የሴት ልጅ ግርዛት በጀርመን | ጤና እና አካባቢ | DW | 07.06.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

የሴት ልጅ ግርዛት በጀርመን

እንደ ሰብዓዊ የመብቶች ተሟጋቹ ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽናል መዘርዝር አውሮፓ ውስጥ 500 000 የሴት ልጅ ግርዛት ሰለባዎች ይኖራሉ። ይህ አይነቱ በብዛት በአውሮፓ በሚኖሩ አፍሪቃውያን የሚፈፀመው በህግ የሚያስጠይቅ ድርጊት ጀርመን ውስጥ የራሱ የሆነ የወንጀል መቅጫ አንቀፅ የለውም።

ባለፈዉ ሳምንት ማለቂያ በጀርመኗ ዱስልዶርፍ ከተማ ሀኪሞች፣ ጠበቆች፤ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች እና በዘርፉ ልምድ ያላቸው ወገኖች ተሰባስበዉ፤ ይህን ድርጊት የሚፈፅሙ ወገኖችን ስለማጋለጥና ታዳጊ ሴት ልጆችን ከግርዛት ስለመታደግ ተወያይተዋል።

ያዋሂር ኩማር ሶማሊያዊት ናት። እንደ አብዛኛው የሶማሊያ ልጃገረዶች ተገርዛለች። ሌሎች ሴት ታዳጊ ህፃናትም እሷ ያለፈችበት አሰቃቂ ጎጂ ልማድ ሰለባዎች እንዳይሆኑ ስትል አኢአ 1996 ዓ ም ጀርመን ውስጥ የሴት ልጅ የመዋለጃ አካላትን ትልተላ ይቁም! STOP MUTILATION -የሚል ማህበር ታቋቁማለች። ምክር የምትለግሳቸው ሴቶች ብዙ ችግር አለባቸው። አንዳንዶቹ የመኖሪያ ፍቃድ የላቸውም፤ ያላቸው ደግሞ ደፍረው ወደ ሀኪም ቤት ሲያመሩ የጤና የመድህን ዋስትና ሰጪዎች በግርዛቱ ሂደት የተደፈነዉን የመዋለጃ አካላቸዉን ለመክፈት ለሚፈለገዉ ቀዶ ጥገና አይከፍሉም ትላለች።

«ሴቶቹ የትኛውም የጤና መድህን ዋስትና ሰጪ የቀዶ ጥገናውን ወጪ ለመሸፈን ፍቃደኛ እንዳልሆነ ነው የሚገልፁልኝ። እነሱ የ ሶስት ወይንም የአራት ዓመት ልጅ ሳሉ ነው የተገረዙት። አሁን 35 አመታቸው ነዉ እንበልና ተሰፋው ብልታቸው እንዲከፈት ይፈልጋሉ። በዚህ ጊዜ ጥያቄ ይነሳል፤ ለምንድን ነው ይህ የሚሆነዉ እድሜያቸውን በሙሉ እንደዚህ ነበሩ አሁን ችግሩ ምኑ ላይ ነው ይላሉ። ብዙዎቹ ለዉበት ሲባል የሚደረግ ቀዶ ጥገና ይመስላቸዋል። ነገር ግን ለህይወት ወሳኝ የሆነ ነገር ነው። ይህን ግልፅ ሊደረግላቸው ይገባል።»

Die Somalierin Jawahir Cumar berät beschnittene Frauen in Deutschland. Bild: Priya Palsule

ያዋሂር ኩማር የምክር አገልግሎት ስትሰጥ

ሴቶች ላይ የሚፈፀመዉ የግርዛት አይነነት ይለያያል። በከፊል ወይንም ሙሉ በሙሉ የመዋለጃ አካላቸዉ የሚተለተልበት፣ ከዚህም አልፎ ትንሽዬ ቀዳዳ ብቻ ለሽንት ተትቶ ሙሉ በሙሉ የሚሰፋበት። ጀርመን ውስጥ ከ25,000 እስከ 50,000 የሚደርሱ ለግርዛት ሰለባ ሊሆኑ የሚችሉ ልጃገረቾች አሉ ተብሎ ይገመታል። በውጭው አለም የሚኖሩ በርካታ አፍሪቃውያን ባህላችን ብለው የሚጠሩትን ጎጂ ልማድ ከመፈፀም አልተቆጠቡም። ስለሆነም ጀርመን ውስጥ የራሱ የሆነ የወንጀለኛ መቅጫ አንቀፅ ያስፈልገዋል ይላሉ ጠበቃ ዲርክ ቩስትንበርግ።

«አሁንም ቅጣቱ እንዳለፉት አስርት ዓመታት ቢበዛ 10 ዓመት ነው። ነገር ግን ካለፉት የሥራ ልምዶች ስንመለከት ለእንደዚህ አይነቱ የአካል ጉዳት ከ 3-4 አመት የመጀመሪያዎቹ ወንጀለኞች፤ ማለትም ወላጆች ላይ ይበየናል። ገራዦቹ ደግሞ 8 ዓመት። በአሁኑ ሰዓት የጀርመን ምክር ቤት የሚበየነውን ቅጣት አስመልክቶ ውይይት እያካሄደ ነው።»

እንደ ያዋሂር ኩማር ያሉ ሴት ተሟጋቾች ወደ ጎረቤት አገር ፈረንሳይ በቅናት ይመለከታሉ። ለምን ቢባል ፈረንሳይ ሴት ልጃቸውን የሚያስገርዙ ወላጆችን ከ10-30 አመት እስራት ትቀጣለች ወይንም ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመለሱ ታደርጋለች። ትዉልደ ማላዊዋ ናና ካማራ ፈረንሳይ ውስጥ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሠራተኛ ናቸው። ጀርመን ከፈረንሳይ ልትማር ትችላለች ስላሉት ስትገልፁ፤

«ጊዜ ቢወስድም ተስፋ አላቸዉ። ይህንን ጉዳይ ለመረዳት እና ለማሳወቅ እንዲሁም ዛሬ ፈረንሳይ የደረሰችበት ለመድረስ ጊዜ ፈጅቶብናል። ይህ ተሞክሮም ምናልባት ኔዘርላንድስ እና ጀርመን ሂደቱን ለማሳጠር ይረዳቸው ይሆናል።»

ጀርመን ዉስጥ ያለዉ ችግር ይህ ብቻ አይደለም፤ ሀኪሞች መረጃ አሳልፈው እንዳይሰጡም ህግ ይከለክላቸዋል። ይህም እንዲህ ባለዉ አጋጣሚ የወንጀር ክትትል እንዳይካሄድ እክል ሆኗል። ዶክተር ክርስቶፍ ሴርም፤ የማሕፀን ሀኪም ናቸው። ከ STOP MUTILATION ማህበር ጋ በትብብር ይሰራሉ። ተጎጂዎችን ይመክራሉ፣ ያክማሉ!

Christoph Zerm, Gynäkologe aus Herdecke, bildet Gynäkologen zum Thema weibliche Beschneidung weiter. Bild: Priya Palsule

ዶክተር ክርስቶፍ ሴርም

«ለእንዲህ ዓይነቱ ጥያቄ በግሌ አስቀድሜ ወስኜያለሁ። እንደዚህ አይነቱ ወንጀል እንደታቀደ ብሰማ፤ እንዳይፈፀም የሚረዱ መንገዶችን እፈልጋለሁ። በማንኛዉም መንገድ ቢሆን ሰለባዉን ለማዳን በተገቢዉ መንገድ የሚመለከተዉ አካል እርምጃ እንዲወሰድ ጥቆማ የሚያገኝበትን ሁኔታ አመቻቻለሁ።»

እሳቸዉ ሁኔታዉ እንዲታወቅ መጠቆም ሲሉ የግድ ወደፖሊስ ጉዳዩን ማድረስ ማለታቸዉ አይደለም። ለምሳሌ ድርጊቱ ከመፈፀሙ በፊት የወጣቶችን መብት የሚመለከተዉ ተቋም እና የጤና ድርጅቶች ለቤተሰብ የምክር አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ይችላሉ።

ናና ካማራ ለስብሰባው ባደረጉት ንግግር ፈረንሳይ ዉስጥ ብቻ ሳይሆን በትውልድ አገራቸው ማሊ እና በጠቅላላው ምዕራብ አፍሪቃ የሚገረዙ ሴቶች ቁጥር ቀንሷል ይላሉ። የጀርመኑ ማህበር ግን ምክር ቤትን የሚያወያየዉ ህግ ተግባራዊ እስኪሆን ገለፃ እየሰጠ መጠበቅ ግድ ይለዋል። ምናልባት ይህ ህግ ሰዎች ደፍረው ወደ ወንጀል መከታተያ እንዲሄዱ እና እንዲጠቁሙ ይገፋፋል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ እንግዲህ የ5,000 ዓመቱን ጎጂ ልማድ ለማጥፋት ትንሽ ይሁንና ተስፋ ሠጪ ርምጃ መሆኑ ነው።

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 07.06.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/158kY
 • ቀን 07.06.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/158kY