የሳካሮቭ ሽልማት ለባዳዊ ተሰጠ | ዓለም | DW | 16.12.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የሳካሮቭ ሽልማት ለባዳዊ ተሰጠ

ስዑድ አረቢያዊዉ የድረገጽ ጸሐፊ ራይፍ ባዳዊ ባለቤት ዛሬ በስሙ ከአዉሮጳ ኅብረት ምክር ቤት የሳካሮቭን የሰብዓዊ መብት ሽልማት ተቀበለች። የባዳዊ ባለቤት ኢንሳፍ ሐይደር ሽልማቱን ስትቀበልም የአረብ ሃገራት በሃይማኖት ስም የሚካሄዱ ጭቆናዎችን በመቃወም የተለያዩ አስተያየቶችን የመታገስ ባህል እንዲያዳብሩ ጥሪ አቅርባለች።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:30
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:30 ደቂቃ

የሳካሮቭ ሽልማት

የሳዉዲዉ የድረገጽ ፀሐፊ ባለቤት ዛሬ ሽትራስቡርግ ፈረንሳይ በሚገኘዉ የአዉሮጳ ኅብረት ፓርላማ ተገኝታ ለባለቤቷ የተዘጋጀዉን ሽልማት ብትቀበልም፤ ከእሷ ይልቅ በዚህ ስፍራ ባለቤቷ በአካል ቢገኝ ኖሮ ትልቅ ትርጉም እንደሚሰጥ ሳትናገር አላለፈችም። የ31 ዓመቱ ራይፍ ባዳዊ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2012ዓ,ም ነዉ በድረገጽ የጻፈዉ እስልምናን ይሰድባል ተብሎ በሳዉዲ መንግሥት የታሠረዉ። 1000 ግርፋት የተፈረደበት የድረገጽ ጸሐፊ በአደባባይ የመጀመሪያዉን 50 ጅራፍ ሲገረፍ የሚያሳየዉ ቪዲዮ ከመላዉ ዓለም ከፍተኛ ተቃዉሞን አስከትሎ የሳዉዲን የሰብዓዊ መብት አያያዝ አስተችቷል። ባዳዊ የሳዉዲ ለነፃ የግንኙነት መረብ በሚል የኢንተርኔት የመወያያ ቡድን ተባባሪ መሥራች ነዉ። ቡድኑ ሃሳብን በነፃ መግለፅን በማበረታታት በሃይማኖት ስም ጫና የሚያደርጉ የሃይማኖት መሪዎች ሚና እንዲያበቃ በአደባባይ ይወያያል። ከመታሠሩ በፊት ስለሁኔታዉ እንዲህ ነበር ያለዉ፤

EP verleiht den Sacharow-Pres an Raif Badawi Ensaf Haidar

ኢንሳፍ ሐይዳር

«የአረቡን ኅብረተሰብ ለተመለከተ በአስገራሚ ሁኔታ ሰምቻለሁ እታዘዛለሁ ከሚለዉ በቀር መስማት በማይፈልጉት የሃይማኖት ምሁራን ሥር ምን ያህል እንደተጨቆነ እና እንደሚሰቃይ ይመለከታል። ትልቁ ስጋቴ አንድ ቀን የአረቡ ዓለም ምሁራን ከሃይማኖት ፈላጭ ቆራጮች ሰይፍ ለማምለጥ እና ነፃ አየር ለመተንፈስ ወደሌላ ይሰደዱ ይሆናል ብዬ ነዉ።»

ባለቤቱ ኢንሳፍ ሐይዳር እንደምትለዉ የአረብ ሃገራት ምሁራን ባዳዊ እና መሰሎቹ የሚያነሱትን እንዲህ ያለዉን ርዕስ፤ ዙሪያ ዙሪያዉን ይሽከረከሩበት ካልሆነ በቀር ደፍረዉ በአደባባይ አይናገሩትም። የሚያደርጉ ካሉ በእምነት እንደመሳለቅ ይቆጠራል። ይህም ነዉ ወጣቱን የድረገጽ ጸሐፊ ለአስር ዓመት እስራት ዳርጎ የጅራፍ ግርፋት ያስፈረደበት። ባለቤቱ እንደምትለዉ ግን ይህ አስመልክቶ እሱ በጽሑፍ ያሰፈራቸዉን ለተመለከተ ከእዉነታዉ የራቀ ነገር የለበትም።

«ጽሁፉን በጽሞና አንብቦ ለተረዳ ራልፍ እንዳለዉ በዉስጡ ምንም ሃሰት አያገኝም። የእሱ ጽሑፎች አንድ የተወሰነ ነገርን የሚቃወሙ አይደሉም፤ ሃይማኖትንም ሆነ ሀገርን ወይም አንድ ሰዉን ለይተዉ የሚቃወሙ አይደሉም።»

EP verleiht den Sacharow-Pres an Raif Badawi Ensaf Haidar und Martin Schulz

ኢንሳፍ ሐይዳር ከማርቲን ሹልስ ጋር

ምንም እንኳን የተመድን የሰብዓዊ መብት መግለጫ ብትፈርምም ስዑድ አረቢያ ያላትን አስከፊ የሰብዓዊ መብት ይዞታ የተቹት የአዉሮጳ ኅብረት ፓርላማ ፕሬዝደንት ማርቲን ሹልስ፤ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2015ዓ,ም ብቻ ከ150 የሚበልጡትን በሞት እንደቀጣች ጠቁመዋል። የሳዉዲ የሞት ቅጣት በአብዛኛዉ አንገት በመቅላት የሚፈጸም እንደሆነም ተጠቅሷል። እንዲያም ሆኖ የኅብረቱ ምክር ቤት የሳካሮቭን የሰብዓዊ መብት ሽልማት የሰጠዉን የድረገጽ ጸሐፊ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ምህረት በማድረግ ባስቸኳይ ፈትታ ከቤተሰቦቹ እንዲቀላቀል እንድታደርግ ጥሪ አስተላልፈዋል። ኢንሳፍ ሐይደር እንደገለጸችዉ ባዳዊ የረሃብ አድማ ከጀመረ አንድ ሳምንት ተቆጥሯል። በዚህ ምክንያትም የጤናዉ ነገር ያሳስባታል።

«የጤናዉ ነገር ያሳስበኛል። ተገርፏል። የአካልም ሆነ የመንፈስ ጤንነት የለዉም። ተስፋ ቆርጧል።»

የሳካሮቭ የሰብዓዊ መብት ሽልማት በየዓመቱ ለሚሰጣቸዉ ወገኖች 50ሺህ ዩሮን ያካትታል። ያለፈዉ ዓመት ተሸላሚ ለሴት ልጆች የመማር መብት አርአያ የሆነችዉ ፓኪስታናዊቱ ማላላ ዩሳፍአዚ ስትሆን፤ የአፍሪቃዉ የመብት ተምሳሌት ኔልሰን ማንዴ እና የፅናት ምሳሌዋ የማይናመሯ ፖለቲከኛ አንግ ሳን ሱኪም በተለያዩ ዓመታት ይህን ሽልማት ወስደዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች