የሳሕል ምስቅልቅል | ዓለም | DW | 07.06.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የሳሕል ምስቅልቅል

ሳርኮዚ ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን ከነዘር-ማንዛራቸዉ፣ ለማጥፋት ሌት-ከቀን የባተሉ፣የጣሩ፣የለፉበት ምክንያት አንዳዶች እንደሚሉት አሁን ፍርድ ቤት የሚያመላልሳቸዉን በሊቢያ ገንዘብ  የቆሸሸ እጃቸዉን ለማፅዳት ወይም ለመሰወር ሊሆን-ላይሆንምም ይችላል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:02

በግጭት፣ ጦርነት የሚተራመሱት አብዛኞቹ የፈረንሳይ ቅኝ ተገዢዎች ናቸዉ

በአዉሮጳዉያን ምርጥ ወታደሮች የሚሠለጥን፣ የሚታገዘዉ የማሊ መንግስት ጦር-ከአማፂያን ጋር በሚያደርገዉ ዉጊያ ሽንፈት ሲጫጫነዉ ወደ ቤተ-መንግስት ዞሮ በመፈንቅለ መንግስት ማግስት-መፈንቅለ መንግስት እያሴረ የቁርዓን-ሐዲስ፣ የመንዙማ-ሙዚቃዊቱን ምድር ቁል ቁል እየነዳት ነዉ።ቻድ ለመንግሥት-አማፂያን ዉጊያ የረጅም ጊዜ መሪዋን መስዋዕት ካደረገች ሁለት ወር ልትደፍን ሁለት ሳምንት ቀራት።ማሊን ከምዕራብ ተንተርሳ ከምሥራቅና ደቡብ ምዕራብ ቻድን የረገጠች የምትመስለዉ ኒዠር ሽብር-ግድያዋን ላፍታ ዉጣ ተረኛ ጎረቤቶቿን ትታዘባለች።ከሰሜን ከማሊ፣ ከምስራቅ ከኒዠር ጋር ድንበር የምትጋራዉ ቡርኪና ፋሶ ለመንሥት አማፂያን ዉጊያ የ160 ሠላማዊ ዜጎችዋን ሕይወት ገበረች።ቅዳሜ።የቡርኪናፋሶዉ ጨፍጨፋ መነሻ፣ የሳሕል ምስቅልቅል ማጣቀሻ፣ ምክንያቱ መድረሻን ነዉ። ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።
                                         
ከምሥራቅ ከኤርትራ እስከ ምዕራብ ሞሪታንያ አግድም የተነጠፈዉ ረጅም፣ቀጭን በረሐማ ምድር  እንደ አሸዋ፣ ነዳጅ-ወርቅ፣ ብረት ማዕድኑ ሁሉ የሐብት ፈላጊዎች ዉጊያ፣ የቅኝ ገዢዎች ሴራ፣ የጎሳ-ኃይማኖት ግጭት፣ መፈንቅለ መንግስት ተለይቶት አያዉቅም።ሳሕል።በዚያ ምድር የቅርብ ዘመን ታሪክ በነበረና ባለዉ ግጭት፣ጦርነት፣ መፈንቅለ መንግስት ሁሉ እንደ ሐገር የቆሞቱን ግዛቶች ለረጅም ጊዜ ቅኝ የገዛችዉ ፈረንሳይ፣ የምዕራብ አጋሮችዋ፣ የምሥራቅ ባላንጦችዋ፣ የአረብ አፍሪቃዉያን ደጋፊ ተቀናቃኞችዋ እጅ ተለይቶት አያዉቅም።
ባለፈዉ አርብ ለቅዳሜ አጥቢያ ሶልሐን የተባለዉን የቡርኪና ፋሶን መንደር ወርረዉ 160 ሠላማዊ ሰዎችን የፈጁት ታጣቂዎች ግን የቡርኪና ፋሶ ባለስልጣናት እንዳሉት በ2012 ግድም (ዘመኑ በሙሉ እንደ

ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) መደራጀት የጀመሩት አሸባሪዎች ናቸዉ።
«ሰኔ 4 ለ5 አጥቢያ ማንነታቸዉ በዉል ያልታወቀ ታጣቂዎች ሳሕል አዉራጃ፣ ሶልሐን መንደር አጥቅተዋል።በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተፈፀመዉ ጥቃት በርካታ ሰዎች ተገድለዋል።የሴባ ወረዳ አንድ ቡድን ባደረገዉ የመጀመሪያ ደረጃ ጥናት መሠረት በአሸባሪዎቹ ጥቃት በመቶ የሚቆጠሩ ሠላማዊ ሰዎች ተገድለዋል፣ በርካታ መኖሪያ ቤቶች ጋይተዋል።የገበያዉ ማዕቀልም ነድዷል።»

ማንነታቸዉ «ያልታወቀ» ብሎ የጀመረዉ የመንግስት መግለጫ «አሸባሪ» ብሎ የማሳረጉ ተቃርኖ አጠያያቂ ነዉ።ይበልጥ የሚያጠያይቀዉ ግን እስከ 2012  የማይታወቁት አማፂ፣ ታጣቂ ወይም አሸባሪዎች ያመጣጥ-አደረጃጀታቸዉ እንዴትነት  እንቆቅልሽ መፍቻ ማጣቱ ነዉ።
በአብዛኞቹ የሳሕል አካባቢ ሐገራት የሚኖሩት የቱአሬግ  ጎሳ አባላት የአዉሮጳ በጣሙን የፈረንሳይ ቅኝ ገዢዎችን ሲዋጉ አመታት ያስቆጠሩ፣ በድሕረ ቅኝ አገዛዝ ዘመንም የራሳቸዉ አስተዳደር እንዲኖራቸዉ በተለይ ሰሜናዊ ማሊ ዉስጥ አሸምቀዉ ይዋጋሉ።ለዓመታት የጎሳ መልክና ባሕሪ  የነበረዉ የቱአሬጎች አመፅ  በ2013 የሐይማኖት ይዘት ተላብሶ ያቺን የጥንት ዩኒቨርስቲዎች መንደር፣ የእስልምና ማዕከል፣ የዜማ ሙዚቃዊቱን ሐገር ያወድም-ይንዳት ያዘ።
በቀድሞዋ የማሊ ቅኝ ገዢ በፈረንሳይ መሪና አስተባባሪነት ማሊ የሰፈረዉ የአዉሮጳና የአፍሪቃ ጦር የአማፂያኑን ግስጋሴ ገትቶታል።ይሁንና ለአፍሪቃዊቱ ደሐ ሐገር ሠላም ሲባል የአዉሮጶች ሕይወት መጥፋት ስለሌለበት የአዉሮጳ ወታደሮች ተልዕኮ ከተዋጊነት ወደ አሰልጣኝነት ሲለወጥ አማፂያኑ አንሰራርተዉ የማሊ መንግስት ጦርን እያስጨነቁ ነዉ።

ኮሎኔል አስሚ ጎይታ የባማኮ ቤተ-መንግሥትን ማማተር የጀመሩት የባልደረቦቻቸዉም ዉጊያ፣ የፈረንሳይ-አዉሮጳ-አፍሪቃዉያን ድጋፍ ዲፕሎማሲም የደኻይቱን ሐገር ሠላም ማስከበር እንዳልቻለ ሲገነዘቡ ነበር።ኮሎኔሉ ባለፈዉ ነሐሴ የኢብራሒም ቡበከር ኬይታን መንግስት አስወግደዉ እንደ ምክንትል ፕሬዝደንት የያዙት ሥልጣን አልበቃ ወይም አላረካ ቢላቸዉ ሁለተኛዉንም ፕሬዝደንት አስወግደዉ ባለፈዉ ሳምንት የመሪነቱን ሥልጣን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠሩት።
ኮሎኔል ጎይታ ከጦር ኃይሉና ከተራዉ የማሊ ዜጋ ከፍተኛ ድጋፍ ያላቸዉ ይመስላል።
                                       
«ይሕቺ ሐገር ያልተሻሻለችዉ በመሪዎችዋ ምክንያት ነዉ።ጥሩ መሪ ቢኖረን ኖሮ ሐገሪቱ ትሻሻል ነበር።ጥሩ መሪ ስለሌለን ግን ሐገሪቱ አልተለወጠችም።አሁን አስሚ ጎይታ ፕሬዝደንት ሆነዋል።በጣም ተደስቻለሁ።» ይላል የባማኮዉ ነዋሪ።ሌላዉ ደግሞ።«አስሚ ጎይታ የማሊ ፕሬዝደንት ሆነዋል።በኔ ግምት ይገባቸዋል።ሁላችንም ወደነዋል።እኔ በተለይ በጣም ተደስቻለሁ።»
ባማኮ በጊዚያዊ መሪዎችዋና ጊዚያዊ መሪዎችዋን ሾሞ-በሻረዉ ወታደራዊ ሁንታ ልዩነት ስትበጣበጥ ሰሜናዊ ማሊ ዉስጥ የሸመቁ አማፂያን በመቶ የሚቆጠሩ ሠላማዊ ሰዎች ገድለዋል።የምዕራብ አፍሪቃ የምጣኔ ሐብት ማሕበረሰብ ECOWAS ማሊ ዉስጥ ሠላም ለማስፈን የተከረዉ የለም።የሠላም እጦት በወለደዉ መፈንቅለ መንግስት ሥልጣን የያዘዉን ወታደራዊ ሁንታ ከአባልነት ለማገድ ግን አልሰነፈም።
ማሊ ዉስጥ የ

