የሴቶች ቀን እና ጥቃት | ዓለም | DW | 08.03.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የሴቶች ቀን እና ጥቃት

የሴቶች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲከበር 106ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ 41ኛ ዓመቱን ዘንድሮ ደፈነ። ዕለቱን አስመልክቶ የተመድ ይፋ ባደረገዉ ዘገባ ከብሪታንያ ይልቅ አፍሪቃዉያት ሴቶች በሕግ አዉች አካላት ዉስጥ በከፍተኛ ደረጃ ተሳትፏቸዉ ትርጉም ያለዉ እድገት አሳይቷል።  የዘንድሮዉ መሪ ቃልም «ተግባራዊ ለዉጥ ለሴቶች ዕኩልነት መረጋገጥ የሚል ነዉ።»

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:37

የሴቶች መብት ለኅብረተሰብ መሠረት፤

 በየመስኩ ስለሴቶች ተሳትፎ መላቅ በሚነገርበት በዚህ ወቅት በተቃራኒዉ ሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች አይነታቸዉ እየተቀያየረ መበራከታቸዉ ማሳሰቡ አልቀረም። የሴቶች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ መታሰብ ከጀመረ  ዓመታት ቢነጉዱም ዛሬም ሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች እልባት አላገኙም። ሴቶች በተለያዩ ሃገራት በፆታቸዉ ምክንያት ብቻ ለጥቃት ተጋላጭ መሆናቸዉ የመንግሥታትን ትኩረት ስቦ እነሱን በቤትም ሆነ ከሥራ ቦቸዉ ከሚደርስባቸዉ ልዩ ልዩ ጥቃት ሊከላከል የሚችል ሕግ በተመድ በይፋ ጸድቋል። አባል ሃገራትም ተቀብለዉታል። በተለይም በጎርጎሪዮሳዊዉ 1993ዓ,ም የድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ያወጣዉ መግለጫ የሴቶች እኩልነት፣ ደህንነት፣ ነፃነት እና ክብር መጣስ እንደማይኖርበት ይደነግጋል። የአባል ሃገራት ሕግም ለዚህ በቂ ጥበቃ እንዲያደርግም ያሳስባል። ይህም ሆኖ ግን ሴቶች ላይ የሚደርሰዉ ጥቃት ግን ዛሬም የሚያባራ አይመስልም። ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን ኢትዮጵያ ዉስጥ ሴቶች ላይ የሚደርሰዉ ጥቃት መበራከቱን ታዝቧል።

ዕድሜያቸዉ ሳይደርስ ለጋብቻ የሚሰጡት አዳጊ ሴቶች ላይ የሚፈፀመዉ በደል እንዳለ ሆኖ ጋዜጠኛ ጌጡ የጠቀሰዉ በፍቅር ስም ከሰሞኑ ሕዝብ በሚበረክትበት የአዲስ አበባ ጎዳና ላይ በጠራራ ፀሐይ የተፈጸመዉም ፆታ ሳይለይ የብዙዎችን ልብ ሰብሯል።

የ17 ዓመቷ  የ10ኛ ክፍል ተማሪ ኑሀሚን ጥላሁን ወድጄሻለሁ በሚላት ወጣት በስለት ተወግታ ሕይወቷ ናለፉ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን ተጠቃሚዎችን ትኩረት የሳበ መነጋገሪያ ሆኗል። በስሙ በተከፈተ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ በሰፈረ አስተያየት ምክንያት የበኩሉን ሃሳብ እንዲያካፍለን የጠየቅነዉ አርቲስት ሰሎሞን ቦጋለ ምንም እንኳን በስሙ ወደ 12 የሚሆኑ የፌስ ቡክ ገጾች ቢኖሩም አንዳቸዉም የእሱ እንዳልሆኑ ገልጾ፤ ሴት ላይ ጥቃት ሲፈጸም  ለአንድ ሰሞን በስሜት በጉዳዩ ላይ ከመነጋገር የዘለለ ነገር ብዙም አለመደረጉ እንደሚያሳስበዉ ተናግሯል። የኢትዮጵያ የሴቶች ማኅበራት ቅንጅት የኮሙኒኬሽን ኦፊሰር ወይዘሮ ትንሣኤ ወርቁ በበኩላቸዉ  ሴቶች ላይ የሚደርሰዉ ጥቃት አይነቱን እየቀያየረ መቀጠሉን ነዉ በግል ማስተዋላቸዉን ገልጸዉልናል። እንዲያም ሆኖ በዛሬዉ ዕለት ሴቶች ላይ ስለሚደርሰዉ ጥቃት ብቻ ሳይሆን ስኬታቸዉ ላይ የምናተኩርበት ቀን ነዉ ይላሉ።

ከዚህም ሌላ  ወ/ሮ ትንሣኤ በሴቶች ላይ የሚደርሰዉን ጥቃት የማስቆሙ ኃላፊነት የሴቶች ብቻ መሆን የለበትም ባይ ናቸዉ።

የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ዘርፍ ዕለቱን ምክንያት አድርጎ ይፋ ባደረገዉ መግለጫ፤ በበርካታ ሃገራት የሴቶችን መብት የማክበሩ ርምጃ ከስኬት ይልቅ ወደ ኋላ የማዝገም አካሄድ እያሳየ መሆኑን አመልክቷል።  ከምንም በላይ ሴቶች በአካላቸዉ እና ሕይወታቸዉ ላይ የመወሰን መብት እንደተነፈጋቸዉም በቅርብ የተከናወኑ አሉታዊ ድርጊቶችን በመጠቆም አሳይቷል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች