የሳይንስ ምርምርና ሽልማት በጀርመን | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 01.04.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የሳይንስ ምርምርና ሽልማት በጀርመን

በጀርመን ሀገር ሳይንስና ሥነ-ቴክኒክ ዐቢይ ትርጉም የሚሰጠው በመሆኑ፣ ከዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ሌላ፣ በተለያዩ ከተሞች በዛ ያሉ የምርምር ተቋማት ይገኛሉ።

default

ከቆዳ ሥር፣ የደም ሥሮችን ሳይቀር ማንሳት የሚያስችል ረቂቅ ፎቶግራፍ ማንሻ በመፈልሰፍ፣ አምና ከተሸለሙት መካከል ፣ የ 20 ዓመቱ ወጣት፣ እሽቴፈን እሽትሮብል፤ ከትምህርትና ምርምር ሚንስትር ወ/ሮ አኔተ ሻቫን ጋር፣

ተቋማቱ በሀገር ውስጥም በዓለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን ይወዳደራሉ። እንደምርምራቸው ውጤት ጉልኅነት ደግሞ፣ ሽልማት ያገኛሉ፣ ይቀባላሉም። በጀርመን ሀገር ከታውቁት ሽልማቶች አንደኛው በታወቁት ጀርመናዊው የአቶም ፊዚክስ ሊቅ Heinz Maier-Leibnitz ሥም የሚሰጠው ነው። ዘንድሮ የተመደበውን 2,5 ሚሊዮን ዩውሮ ሽልማት 10 ሳይንቲስቶች ያገኙ ሲሆን ፣ ከገንዘቡ ይልቅ፣ የምርምሩ ነጻነት ያረካቸው መሆኑን ነው ተሸላሚዎቹ የገለጡት። የጀርመን የምርምር ማኅበረሰብ ፕሬዚዳንት ማቲያስ ክላይነር ---

«በ ላይብኒትስ ሽልማት ከፍተኛ የሳይንስ ምርምር እንዲካሄድ ፣ ከ 25 ዓመት በፊት ማበረታቻው ሲቀርብ፣ በጀርመን ሀገር ፣ ሳይንስ ነጻ እንደወጣ ያህል ነው የተቆጠረው። ይህም ፣ በዩኒቨርስቲዎች ይጠበቅ ከነበረው ፣ እ ጎ አ በ 1970ኛዎቹና 80ኛዎቹ ዓመታት ፣ ከአነስተኛ ክፍፍልና ከሚያስገድድ ሁኔታ፣ እንዲሁም ከሚጠበቅ የምርምር ውጤት ራስን ነጻ ማድረግ ሆኖ ነው የታየው።»

የላይብኒትስ ሽልማት ካገኙት መካከል አንዱ ክሪስቶፍ ክላይን፣ በተፈጥሮ በሽታን የመከላከል አቅም የሌላቸው ህጻናት እንዴት የህክምና እርዳታ አግኝተው ሊድኑ እንደሚችሉ በተግባር ያሳዩ ናቸው። ለምሳሌ ያህል ቶም የተባለው ህጻን ልጅ፣ በሽታን የመከላከል የተፈጥሮ አቅሙ ደካማ ስለነበረ፣ ህልውናውን ሊያጣ ይችል ከነበረበት ሰደጋ ተላቆ፣ በክላይን የህክምና ጥበብ ጤናማ ሆኖ ኑሮውን መምራት ችሏል። ሽልማቱ ታዲያ፣ ያለግፊት ያለውል ፣ ያለአስገዳጅ አቅድ፣ ዘና ብለው እንደሚራመሩ ያስቻላቸው መሆኑን ነው የሚናገሩት።

«ሽልማቱ፣ ኀላፊነት ይበልጥ እንዲሰማንና በሥራችን እንደንተጋ የሚያደረግ ፣ ነጻነትም የሚያጎናጽፈን በመሆኑ ትልቅ ትርጉም አለው። ከአንግዲህ፣ አዳዲስ በሮች ሊከፈቱልን ይችላሉ፣ አዲስ ምርምር ማካሄድ ያስችለናል፣ ስለአዳዲስ የበሽታ ዓይነቶች ይበልጥ ግንዛቤ እንዲኖረንና ምናልባትም አንድ ቀን የተሻለ የህክምና ዘዴ እንድንፈጥር ያስችለን ይሆናል።»

የላይብኒትስ ሽልማት መሰጠት ከተጀመረ 25 ዓመት ሲሆን፣ ስኬታማ ታሪክ እንዳለውም ይነገርለታል ። የላይብኒትስን ሽልማት ካገኙት መካከል 6ቱ በመጨረሻ የኖቤል ሽልማት ለማግኘት መብቃታቸው ታውቋል። ዘንድሮ ድርጅቱ ለ 10 ተመራማሪዎች ሲሆን ሽልማት የሰጠው፣ አንደኛዋ ብቻ አነስታይ ተመራማሪ ሲሆኑ የተቀሩት ወንዶች ናቸው። ብቸኛይቱ ሴት ተሸላሚ፣የ 41 ዓመቷ ፣ የ 3 ልጆች እናት የሆኑት፣ በድሬስደን ከተማ በሚገኘው የቴክኒክ ዩኒቨርስቲ ፣ በሥነ-ህይወታዊ ፊዚክስ ላይ ያተኮሩት ፕሮፌሰር Petra Schwille ናቸው።

«በመጀመሪያ ደረጃ፣ አርኪ የሆነ ለሥራዬ የተሰጠ ከበሬታ ሲሆን፣ በተጨማሪ ለቀጣዩ የምርምር ትልሜ ጠቀሚ ወረት ነው። በሚመጡት ዓመታት ፣ ሰፊ ነጻነት አስገኝቶልኝ፣ ትንሽ ውጤታማ ላይሆን በሚችል፣ በሳይንስ ያን ያህል ባልተደላደለ ፕሮጀክትም ላይ ለማትኮር ያስችለኛል።»

ሽቪለ፣ እ ጎ አ ከ 2002 ዓ ም አንስቶ፣ በተጠቀሰው ዩኒቨርስቲ፣ የስነ-ህይወታ ፊዚክስ ፕሮፌሰር ናቸው። ፊዚክስንና ሥነ ህይወትን ለምን እንዳጣመሩም ሲያብራሩ---

«ፊዚክስ፣ ውስብስብ ያሉ ሳይንሳዊ ፈታኝ ነገሮች በሂሳብ መልክ መፍትኄ እንዲገኝላቸው የሚያደርግ የሳይንስ ዘርፍ ነው። ሥነ ህይወት ደግሞ መስጦኝ የኖረ የሳይንስ ክፍል ነው። ህይወታ ያላው ሥርዓት እንዴት አንደሚሠራ ለማወቅ ጽኑ ፍላጎቱ አለኝ። ሥነ- ህይወት፣ ከመደበኛው ፊዚክስና ሥነ-ቅመማ ይለያል። ብዙው ነገርም ገና በጥሞና አይታወቅም።

ብዙ መሠረታዊ ጥያቄዎች አሉ፣ ገና መልስ ያላገኙ። ፊዚክስ ከመጀመሪያውም ምርምርን በዘዴ መምራት የሚያስችል ቁልፍ ነው።»

