የሳዑዲ ተመላሾች የስነልቦና እና ማህበራዊ ጉዳት | ዓለም | DW | 21.06.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የሳዑዲ ተመላሾች የስነልቦና እና ማህበራዊ ጉዳት

ሳዑዲ አረቢያ ህገ ወጥ ያለቻቸውን ወደ 164 ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያንን ከሶስት ዓመት በፊት ማባረሯ የሚታወስ ነው፡፡ ተመሳሳዩን እርምጃ ለመድገም የሰጠችው ቀነ-ገደብ ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት ቀርተውታል፡፡ ያኔ ወደ ኢትዮጵያ በተመለሱ ኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰውን የስነልቦና እና ማህበራዊ ጉዳት ባለሙያዎች ጥናት አካሄደውበታል፡፡ 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:12

በስነልቦና እና ማህበራዊ ቀውስ እንደተጠቁ ተደርሶበታል

ታህሳስ 2006 ዓ.ም፡፡ የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) ማስተናገጃ ግቢ ውስጥ ከሳዑዲ አረቢያ የተመለሱ ኢትዮጵያውያን ተሰብስበዋል፡፡ ከእነርሱ ውስጥ አንዷ የሆነችው ዘይነባ ከሰሜን ኢትዮጵያ ወሎ ወደ ሳዑዲ አረቢያ የተጓዘች ነበረች፡፡ ሪያድ ሶስት ዓመት ቆይታለች፡፡       

ያኔ እምባዋን እያዘራች ለዶይቸ ቨለ “እንደዚህ የሚሆን ስላልመሰለኝ ነው፡፡ እንደጠበቅኩት እንደተባልኩት አይደለም፡፡ ገንዘቤን አውጥቼ፡፡ ሰርቼ እንኳ አይደለም ተበድሬ ነው የሄድኩት” ብላ ነበር፡፡

የዘይነባ ድምጽ በሳዑዲ አረቢያም ሆነ በመካከለኛው ምስራቅ በቤት ሰራተኝነት የሚያገለግሉ ኢትዮጵያውያንን ስሜት የሚወክል ይመስላል፡፡ በዚያን ወቅት በግዴታ ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ኢትዮጵያውያን የደረሰባቸውን የስነ-ልቦና ቀውስ የመረመሩ ባለሙያዎች ከመደበኛው ሰው በላቀ የአእምሮ ጤና ችግር እንደለባቸው መዝግበዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሳይኮሎጂ ትምህርት ክፍል የስነ-ማህብረሰብ ሳይኮሎጂ መምህር የሆኑት ዶ/ር አበባው ምናዬ ከባልደረቦቻቸው ጋር ሆነው በ1036 ስደተኞች ላይ ባካሄዱት ጥናት 27 በመቶ ገደማው የአእምሮ ጤና ጉዳት እንዳጋጠማቸው ደርሰውበታል፡፡ ዶ/ር አበባው ጥናታቸውን ያከናወኑት የዓለም ጤና ድርጅት ያስቀመጠውን የአእምሮ ደህንነት መለኪያ ተጠቅመው ነው፡፡

“በጣም የተለያዩ ግፎች ይደራረቡና ይከማቹና መጨረሻ ላይ ጠብቀው የሄዱት ነገር አለ አይደል? በገንዘብም የተሻለ ይዞ መምጣት፣ በኑሮም የተሻለ መኖር፣ ቤተሰብን መደገፍ - እንዲህ አይነት የጠበቋቸውን ነገሮች አለማግኘት የሚያስከትለው ነገር ጭንቀት ነው፡፡ ራስን ዝቅ አድርጎ የማየት፣ ራስን ተጠያቂ አድርጎ የመውሰድ፣ ያልተሳካላት ሰው አድርጎ ራስን የመውሰድ ነገር [ይታይባቸዋል]፡፡ እነዚህ ስሜቶች ደግሞ ወደ አካላዊ ስሜት ይቀየራሉ፡፡ ለምሳሌ ራሴን አመመኝ፣ ይፈልጠኛል፣ የምግብ ፍላጎቴ ቀነሰ፣ ጨጓራዬን አመመኝ እንደዚህ እንደዚህ የሚሉ መገለጫዎች ውስጥ ይገባሉ፡፡

ሌላው በአብዛኛው ከሰዎች ጋር የሚኖራቸው ግንኙነትም የመራቅ ነገር [ይሆናል]፡፡ ምክንያቱም ሰዎቹ ‘ያልተሰካለት፣ ተመላሽ ይሉናል’ ብለው ስለሚወስዱ ነው፡፡ ለእነሱ የወጣው ያልተመለሰ ገንዘብ አለ፣ ቤተሰብ ከእነርሱ የሚጠብቀው ብዙ ነገር አለ፡፡ ያንን ስለሚያስቡ ከሰው ይርቃሉ፡፡ የመሸማቀቅ፣ የመሳቀቅ ስሜቶች ሁሉ ከዚህ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ” ሲሉ ዶ/ር አበባው በጥናታቸው ያስተዋሉትን የስነልቦና ችግር ከእነመንስኤው ያስረዳሉ፡፡