ሠፈረዉ ከ5ሺሕ በላይ የፈረንሳይ ጦር ሠላማዊ ሰዎች ሲገደሉ በቅርብ ርቀት ይከታተል ነበር።ጦሯ ለማሊ ሠላም የፈየደዉ እንደሌለ የምታዉቀዉ የቀድሞዋ  ቅኝ ገዢ ፈረንሳይ፣ ከአሜሪካ  ጋር ሆና በማሊ የጦር መኮንኖችት ላይ ማዕቀብ ለመጣል እየተጋበዘች ነዉ።
ማሊን ቡርኪና ፋሶና ቻድን የምትዋሰነዉ ሌለኛዋ የቀድሞ የፈረንሳይ ቅኝ ተገዢ ኒዠር ሰሞኑን ሠላም መስላ ጎረቤቶችዋን ትታዘባለች።ባለፈዉ ሚዚያ መጀመሪያ ግን አማፂያን ደቡባዊ-ምዕራብ ግዛትዋ በሚገኙ መንደሮች ዉስጥ በከፈቱት ጥቃት 137 ሠላማዊ ሰዉ ፈጅተዋል።የኢጣሊያዉ መከላከያ ሚንስትር ሎሬንሶ ጉሪኒ ግን በቀደም ኒያሚን ሲጎበኙ የኒዠርን ሠላም እናስከብራለን አሉ። 
                                    
«ድንበራችን የሚያልፈዉ በዚሕ በኩል ነዉ።ስለዚሕ ከመላዉ አዉሮጳ ጋር እዚሕ መገኘት አለብን።የዚቺን ሐገርና የዚሕን አካባቢ ሠላም የሚያሰጉ ኃይላትን መዋጋት አለብን።ሥጋቱ በኛም ላይ ያነጣጠረ ነዉ።»
እንደ ሁሉም የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት ጦር ሁሉ የኢጣሊያ ጦር የሳሕልን ሠላም ለማስከበር ከዘመተ ዓመታት ተቆጠሩ።ጦራቸዉ፣ ከወር በፊት የደረሰዉን ጥቃት አለመከላከሉን ሚንስትሩ አልሰሙ ይሆን? 

በ1980ዎቹ በርበርስ ጦርነት፣ በምዕራብ-ምስራቆች ሽኩቻ፣ በሊቢያ አሜሪካኖች የእጅ አዙር ዉጊያ ስትተራመስ የነበረችዉ ቻድ የቀድሞዉ አማፂ ቡድን መሪ ኢዲሪስ ዴቢን በፈረንሳዮች ፈቃድና ድጋፍ ካናቷ ከሰቀለች ከ1990 ወዲሕ አንፃራዊ ሠላም ሰፍኖባት ነበር።እንዲያዉም ዴቢ ከፓሪስና በፓሪስ በኩል ከምዕራባዉያን በሚሰጣቸዉ ያላሰለሰ ድጋፍ የሳሕል አካባቢን «አሸባሪ» ከሚባሉት ኃይላት ጥቃት የሚከላከል ጦር አዝማች፣ የሠላም ጠንካራ ዘብ ተደርገዉ ይወደሱ-ይሞገሱም ነበር።
ዋና ምሽጉን ናጄሪያ ያደረገዉን ቦኮ ሐራምን የሚወጋ ጦር ካሜሩን ድረስ ያዘመቱት ዴቢ ጥንት እንደለመዱት ሰሜናዉ ቻድ ዉስጥ ጦር ግንባር ሲያዋጉ ባለፈዉ ሚያዚያ አጋማሽ በጠላቶቻቸዉ ተገደሉ።የአማፂ-መንግስት ጦር ዉጊያ እንደቀጠለ ነዉ።
ከ2012 ጀምሮ የሳሕል አካባቢ ሐገራትን የሚያተራምሰዉ ሁከት፣ ግጭት፣ጦርነት፣ሽብር ምክንያት ብዙዎችን የሚነካ እብዙ የሚከፈል ሊሆን ይችላል።የጎላዉ ግን የሊቢያ መፍረስ ነዉ።ስልታዊቱ፣ ሐብታሚቱ፣ ሰፊይቱ ሐገር ስትፈርስ ለረጅም አመታት ያከማቸችዉ ጦር መሳሪያ ተበተነ።

አፍሪቃን እርስበርስና ከመላዉ ዓለም የሚያገናኙ ወደብ፣መንገድ፣ በረሐዎችዋ ለጦር መሳሪያ ሺያጮች፣ ለሸማቂዎች፣ ለስደተኛ አሸጋጋሪዎች፣ ለወሮቦሎች  በሰፊዉ ተበርግዷል።

ከ2013 ጀምሮ የምዕራባዉያን መንግስታትና መገናኛ ዘዴዎች ጂሐዲስት፣ አሸባሪዎች፣ አማፂ፣ ታጣቂ እያሉ የሚጠሩ የሚያወግዟቸዉ ኃይላት እንደ አሸን የፈሉት፣ ቀድሞ በቀጥታ፣ አሁን በተዘዋዋሪ የፈረንሳይ ቅኝ ተገዢ በሆኑ ሐገራት ዉስጥ ነዉ።ሊቢያን ያፈረሰዉን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት (ጦር)ንና የአረብ ሐገራትን ወረራ በግንባር ቀደምትነት የመሩና ያስተባበሩት  የያኔዉ የፈረንሳይ መሪ ኒላይ ሳርኮዚ መሆናቸዉ ነዉ ዚቁ።
ሳርኮዚ ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን ከነዘር-ማንዛራቸዉ፣ ለማጥፋት ሌት-ከቀን የባተሉ፣የጣሩ፣የለፉበት ምክንያት አንዳዶች እንደሚሉት አሁን ፍርድ ቤት የሚያመላልሳቸዉን በሊቢያ ገንዘብ  የቆሸሸ እጃቸዉን ለማፅዳት ወይም ለመሰወር ሊሆን-ላይሆንምም ይችላል።

ሳርኮዚ ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወዲሕ ምዕራቡን ዓለም ከምትመራዉ ከአሜሪካ መሪዎች ቀድሞዉ ሊቢያን ማስወረራቸዉ ግን ሐቅ ነዉ።«ዓየር ኃይላችን፣ የኮሎኔል ጋዳፊ አዉሮፕላኖች በቤንጋዚ ሕዝብ ላይ የሚያደርሰዉን ጥቃት ያከሽፋሉ።ተዋጊ አዉሮፕላኖቻችን በከተማይቱ ላይ የሚደርስ ጥቃትን እየተከላከሉ ነዉ።ሰላማዊ ሰዎችን የሚያሰጉ መድፎችንም ያጠቃሉ።»

ዓለም የሳርኮዚን መቅለብለብ፣ የሊቢያን ዉድመትና መዘዙን ዘንግቶታል።ካለፈዉ ቅዳሜ ወዲሕ ደግሞ ስለአፍሪቃ ካነሳ የቻድን የርስ በርስ ጦርነት፣ የኒዠርን ግድያ፣ የማሊን መፈንቅለ

መንግስት አይደለም።የቡሪኪና ፋሶዉን ጭፍጨፋ እንጂ።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ የአንቶኒዮ ጉተሬሽ ዉግዘት፣ የሮማ ካቶሊካዊት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የፍራንሲስ ፀሎትም የተንዠቀዠቀዉ ለቡርኪና ፋሶዉ ጭፍጨፋ ሰለቦች ነዉ።
«በአርብና በቅዳሜ መሐል በነበረዉ ሌሊት ቡርኪና ፋሶ ትንሽ ከተማ ዉስጥ ለተጨፈጨፉት ሰዎች መፀለይ እፈልጋለሁ።ከሟች ቤተሰቦችና በተደጋጋሚዉ ጥቃት ከተሰቃየዉ ከመላዉ የቡርኪና ፋሶ ሕዝብ ጎን ነኝ።አፍሪቃ የሚያስፈልጋት ሰላም እንጂ ሁከት አይደለ።»
አዎ አፍሪቃ፣ ከኢትዮጵያ እስከ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ከሶማሊያ እስከ ካሜሩን ሠላም ትሻለች።የእስካሁኑ ዱዓ-ፆም-ፀሎት ግን በርግጥ አልያዘም።ለነገሩ አፍሪቃ ሠላም እንድትሆን አፍሪቃዉያን ራሳቸዉ ይፈልጉ ይሆን? ኃያሉ ዓለምስ? ቸር ያሰማን

ነጋሽ መሐመድ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ
 

Audios and videos on the topic