ታዲያ ፕሮፌሰር ፔትራ ሽቪለ፣ ፊዚክስን እንደ መመራመሪያ ዘዴ በመጠቀም በሰውነት ውስጥ በተለያዩ አካላት የሚገኙ ኅዋሳትን በጨረር ጎልተው እንዲታዩና ለመመራመር እንዲያመቹ በማድረግ ነው ፣ የተሳካ ውጤት ማግኘታቸው የተነገረላቸው። በዚህ አሠራር ዘዴም ነው ሽቪለ ፣ «የጀርመናውያን ኖቤል ሽልማት» የሚሰኘውን የዘንድሮውን የላይብኒትስ ሽልማት ለማግኘት የበቁት። የልጆች እናት ሆኖም በእንዲህ ዓይነት ሳይንሳዊ ምርምር ማትኮር እንደማያዳግት የገለጡት ሳይንቲስት፣ ጀርመን ሴቶችን ይበልጥ ልታበረታታ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በጀርመን ሀገር እንደ ላይብኒትዝ የሽልማት ድርጅት ሁሉ፣ በተለይ ወጣት ተማራማሪዎችን ይበልጥ የሚያበረታታው Jugend Forscht (ወጣቱ ይመራመራል) እንደማለት ነው በዚህ ሥያሜ የሚታወቀው ድርጅትም ሊጠቀስ የሚገባው ነው። ይህ ፣ በያመቱ በተለያዩ ከተሞች የሚካሄደው የፈጠራ ውጤቶችን ማሳያ ውድድር ከተጀመረ ዘንድሮ 45 ዓመቱ ሲሆን የዘንድው ውድድር በኖርድ ራይን ቬስትፋለን ፌደራል ክ/ሀገር፣ በሩር አውራጃ በምትገኘው፣ ከጀርመን ከተሞች በስፋት 5ኛ ደረጃ ላይ በምትገኘው Essen በተሰኘችው ከተማ ነው፣ ከግንቦት 5-8, 2002 የሚካሄደው። የውድድሩ አዘጋጅ ጽ/ቤት ከሐምበርግ ትናንት እንዳስታወቀው፣ 10,196 ወጣቶች ናቸው፣ ለውድድር የተመዘገቡት። የወጣት ሴቶች ድርሻ 36 ከመቶ ነው። አጠቃላዩ አኀዝ ካምናው ጋር ሲነጻጸር የ 1,3 ከመቶ ጭማሪ አሳይቷል። በብሬመን፣ ኒደርሳኽሰንና ሄሰን ፌደራል ክፍላተ ሀገር አሸንፈው በሄሰኑ ውድድር የሚሳተፉት የተገለጠ ሲሂን፣ የሌሎቹ ፌደራል ክፍላተ ሀገር አሽናፊዎች ከዛሬ አንስቶ እስከ ፊታችን እሁድ ተለይቶ ሊታወቅ እንደሚችል ተመልክቷል።

«ዩገንድ ፎርሽት» በ 7 የተለያዩ የሳይንስ የምርምር ዘርፎች ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ በዘንድሮው ውድድር ከወዲሁ ላቅ ያለ ግምት ከተሰጣቸው መካከል የግል መኖሪያ ቤቶችን ፣በቁጠባ፣ በተሟላ ሁኔታ የሚያሞቅ ዘመናዊ መሳሪያ ፣ ባልቴቶችና ሽማግሌዎች በሚኖሩባቸው ማዕከላት የአስቸኳይ እርዳታ ማግኘት የሚችሉበት ቀላጣፋ ዘዴ፣ ፣በኤልክትሪክ አጠቃቀም ሳቢያ አደጋ ቢደርስ ፣ በአንድ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ሊያውቁ የሚችሉበት ዘዴና የመሳሰሉት ናቸው።

ዩገንድ ፎርሽት (የወጣቶች ሳይንሳዊ የምርምር ውድድር)በጀርመን ሀገር ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲካሄድ ያበቁት ሳይንቲስት ሳይሆኑ ጋዜጠኛ ነበሩ። እርሳቸውም STERN (ኮከብ)በሚል ርእስ የሚታወቀው መጽሔት የረጅም ጊዜ ዋና አዘጋጅ የነበሩት ሄንሪ ናነን ናቸው። ከዩናይትድ እስቴትሱ (Science Fairs) ዝግጅት ሐሳብ የቀሰሙት ናነን፣ እ ጎ አ በ 1965 ዓ ም፣ Wir suchen die Forscher von Morgen «(የነገዎቹን ተማራማሪዎች እንፈልጋለን! » በሚል መፈክር ያሰሙት ጥሪ ውድድሩ በዓመቱ በ 1966 ዓ ም እንዲጀመር አበቃ። የተጠቀሰው ውድድር ሲካሄድ ዘንድሮ 45 ኛ ዓመት ሊሆነው ነው። ሳይንስ ለኤኮኖሚ ብቻ ሳይሆን ለአጠቃላይ ዕድገትም መሠረት በመሆኑ ጀርመን በአገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ፣ ዐቢይ ግምት ትሰጠዋለች።

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