የሴራሊዮናዊዉ ሞትና የፍርድ ዉሳኔ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 04.09.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የሴራሊዮናዊዉ ሞትና የፍርድ ዉሳኔ

አንድ የጀርመን ፍርድ ቤት በእስር ላይ ሳለ በእሳት ቃጠሎ ሕይወቱን ባጣ የዉጭ ዜጋ ጉዳይ በፖሊስ ላይ ያሳለፈዉን ፍርድ አጸና። ካልስሬኸ ከተማ የሚገኘዉ የፌደራሉ መንግሥት ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሴራሊዮናዊዉ እስረኛ በንዝህላልነት ሕይወቱ ጠፍቷል በሚል ከዚህ ቀደም በፖሊስ ላይ የተጣለዉን የገንዘብ ቅጣት ዛሬም በድጋሚ አፅንቶታል።

ዑሪ ጃሎ የተባለዉ ሴራሊዮናዊ በጎርጎሪዮስ የዘመን ቀመር 2005 ዓ,ም ጥር ወር መጀመሪያ አካባቢ ዴሳዉ በተባለች ከተማ በታሠረበት የፖሊስ ጣቢያ እንዳለ በእሳት ተቃጥሎ ሕይወቱ ያልፋል። ክስተቱ ብቻ ሳይሆን የጥገኝነት ጠያቂዉ ሕይወት ሊያልፍ ቻለ ተብሎ የቀረበዉ ገለጻ በመላዉ ጀርመን የመገናኛ ብዙሃን ብቻ ሳይሆን የሕዝብ መነጋገሪያ ሆነ። እንዲህ ነዉ የሆነዉ፤ በአንድ ምሽት ፖሊስ ከአራት ሴቶች አቤቱታ ቀረበት።ጃሎ ተንቀሳቃሽ ስልካቸዉን የራሱን ጥሪ ሊያደርግበት ጠየቀን በዚህም አስገደደን አስፈራራን የሚል ነዉ ክሱ። ፖሊስ እንደደረሰ ማንነቱን የሚገልፅ ማስረጃ ጠየቀ፤ ሆኖም ፖሊስ እንደሚለዉ በቁጣና በኃይለ ቃል በመፋጠጡ ወደፖሊስ ጣቢያ ተወሰደ። እዚያም ዶክተር እንደሰከረ አረጋገጠ። ሆኖም ዑሪ ጃሎ ወደሃኪም ቤት ሳይሆን መታሠር እንደሚችል ገለጸ። ከተፈተሸ በኋላ ፖሊስ ጣቢያዉ ምድር ቤት በሚገኝ ክፍል ዉስጥ ዶክረቱ ራሱን እንዳይጎዳ ባለዉ መሠረት እጅና እግሩ ታሥሮ ተቀመጠ። እንዲያም ሆኖ ጃሎ ብቻዉን መተዉን ነዉ መረጃዎች የሚያመለክቱት። በወቅቱ በጣቢያዉ ተረኛ የነበረዉ የፖሊስ መኮንን ከባልደረባዉ ጋ ባሉበት የሆነ ታች ካለዉ የእስር ክፍል የተለየ ድምፅ ይሰማሉ።

ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ገደማ ጭስ ሲጨስ የሚያመላክተዉ የማስጠንቀቂያ ደወል ጮኸ ቁብ የሰጠዉ የለም። የተፈጠረዉ ከታወቀ በኋላ ፖሊሶቹ ተጠይቀዉ የሰጡት ምላሽ ያ የእሳት አደጋ ማስጠንቀቂያ እየተበላሸ በተደጋጋሚ የተሳሳተ ማስጠንቀቂያ ይሰጥ ነበር የሚል ነዉ። የእሳት አደጋ ተከላካይ ብርጌድ በስፍራዉ ሲደርስ ግን ዑሪ ጃሎ እጅና እግሩ እንደታሠረ በቃጠሎዉ ሕወቱን አጥቶ ያገኛል። ፖሊስ ጃሎ በያዘዉ እሳት መለኮሻ ራሱን ማቃጠሉን ይገልጻል። ተቺዎች ግን ጥንብዝ ብሎ የሰከረ እጅና እግሩ የታሰረ ሰዉ እሳት በማያነደዉ ፍራሽ ላይ እሳት ለኩሶ ራሱን አቃጠለ የሚለዉ አያሳምንም ባይ ናቸዉ። ጥርጣሬዉ ከፍ የሚለዉም ጃሎ ሲታሠር ከተመዘገቡት እቃዎቹ መካከል እሳት መለኮሻዉ አለመኖሩ ነዉ። የእጅ አሻራዉም ቢሆን በተደረገ የDNA ምርመራ አልተገኘም እንደዘገባዎች ትንታኔ። ጃሎ ከሞተ ከሁለት ዓመታት በኋላ አቃቤ ሕግ ጉዳዩን ወደፍርድ ቤት አቀረበ። አቃቤ ሕግ ታሳሪዉ ሕይወቱን አጠፋ የሚለዉን እንደመነሻ በመያዝም በወቅቱ ተረኛ የነበሩትን ሁለት ፖሊሶች ለሞት የሚያደርስ አደጋ በማድረስ ይከሳል። ፍርድ ቤትም ከመጀመሪያዉ ሟችን ወደፖሊስ ጣቢያ ወስዶ ማስር አልነበረባቸዉም ሲል ይወስናል። በፖሊሶቹ ላይም የ10,800 ዩሮ ቅጣት ይበይናል። ዘግየት ብለዉ የወጡ የአስከሬን ምርመራ ዉጤቶችም ጃሎ መደብደቡን ያሳያሉ። በደረሰበት ድብደባ ቀልቡን በመሳቱም እሳት ሲቃጠል እንዳልሰማ ከምርመራዉ ዉጤት ተነስቶ ተገምቷል። የዛሬ ስድስት ዓመት ጉዳዩን ፍርድ ቤት ሲመለከተዉ ዳኛዉ በትክክል ምን እንደተፈፀመ በተጨባጭ መግለጽ ባይቻልም ከተገኙት መረጃዎች በመነሳት ፖሊሲቹ የሕግን የበላይነት እንዳላከበሩ ግልፅ አድርገዉ ነበር።

የቀድዉን የቅጣት ዉሳኔ ያፀናዉ ካልስሩኸ ከተማ የሚገኘዉ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቃል አቀባይ ካሪን ሚልጋ ታሳሪዉ ራሱን አጥፍቷል ቢባልም ተገቢዉ ክትትል ተደርጎ ቢሆን ኖሮ ያንን ማስቀረት ይቻል እንደነበር ነዉ ያመለከቱት።

«የፌደራል ፍርድ ቤት ከክፍለ ግዛቱ ፍርድ ቤት ባገኘዉ መረጃ መሠረት ዑሪ ጃሎ ህይወቱን ያጣዉ ራሱ ባመጣዉ የእሳት መለኮሻ አማካኝነት ነዉ ብሎ ማረጋገጡን ተቀብሎታል። ይሁንና ተከሳሹ ይህን በንቃት በመከታተልና በመቆጣጠር ቃጠሎዉ እንዳይደርስ ማድረግ ይችል እንደነበርና ማድረግም ይገባዉ እንደነበር ነዉ ያረጋገጠዉ።»

በዚህ መሠረትም የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፖሊስ ባሳየዉ ግድየለሽነት ለሞት መዳረጉን ገልጿል። በፍርድ ቤቱ የተገኘዉ የሟች ወንድም ግን በዉሳኔዉ አልተደሰተም፤ እሱ ፖሊስ በሕይወት ምጥፋት መጠየቅ አለበት ባይ ነዉ።

«በዚህ ፍርድ በጣም አዝኛለሁ በጣምም ተገርሜያለሁ። ወንድሜ የተያዘበትን ሁኔታ በትክክል የመረመረ ማንም ሰዉ አንድ ስህተት መፈፀሙን በደንብ ይረዳዋል።»

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic