 15.7 በመቶ ለዉጥ ታይቷል።
ታዛቢዎች እንደሚሉት ይህ አሃዝ በቂ ነዉ ባይባልም በፃታ ዉክልና ረገድ ለተፈጠረዉ ለዉጥ ቀናና የሚያበረታታ ምልክት ነዉ።
መረጃዉ እንደሚተነትነዉ በማደግ ላይ ባሉ አገራት በምጣኔ ሃብቱና በአስተዳደር ረገድ ከፍተኛና ጠቃሚ ሚና እየተጫወቱ የሚገኙት ሴቶች በመሆናቸዉ በፓለቲካዉ ዘርፍም የመሳተፍ ፍላጎት ይታያል።
በተጨማሪም በርካታ ሴቶች ከመቼዉም ጊዜ በበለጠ ከፍተኛ ትምህርት የመከታተል እድል አግኝተዋል።
ያም ሆኖ ግን ባለፈዉ አምስት አመት ዉስጥ በርዕሰ ብሄርነት ወይም በጠቅላይ ሚኒስርነት ደረጃ ላይ የደረሱ ሴቶች ቁጥር ሲታይ ከፊሊፒንስና ከሞዛምቢክ በቀር ተመሳሳይ ሁኔታ ነዉ በየአገራቱ የሚታየዉ።
በዚህ አመት በፃታ እኩልነት ዙሪያ የተደረጉት እንቅስቃሴዎችን አስመልክቶ የቀረበዉ የጥናት ዉጤት ሩዋንዳና ስዊድን ከፍተኛ ለዉጥ ያታየባቸዉ አገራት ብሏቸዋል።
በአንፃሩ ብዕራባዊ ስልጣኔና ዲሞክራሲ በጥንካሬያቸዉ የሚጠቀሱ አገራት የታሰበዉን ያህል ተሳትፎና ለዉጥ አላሳዩም።
ለምሳሌ በወጣዉ መስፈርት መሰረት ብሪታንያ 49ኛ፤ ዩናይትድ ስቴትስ 60ኛ እንዲሁም ፈረንሳይ 71ኛ መሆናቸዉ ነዉ የተገለፀዉ።ታዛቢዎቹ እንደሚሉት ይህ እጅግ ተስፋ አቆራጭና አሳፋሪ ነዉ።
በጥናት የደረሱበት እዉነታም ከበለፀጉት አገራት ይልቅ በማደግ ላይና በሽግግር ሂደት ዉስጥ ባሉት አገራት ሴቶች የተሻለ የፓለቲካ ተሳትፎ አላቸዉ።ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካ የመከላከያ ምክት ሚኒስትሯን ጨምሮ በርካታ ከፍተኛ ሴት ሚኒስትሮች ሲኖሯት የፓርላማዉ አፈጉባኤና ምክትሏ ሴቶች ናቸዉ።ተዛማጅ ዘገባዎች