የአእምሮ ህምሞችን በሁለት የሚከፍሉት ዶ/ር አበባው አሳሳቢው “ጠንከር ያለ ቀውስ” እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በእዚህ የተጠቁቱ ራሳቸውን የማጥፋት ስሜት በየጊዜው የሚመጣባቸው እንደሆኑ ይገልጻሉ፡፡ በጥናቶቻቸው ካስተዋሏቸው ውስጥ “በመሀል ለየት ያለ ሀሳብ እየመጣ” የሚረብሻቸው ይገኛሉ፡፡ መምህሩ ለዚህ ከስደተኞቹ መካከል በምሳሌ ያጣቅሳሉ፡፡

“ለምሳሌ አንዲቱ ልጅ በቁጥሩ ከሚገለጸው ውጭ በሀተታዊ ጥናት ከገለጸችው ነው የምነግርህ፡፡ ‘የሆነ ነገር እየመጣ ምን ልታደርጊ ትመለሻለሽ? ቤተሰቦችሽ በሙሉ አልቀዋል እያለ ይነግረኛል’ ብላለች፡፡ የቀን ህልም ወይም የቀን ቅዥት የሚሉት (hallucination) ዓይነት ውስጥ ይገባሉ፡፡ አንዳንዶቹ እኮ አየር ማረፊያ ላይ ጸጉራቸውን እየነጩ የሚቆሙ አሉ፡፡ አስተሳሰባቸው፣ የማስታወስ ችሎታቸው ሁሉ ይዛባል፡፡ የቤተሰብ ስልክ ሁሉ የሚጠፋባቸው ብዙ ናቸው፡፡ ለማገናኘት የሚያስቸግሩት ማለት ነው፡፡”   

በተመሳሳይ መልኩ የሳዑዲ ተመላሾች ላይ የደረሰውን ማህበራዊ ጥናት ያጠኑት አቶ ደሳለኝ ቢራራ ስደተኞቹ ማህበራዊ ቀውስ እንደገጠማቸው በጉልህ ማስተዋላቸውን በጥናታቸው አካትተዋል፡፡

“በዚያን ጊዜ ተመልሰው ሀገር ቤት መጥተው የነበሩት ኢትዮጵያውያን ከነባር ማህበረሰባቸው ጋር የሚኖሩበት፣ ትተውት የሄዱት አኗኗር ዘይቤ ተለውጦ ያገኙት ያህል ነው የተሰማቸው፡፡ በዚያን ምክንያት ብዙዎቹ አብሮ ከመኖር ይልቅ እንደገና የመሰደድ ዝንባሌ ነበር የታየባቸው፡፡ ለማጥናት ከተሞከሩት ላይ ማስተዋል የተቻለው አንደኛ ወደ ውጭ ሀገር ሲሄዱ ቤተሰቦቻቸው ልጆቹን የሚልኩበት ገንዘብ ከተለያየ ምንጭ ተበድረው ስለሚሆን በተመለሱበት ጊዜ ያንን እንኳ ተበድረው የተላኩበትን መክፈል የማይችሉ ይሆናል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ቤተሰብ የሚጠብቃቸው ‘አምጥተው ያሳልፉልናል፣ ለችግራችን ደራሽ ይሆናሉ፣ ገንዘብ ልከው እኛን ይረዱናል’ በሚል ነው፡፡ ይህ ግምት እያለ እነርሱ በመካከል እንደውም እዳቸውን ሳይከፍሉ ሲመለሱ ራሳቸውን በራሳቸው የመውቀስ ስሜት ስለነበር ይህም ከጎረቤት እና ከአብሮ አደጎቻቸው ጋር አብሮ ለመኖር በጣም ከባድ አድርጎባቸዋል፡፡”

እንዲህ አይነትማህበራዊ ችግር የሚገጥማቸው ተመላሾች ሶስት አይነት አማራጮችን አንደሚጠቀሙ አቶ ደሳለኝ በጥናታቸው ጠቁመዋል፡፡

“አንደኛው የሚያውቃቸው ሰው ወደ ማይገኝበት ቦታ ከተማ ሄደው ከዚህ በፊት ምን አይነት ሰው እንደነበሩ ከማያውቃቸው ማህበረሰብ ጋር ተቀላቅለው መኖርን የመረጡ አሉ፡፡ ሁለተኛው አማራጫቸው ደግሞ በተለያዩ አነስተኛ በሚባል የስራ ዘርፍ ተሰማርተው እየሰሩ አረብ አገር ወይም ሳዑዲ አረቢያ ሄደው መክፈል ያልቻሉትን ዕዳ ቢያንስ ለመክፈል ጥረት ማድረግ ነው፡፡ ይህንን ማድረግ ያልቻሉና አእምሯቸው ያልተቀበለላቸው ግን አሁንም ድጋሚ በህገወጥ መንገድ፣ ባህር አቆራርጠው፣ በግድ ወደወጡበት፣ ወደተባረሩበት ሀገር ተመልሰው መሄድ የመረጡ በርካቶች ናቸው፡፡”    

አጥኚዎቹ በቀደምት የሳዑዲ ተመላሾች ላይ በታዘቡት ላይ ተመስርተው የስነልቦናም ሆነ ማህበራዊ ቀውስ እንዳይገጥማቸው በቂ ትኩረት ተሰጥቶ አልተሰራም ይላሉ፡፡ ተመሳሳይ ችግር በድጋሚ እንዳይከሰት ቅድመ ዝግጅት መደረግ እንዳለበት ይመክራሉ፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ

   

 

 

Audios and videos on the topic