የሳን ሱ ቺ መፈታትና የበርማ ፖለቲካ | ዓለም | DW | 15.11.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የሳን ሱ ቺ መፈታትና የበርማ ፖለቲካ

ማንዴላ የፈጠሯትን ደቡብ አፍሪቃን መሰል-በርማ ወይም ምያንማርን ለመፍጠር ከማንዴላ ድንቅ ተጋድሎ-አላማ የወረሱት ትግል-ተጋድሎ ፥ከሕዝባቸዉ እና ከምዕራቦች የሚጎርፈዉ ድጋፍ ብቻዉን በቂ አይሆንም።ምያንማር ማንዴላን ብቻ ሳይሆን በወዲያኛዉ ጠርዝ-ፍሬድሪክ ዴ ክላርክንም ትሻለች።

default

ሳን ሱ ቺ

አድናቂ ደጋፊዎቻቸዉ የማይናምሯ ማንዴላ ይሏቸዋል። በእርግጥም እንደ ማንዴላ ለሕዝባቸዉ ነፃነት፣ ለፍትሕ እኩልነት ታግለዋል። ከማንዴላ እኩል ባይሆንም-ለአመታት ተሰቃይተዋል-ታስረዋልም።የደጋፊ-አድናቂ ወገናቸዉ ጭፈራ-ቡረቃ ሲደራ ቅዳሜ-የሐያላኑ ሐገራት መሪዎች ለማንዴላ ካሉት-በላይ ዉደሳ፣ ሙገሳዉን ያንቆረቆሩላቸዉ ገቡ። ኦዉንግ ሳን ሱቺ። ከማንዴላ ያመሳሰላቸዉ የእስራት-መከራ ፍፃሜ፣ የሕዝባቸዉ ድጋፍ፣ ከማንዴላ ያላቃቸዉ ዉዳሴ-ሙገሳ የማንዴላዋን ደቡብ አፍሪቃ መሠል-ማይናምርን ለመፍጠር መሠረት-ድጋፍ ምርኩዝ ይናቸዉ-ይሆን? ስብዕና፣ ትግል፣ ሐገራቸዉን እያነሳን ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

በርማ-ቢሏት ምያንማር እሷዉ ናት። ያቺ ሞቃት፣ ደናማ፣ ዉብ፣ ጥንታዊ-ሥልታዊ የሐምሳ ሚሊዮኖች ሐገር። እንደ ሐገሪቱ ሁሉ የትልቂቱ ከተማዋ ስምም ሁለት ነዉ። ራንጉን አለያም ያንጉን። እንደ በርማ-ምያንማር እንደ ራንጉን-ያንጉን ስሞች ሁለትነት ሁሉ የሐገር-ከተማይቱ የረጅም ጊዜ-ጥቅል ታሪክ ሁለት ነዉ።ግን ተቃራኒ።ያቺን-ጥንታዊ-ሐገር ያቺን ሰፊ ከተማ ካነፁት ሁለቱ ተቃራኒ ታሪኮች አንዱ-ቅዳሜ ተደገመ።
በርማ-ምያንማር፥ ራንጉን-ያንጉን-ቦረቀች።የበርማ-ምያንማሮቿ ማንዴላ ከቁም ወይም ከቤት ዉስጥ እስረኝነት ተፈቱ።ኦዉን ሳን ሱቺ።ከቦራቂ-ፌስተኞቹ ባንዷ ቋንቋ ጨረቃዋ ደማቅዋ ጨረቃ ጨለማዉን በርቃ-ደመቀች።
«እሳቸዉ በመፈታታቸዉ በጣም ተደስተናል።ጨረቃዋ ወጣች እናም በጨለማዉ መሐል ብርሐን ትሰጠናለች። የበርማ ሕዝብ እሳቸዉን ያከብራል። እሳቸዉ ሐይል እና ፅናት ይሰጡናልና።»
በቡድሐ-እምነት፥ በምስራቆች ሥልጣኔ፥ በጎሳዎች-የዘመናት ስብጥር የተቀረፀዉ ያ-ሕዝብ ከ1962 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ጀምሮ ወታደራዊ፥ አምባገነናዊ፥ አንዳዴም ሶሻሊስታዊ ገዢዎች ሲፈራረቁበት የቅፅበት ደስታ-ተስፋዉ ሲቀጭ፥ ፍላጎት ምኞቱ ሲደፈልቅ፥ ኑሩ-እንዳዴም ሕይወቱ ሲጨፈለቁበት እንጂ ሌላ ብዙም አያዉቅም።

የሩቅ ተስፋ-ምኞቱ ጭላንጭል ሲበርቅ፥ የትግል መሪ አስተባባሪዉ መፈታታቸዉን ሴትዮዋ እንዳሉት ከጨረቃ-መዉጣት፥ ተፈቺዋን የጥንካሬ ፅናቱ መሠረት ቢያደርጋቸዉ በርግጥ አይበዛበትም። በቅርቡ ለወጥ ፈላጊ ሰልፈኞች፥ የተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኛ ደጋፊዎች ሲገደሉ፥ ሲደበደቡ፥ ሲጋዙ፥ ሲታሰሩ፥ ሠላም ጠያቂ መነኮሳት ሲዋረዱ፣ ሲሳቀሉ-ሲሳቀቁ እያየ ከማዘን-መሸማቀቅ በስተቀር ሌላ የማያዉቀዉ ትዉልድ በርግጥ ተደሰተ።

የአዉሎንፋስ ሰለባዎች-አስከሬን-መከራ፥ የርዳታ አቀባዮችን ጥድፊያ ሩጫ ስታፈራርቅ የከረመችዉ ራንጉን-ያንጉን ባንድ ጀምበር፥ ባንድ ምክንያት፥ በጥልቅ ደስታ የሚፈነድቅ ያን ያሕል ሕዝብ ሲያስተናግድባም በቅርብ ዘመን ታሪኳ የቅዳሜዉ የመጀመሪያዉ ነዉ።እሱም አለዉ።

«ይሕን ያህል ሕዝብ ሲደሰት ሳይ የመጀመሪያዬ ነዉ።»

Aung San Suu Kyi Unterstützer feiern vor ihrem Haus

የሐዘን-ደስታ ቅይጥ ሁለት ታሪክ።እንደ ቅርብ ዘመኑ፥ እንደ ዘንድሮዉ ሁሉ-ድሮ-ጥንት በጣም ጥንትም ለባለ-ሁለት ስሟ ሐገር እንዲያ ነበር።በአስር-አመተ አለም ግድም የሠፈረዉ የሞን ሕዝብ ከመሐሉ ከሚወጡ ገዢዎቹ ዘመን የከዳቸዉን እያሰናበተ-ዘመን ላደረለት ገዢዉ እንደቦረቀ ዘመናት ያስቆጠረበት ይትባሕሉ ከአንደኛዉ አመተ-አለም በሕዋላ አልቀጠለም።

ለሞኖች ዉድቀት ያፈሰሰዉን እንባዉን በቲቤቶ-በርማዎች ድል-ፌስታ እንዳበሰ ፣በቲቤቶ-በርማዎች ዉድቀት የገባዉን ሐዘን-በናንዢዎች ትንሳኤ-እንደተፅናና፣ አናወራታኖች፣ በታቶኖችን እንዳለዋወጠ በሞንጎሎች፣ በላኦሶች፣ በሲያሞች፣ በአሰሞች ድል-ሽንፈት ደስታን-ከሐዝን ያፈራረቀበት ረጅም ታሪኩ በአስራ-ዘጠነኛዉ መቶ ክፍለ-ዘመን አዲስ መልክና ባህሪ ያዘ።

ፈርጣማዎቹ የበርማ ገዢዎች (ያኔ ሁለተኛዉ ስሟ ለዉጪዉ አይታወቅም ነበር) በ1824 የያኔዋን የብሪታንያ ቅኝ ተገዢ ሕንድን ለማስገበር የከፈቱት ዉጊያ የዚያችን ሐገር ታሪክ ባዲስ ጎዳና ያሾረዉ ገባ። የብሪታያ ቅኝ ገዢዎች ሕንድን ከመከላከል አልፈዉ በርማን ለመጠቅለል-ሁለቴ ያዘመቱትን ጦር አላማን የበርማ ተዋጊዎች ማክሸፋቸዉ-በወረራዉ ባለቀ ወገኑ የተሰበረዉን የዚያን ሕዝብ ልብ መጠገኑ አልቀረም። ብዙ ግን አልቆየም።

የብሪታን ቅኝ ገዢዎች ጠላቶቻቸዉን ቀስ በቀስ እያዳከሙ በ1886 የመጨረሻዎቹን የበርማ ጀግኖች ጨፍልቀዉ ሐገሪቱን ከሕንድ ጋር ጠቅልለዉ ይገዟት ገቡ። ያ ሕዝብ-ነፃነቱንም አንደ-አንድ የሚያቆሞዉን የሐገሩን የግዛት አንድነትም-አጣ።

ሁለተኛዉ የአለም ጦርነት ለበርማ-የደስታ-ሐዘን ሁለት ተቃራኒ ታሪክ የደመቀበት ነበር።የብሪታንያ ቅኝ ተገዢዋ የሕንድ-አንድ ክፍለ ግዛትነትዋ አብቅቶ የብሪታያ ቅኝ ተገዢ ግን አንድ ሐገርነቷ በ1937 ተመለሰላት።ያኔ-ወጣቱ በርማዊ ነፃነት-ነፃነት ይሸተዉ የነፃነት ትግል-ወኔዉ ይሞግተዉ ያዘ። ከግንባር ቀደሞቹ ወጣቶች አንዱ ያሁኒቱ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ተሟጋች አባት ነበር።አዉንግ ሳን።

አዉግ ሳንና ብጤዎቹ የዩኒቨርስቲ ትምሕርታቸዉን አቋርጠዉ የብሪታንያን ቅኝ ገዢዎች ለመዋጋት ላደራጁት ሐይል ድጋፍ የሚሰጣቸዉ ፍላጋ ከቤጂግ፥ደልሒ ቢንከራተቱም የደረሱላቸዉ የጃፓን ወታደራዊ ገዢዎች ነበሩ።በጦርነቱ መሐል ጃፓኖች ብሪታንያን ድል ሲደርጉ በአዉሮጳ ቅኝ ገዢዎች ሲማቅቅ የነበረዉ ሕዝብ ላፍታም ቢሆን ቦረቀ። ከባሱ ገዢዎች እጅ መዉደቁን ለማወቅ ግን ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም። ከድጡ ወደ ማጡ መግባቱን እንዳወቀ ወዲያዉ በጃፓኖች አገዛዝ ላይ አመፀ።

መጀመሪያ በብሪያታንዎች፥ ቀጥሎ በጃፓኖች፥ አሰልሶ ጃፓኖችን ድል ባደረጉት እንግሊዞች ላይ ያመፀዉን ሕዝብ እንደ ፖለቲከኛ ያደራጁት፥ እንደ ወታደር ያዋጉት፥ እንደ ዲፕሎማት ያደራደሩት በትግሉ መሐል የመጀመሪያ-ሴት፥ ሰወስተኛ እና የመጨረሻ ልጃቸዉ ተወለደችላቸዉ።ራንጉን-1945።
የትዉልድ ከተማ የድፍን ሐገሯ ስምም እንደ ሕዝብ ሐገሯ ታሪክ ሁሉ የቅኝ ገዚዎችን አጠራር-ከሐገሬዉ ስያሜ ጋር የቀየጠ ሁለት ተቃራኒ ነዉ።በ1945 ይሕን ዓለም የተቀየጠችዉን ሕፃን ግን ወላጆችዋ፣ አዉንግ ሳንን--- ካባቷ፥ ሱን ከሴት አያቷ፥ ቺን ከእናቷ ቀይጠዉ በሰወስት ቅይጥ ስም ሰየሟት።

በሕዝባቸዉ ብዙ የተወደዱ፥ የተመሰገኑት፥ በትግላቸዉ የተከበሩት አዉንግ ሳን የፖለቲካ ፓርቲ መሪነትን ከጄኔራል ማዕረግነት ጋር ደርበዉ የሐገራቸዉን የነፃነት ዕለት እንዳሰሉ፥ ነፃነቱን ለማየት ወራት ሲቀራቸዉ በሰዉ እጅ ተገደሉ።እሷ ያኔ ገና የሁለት አመት ጨቅላ ነበረች።እና ወላጅ አባቷን የሁለት አመት ሕፃን አዕምሮዋ ቀርፆ ካስቀረላት ጭላንጭል ትዉስታ ባለፍ የምታዉቀዉ ከናት ወንድሞቿ በሰማችዉ አለያም እንደ ብዙዉ በርማዊ ሁሉ ከታሪክ ነዉ።

የማሕተመ ጋንዲን የሰላማዊ ትግል ፍልስፍናን ከጋንዲም በላይ የቡደሐ እምነት ተፅኖ-ከምዕራቡ ዘመናይ ትምሕርት ጋር እንደቀየጠች-አደገች።ከእንግዲሕ አንቱ ናቸዉ።ዛሬ ደግሞ የስልሳ-አምስት አመት ባልቴት፥ እዉቅ ፖለቲከኛ፥ ከአለም ኖቤል ኮሚቴ፥ የሰላም ኖቤል፥ ከሕንድ መንግሥት፥ የጀዋሕራል ኔሕሩ መታሰቢያ፥ ከአዉሮጳ ሕብረት የሳኻሮቭ-የነፃ አስተሳሰብ፥ ከቬኑዝዌላ መንግሥት የሲሞን ቮልቨር መታሰቢያ፥ ሽልማት የጎረፈላቸዉ፥ ከሁሉም በላይ በሕዝብ-ወገናቸዉ የተከበሩ ናቸዉ።ከአንቱም በላይ አንቱ።

ጋንዲን ያደንቁ፥ የቡድሐ እምነትን ያከብሩ፥ ደጋፊዎቻቸዉ እንደሚሉት እንደ ማንዴላ ብልሕ ጠንካራ-ታጋሽም ይሆኑ-ይሆናል።በ1988 ፖለቲካዉን ተቀይጠዉ ብሔራዊ ሊግ ለዲሞክራሲ የተሰኘዉን ፓርቲ ሲመሰርቱ ግን ከማንም በላይ የስም-አካላቸዉ መሠረተ-ዉልድ የሆኑትን-አባታቸዉን ነበር-የሆኑት።ትናንትም ያሉት አባታቸዉ ከስልሳ አምስት አመታት በፊት ካሉት ብዙም የራቀ አልነበረም።

«እናንተን እዚሕ በማየቴ በጣም ደስተኛ ነኝ።እበረታታለሁም።ሕዝቡ ምን እንደሚፈልግ እዚሕ የተሰበሰባችሁት ሁላችሁም ምን እንደምትሹም አዉቃለሁ።አንዳዴ አሰልቺ ቢሆንም በየዕለቱ ከአምስት-እስከ ስድስት ሰአት ራዲዮ ሳዳምጥ ነበር።»

Flash-Galerie Birma

ባለፈዉ ቅዳሜ ከቁም እስረኝነት ሲለቀቁ ቀድመዉ ካያቸዉ የዉጪ ዲፕሎማቶች አንዱ የብሪታንያዉ አምባሳደር አንድሪዉ ሔይን እንዳሉት ደግሞ መከራን የተቋቋሙ ጠንካራም ወይዘሮ ናቸዉ።
«በጣም ጥሩ መንፈስና ቅርፅ ነዉ ያላቸዉ።ደስተኛ፥ ዘና ያሉና በጣም ተፈጥሯዊ ይመስላሉ።በሰልፈኞቹ እና በሳቸዉ መሐል ማስመሰል የሌለበት ደስታና ፈገግታ መኖሩን ትገነዘባለሕ።ከሰልፈኞቹ ጋር ሲቀልዱም።እዉነቱን ለመናገር ይሕን ማየት በጣም ያስደስታል።እርግጥ ፈተናዉ ከባድ ነዉ።አሁን ገና መጀመሩ ነዉ።ይሕንን እሳቸዉም አያጡትም።ሕዝቡ እዚሕ ለሳቸዉ ያለዉ ስሜት ግን እነዚያን ፈተናዎች ለመወጣት ለሚያደርጉት ጥረት ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ እንዳላቸዉ መስካሪ ነዉ።»

ከማንዴላ ያስቆጣራቸዉ ይሕ የሕዝብ ድጋፍ መከራን የመቋቋም ችሎታዉ ነዉ።ከፊታቸዉ የተጋረጡባቸዉን ፈተናዎችን ለመወጣት የማንዴላን ብልሐት፥ ትዕግስት፥ይቅር ባይነት መሳሪያቸዉ ያደርጉት ይሆናል። ከዉጪ በተለይ ከምዕራቡ አለም የጎረፈላቸዉ አድናቆትና ድጋፍም ቀላል የሚባል አይደለም።

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ «ለኔ ጀግናዬ ለበርማ ሕዝብ ደግሞ የመብት ነፃነት አብነት» ብለዋቸዋል።ለጀርመንዋ መራሒተ መንግሥት ለአንጌላ ሜርክል ደግሞ የሰብአዊ መብት ታጋይ አብነት።ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን ሌሎችም የብዙ ሐገር መሪ-ዎች አድንቀዉ ድጋፋቸዉን ሰጥተዋል።የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጊዶ ቬስተር ቬለ እንደገለፁት አብዛቸዉ የምዕራቡ ፖለቲከኛ የኦንግ ሳን ሱቺ መፈታት የመጀመሪያዉ እንጂ የመጨረሻዉ እርምጃ ሊሆን አይገባም ባይ ነዉ

«ይሕ ከቁም እስረኝነት የመፍታቱ ዉሳኔ የመጀሪያዉ እርምጃ እንደሚሆንና እርምጃዉ ይቀጥላል ብለን እናስባለን።እንጠብቃለንም።አሁንም በርካታ የፖለቲከኞች እንደታሰሩ ነዉ።እነሱም ያለ ቅድመ ሁኔታ መለቀቅ አለባቸዉ።»
ይሕን መሰሉን ድጋፍ ደጋፍ ደግሞ የብሪታንያዉ አምባሳደር ፈተና ያሉትን ትግል ከግብ ለማድረስ ጠንካራ ምርኩዝ ያደርጉት ይሆናል።የማንዴላን ድል ለመጎናፀፍ፥ ማንዴላ የፈጠሯትን ደቡብ አፍሪቃን መሰል-በርማ ወይም ምያንማርን ለመፍጠር ከማንዴላ ድንቅ ተጋድሎ-አለማ የወረሱት ትግል-ተጋድሎ ፥ከሕዝባቸዉ እና ከምዕራቦች የሚጎርፈዉ ድጋፍ ብቻዉን በቂ አይሆንም።ምያንማር ማንዴላን ብቻ ሳይሆን በወዲያኛዉ ጠርዝ-ፍሬድሪክ ዴ ክላርክንም ትሻለች።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ


Audios and videos on the topic