የሳውዲ ዐረቢያ እና የዩኤስ አሜሪካ ግንኙነት | 1/1994 | DW | 09.08.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

1/1994

የሳውዲ ዐረቢያ እና የዩኤስ አሜሪካ ግንኙነት

የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ እአአ ሰኔ 2009 ዓም ስልጣኑን ከተረከቡ በኋላ በመካከለኛው ምስራቅ ባደረጉት የመጀመሪያው ጉዞዋቸው በሳውዲ ዐረቢያ ሪያድ ከተማ ጎራ ባሉበት ጊዜ ንጉሳዊውን ቤተሰብ ባጣም ነበር ያሞገሱት።

default

ፕሬዚደንት ኦባማ ሳውዲ ዐረቢያን በጎበኙበት ጊዜ

ዩኤስ አሜሪካ እና ሳውዲ ዐረቢያ በኤኮኖሚያው ብቻ ሳይሆን በስልታዊ ጉዳዮችም ላይ የቅርብ አጋሮች መሆናቸውን ነበር ኦባማ ያኔ ያመለከቱት። ዊኪሊክስ ያወጣው ዘገባ የሚታመን ከሆነ፡ የኦባማ መስተዳድር ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሂለሪ ክሊንተን በዚያው ዓመት ነበር የሳውዲ ባለስልጣናት ለሽብርተኝነት ተግባር ማስፋፊያ ከሳውዲ ዐረቢያ የሚደረገውን ርዳታ የማስቆሙን ተግባር ቀዳሚውና ዋነኛ ስልታዊ ተግባራቸው እንዲያደርጉ ለማግባባት ሁሌ የሚደረገው ጥረት በጣም ፈታኝ መሆኑን በመንግስታቸው ማስታወሻቸው ላይ በይፋ መጻፋቸው ተገልጾዋል። የክሊንተን ማስታወሻ እንዳስታወቀው፡ ከሳውዲ ዐረቢያ የሚደረገው የገንዘብ ርዳታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚንቀሳቀሰው የሱኒ ሽብርተኞች ቡድን ዋነኛ የገቢ ምንጩ ነው።

ባለሁለት መልኳ አጋር ሳውዲ ዐረቢያ


እነዚህ ሁለት ተጻራሪ የኦባማ እና የክሊንተን አስተያየቶች በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለው ግንኙነት ምን ያህል የተወሳሰበ መሆኑን ያሳያል። ሳውዲ ዐረቢያ በመካከለኛው ምስራቅ ያለችው ዋነኛዋ የዩኤስ አሜሪካ የነዳጅ ዘይት አቅራቢ ብቻ ሳትሆን እያደገ በመጣው የኢራን ተጽዕኖ አንጻርም ስልታዊ ተጓዳኝ ከመሆንዋም ሌላ፡ ባካባቢ ለሚነሱ ውዝግቦችም በዲፕሎማቲካዊ ዘዴ መፍትሄ በማፈላለጉ ጥረትም ላይ ተሳታፊ ናት። በሌላ በኩል ግን ዩኤስ አሜሪካ ሌሎች ሀገሮችን የምትወቅስባቸው የሰብዓዊ መብት ረገጣ፡ የሀይማኖት እና የፕሬስ ነጻነት፡ እንዲሁም፡ የፆታ እኩልነት መጓደልን የመሳሰሉ መሰረታዊ መብቶች ጥሰቶች በሳውዲ ዐረቢያም የሚታዩ ናቸው። እነዚህ መሰረታዊ መብቶቸ በሳውዲ ለተጓደሉበት ድርጊት የሳውዲ መንግስት የሚከተለው አክራሪው የእስልምና መስመር፡ ማለትም፡ የዋሃቢዝም ርዕዮት ተጠያቂ ነው። በዚህም የተነሳ የመስከረም አንዱን ጥቃት ከጣሉት መካከል ብዙዎቹ የሳውዲ ተወላጆች መሆቸው ብዙዎቹን ጠበብት ያን ያህል አላስገረመም።

የሳውዲ ዐረቢያ ንጉስ አብዱላ በሀገራቸው በጥንቃቄ የተሀድሶ ለውጥ ለማነቃቃት መሞከራቸው አልቀረም። ይሁንና፡ በዋሃቢዝም እና በአል ቓይዳ ርዕዮት መካከል ብዙ ተመሳሳይ አሰራር መኖሩ፡ እንዲሁም፡ ወጣት የሳውዲ ዜጎች በትምህርት ቤት እና በዩኒቨርሲቲዎች የሚቀስሙት ትምህርት አዘውትሮ ወደ ጽንፈኝነት እንደሚያመራቸው በበርሊን የሚገኘው የፖለቲካ ተቋም የሽብርተኝነት እና የእስልምና ጠቢብ ጊዶ ሽታይበርግ አስረድተዋል። ይሁን እንጂ፡ የሳውዲ አመራር የመንግስቱ ርዕዮት እና የአል ቓይዳ ርዕዮት ተቀራራቢ መሆኑን ለማመን አይፈልግም።

የፊናንሱ ርዳታ

ሳውዲ ዐረቢያ ሽብርተኝነትን በገንዘብ ትረዳለች በሚል ትልቅ ወቀሳ ይሰነዘርባታል። በርግጥ ሳውዲ ዐረቢያ ወይም ሌሎቹ የባህረ ሰላጤ መንግስታት አል ቓይዳን በገንዘብ መርዳታቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ የለም። ያሲን ሙሻርባሽን የመሳሰሉ በሀምቡርግ የሚታተመው ሳምንታዊ መጽሄት ዴር ሽፒግል ጋዜጠኞች እንደሚገምቱት፡ በየጊዜው መልዕክተኞ በብዙ ሺህ የሚገመት ገንዘብ ከሳውዲ ዐረቢያ ወደ አፍጋኒስታን ወይም ፓኪስታን ያጓጉዛሉ፤ ይኸው ገንዘብም በዚያ ወደሚገኙ የአሸባሪዎች ጣቢያዎች ወይም ማሰልጠኛ ማዕከላት ይደርሳል። ይሁን እንጂ፡ ገንዘቡ ከሳውዲ መንግስት የተገኘ አይደለም። ለዚሁ የገንዘብ አቅርቦት ኃላፊነቱ ያለው፡ በከፊል ሳያውቁት የአሸባሪዎች ሰለባ በሆኑ የተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እጅ መሆኑን ሙሻርባሽ ገልጾዋል። ግን በመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ እያዩ እንዳላዩ የሚያልፉ ሰራተኞች መኖራቸው መታወቅ እንዳለበት ስለ አል ቓይዳ የሚከታተለው ጋዜጠኛ ሙሻርባሽ ይናገራል። በሳውዲ እና በፓኪስታን መካከል ስራ ፍለጋ እያለ የሚንቀሳቀሰው ሰው ቁጥር እጅግ ከፍተኛ የሆነበት ድርጊት ራሱ የዚህኑ ገንዘብ ፍሰትን መከታተሉን እና ፍሰቱን ማድረቁን እጅግ አዳጋች እንደሚያደርገው ጊዶ ሽታይንበርግ አስረድተዋል።

ለታጋይ ቡድኖች መዋጮ የመስጠቱ ልማድ ባለጸጋ ዐረባውያን በአፍጋኒስታን በቀድሞ ሶቭየት ህብረት አንጻር ይዋጉ የነበሩ ሙዤሀዲኖችን መርዳት ከጀመሩበት ከ 1980 ኛዎቹ ዓመታት ጊዜ አንስቶ የተስፋፋ ነው። በዚሁ የመዋጮ አሰጣጥ ድርጊት ላይ ኦሳማ ቢን ላደን በ1990 ዓም ከሳውዲ ንጉሳዊ ቤተሰብ እስከተጣላበት ጊዜ ድረስ ትልቅ ሚና ተጫውቶዋል። በነዚያ ዓመታት፡ እንደ ሽታይንበርግ ገለጻ፡ የአፍጋኒስታን ሙዤሀዲኖች ከሳውዲ መንግስት በይፋ የገንዘብ ርዳታ ሳያገኙ አልቀረም። ከመስከረም አንዱ 2001 ዓም ጥቃት በኋላ ግን ብዙ የአል ሀራማይን ተቋምን የመሳሰሉ ከፊል መንግስታዊ ድርጅቶች፡ ለአሸባሪ ወይም ለታጋይ ድርጅቶች ቢያንስ በተዘዋዋሪ መንገድ ገንዘብ ሰጥተዋል በሚል ምክንያት ተዘግተዋል። አሜሪካውያኑ ግፊት ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱ ራስዋ በ 2003ዓም የጥቃት ሰለባ መሆንዋ ሳውዲዎች አስተሳሰባቸውን እንዲቀይሩ ያደረገው። እና በወቅቱ ሆን ተብሎ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚደረግ ርዳታ ለመኖሩ ማስረጃ የለም ይላሉ ሽታይንበርግ። የሳውዲ ዎች ይፋ ፖለቲካ ባጠቃላይ ሲታይ ይበልጥ ግልጽ ሆኖዋል። ይሁንና፡ የሚሰራበት የመቆጣጠሪያ ዘዴ በቂ መሆኑ አጠያያቂ እንደሆን ይገኛል።

ከሳውዲ ዐረቢያ እና ከባህረ ሰላጤ ሀገሮች ብቻ አይደለም የገንዘብ መዋጮ የሚያገኘው። ዕድሜ ለኢንተርኔት እና ለግል መረቦች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚገኙት ደጋፊዎቹም ገንዘብ ይሰበስባል ይላል ያሲን ሙሻርባሽ። በአውሮጳም። በማግሬብ ሀገሮችን ሌላ የገንዘብ ምንጭ አግኝቶዋል። በዚያ ያካባቢ ታጋዮች የውጭ ዜጎችን እያገቱ ቤዛ ለማግኘት እያሉ።

ኻሊድ ኤል ካውቲት

አርያም ተክሌ