የሳህል አካባቢ ጦር ያጋጠመው እክል | አፍሪቃ | DW | 26.05.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የሳህል አካባቢ ጦር ያጋጠመው እክል

በይበልጥ ተለዋዋጭ ሁኔታ በሚታይበት የሳህል አካባቢ በሚንቀሳቀሱ ጂሀዲስቶች አንጻር ለሚታገለው የምዕራብ አፍሪቃውያን ጦር ጠንካራ የተመድ ድጋፍ እንዲኖር የቀረበውን ጥሪ ዩኤስ አሜሪካ ውድቅ አደረገች።  በፈረንሳይ የሚረዱ አምስት የምዕራብ አፍሪቃ ሀገራትጦር ለማቋቋም የተስማሙት ባለፈው ዓመት ነበር።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:34

ለቡድን አምስት ጦር የተጠየቀው ቋሚ በጀት ተቀባይነት ሳያገን ቀረ።

ቡርኪና ፋሶ፣ ቻድ፣ ማሊ፣ ሞሪታንያ እና ኒጀር ላቋቋሙት ቡድን አምስት በሚል ለሚታወቀው የጋራ ጦር  በዚያን ጊዜ የ500 ሚልዮን ዶላር ርዳታ ቃል ተገብቶላቸዋል። ጂሀዲስቶችን የመታገል ተልዕኮ የያዘው ቡድን አምስት የሳህል ጦር በአካባቢው ከሚንቀሳቀሰው የፈረንሳውያን የባርክሀኔ ግብረ ኃይል ጎን የሚሰለፉ ወደ 5,000 የሚጠጉ ወታደሮች ማሰማራት ያሰማራል ተብሎ ይጠበቃል። ይሁን እንጂ፣ የቡድን አምስት የጋራ ጦር በቂ የጦር መሳሪያ ትጥቅ የሌለው መሆኑ ይነገራል። ይህን መነሻ በማድረግም የተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶንዮ ጉተረሽ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ለቡድን አምስት ጦር ዓመታዊ መደበኛ ድጋፍ እንዲሰጥ ባቀረቡት ሀሳብ ላይ ዩኤስ አሜሪካ እንድትስማማ ቢያሳስቡም፣ ሀሳባቸው ተቀባይነት አላገኘም። በዋና ጸሀፊው ዘገባ ላይ በፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ ማብራሪያ ያቀረቡት የተመድ ሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ምክትል ዋና ጸሀፊ ቢንቱ ኬይታ ከተጓደለው ትጥቅ ጉዳይ ጎን፣ በስምሪቱ ላይ የታየው ዝግመትም ባፋጣኝ ሊስተካከል እንደሚገባው አሳስበዋል።


« የጋራው ጦር ስራውን ይጀምር ዘንድ የቡድን አምስት የሳህል አካባቢ አባል ሀገራት ቀሪዎቹን ወታደሮች ባፋጣኝ እንዲያሰማሩ ጥሪ አቀርባለሁ። »
ከጥቂት ጊዜ በፊት በወጡ ዘገባዎች መሰረት፣ በአካባቢው የተሰማሩ ሰላም አስከባሪዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል በሚል የተሰነዘረውን ወቀሳ በተመለከተ ቢንቱ ኬይታ የቡድን አምስት አባል ሀገራት በማሊ የተሰማራው የተመ ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ፣ በምህፃሩ ሚኑስማ እና የተመድ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ተመልካች መስሪያ ቤት አንድ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግ ማስከበሪያ ማዕቀፍ ለማውጣት የጀመሩት ጥረት እንዲሳካ እና ባፋጣኝ ተግባራዊ እንዲሆን አብረው እንዲሰሩ ተማፀነዋል።   
ፈረንሳይም አሁንም ስራውን ሙሉ በሙሉ በመጀመሩ ረገድ ብዙ ተግዳሮቶች ያሉበትን የጋራውን የጦር ተልዕኮ ለማጠናከር ብዙ መሰራት እንዳለበት መከራከሪያ ሀሳብ ማቅረቧ የሚታወስ ነው። በፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ የዩኤስ አሜሪካ ፖለቲካ አስተባባሪ ኤሚ ታኾ  ግን ሀገራቸው ሀሳቡ በምክር ቤቱ ለውይይት የሚቀርብበትን ሀሳብ እንደምታከላክል አስታውቀዋል።  ዩኤስ አሜሪካ ሀገራት ለሳህል የቡድን አምስት ጦር በተናጠል ርዳታ የሚሰጡበትን ተግባር ብትደግፍም፣ የተመድ ላካባቢው የጋራ ጦር ተልዕኮ አዲስ በጀት የሚመድበትን እቅድ አጥብቃ ተቃውማለች።  


እርግጥ፣ የቡድን አምስት ጦር በማሊ ከተሰማራው  ከሚኑስማ አንዳንድ ቴክኒካዊ ድጋፍ ያገኛል። ይሁንና፣ ሚኑስማ ርዳታውን መቀጠል ይችል ዘንድ፣ በተለይም፣ በማሊ የሚገኙት የቡድን አምስት የጋራ ጦር ሰፈሮችን ለማጠናከር  አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው መጠየቁን አላቋረጠም።  የተመድ ሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ምክትል ዋና ጸሀፊ ቢንቱ ኬይታ በሳህል አካባቢ ያለው የፀጥታ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ለፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ በመግለጽ፣ ርምጃ የማይወሰድበት ሁኔታ አደገና መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። እንደ ቤንቱ ኬይታ ገለጻ፣ ሽብርተኝነት እና የተደራጀው ወንጀል አካባቢውን ለሚቀጥሉት ብዙ ዓመታትም ችግር ሆኖ ይቀጥላል።  


የቡድን አምስት የጋራ ጦር ከሚጠብቀው ግዙፍ እና ቀላል ያልሆነ ተልዕኮ ጋር የሚመጣጠን ትጥቅ እንደተጓደለው የቡድኑ ቋሚ ተጠሪ ማሞ ሲዲኩ አረጋግጠዋል።
« እርግጥ፣ ምንም  እንኳን ከሰው ኃይላችን መካከል  80 ከመቶው  ማሊ በሚገኘው  የሴቫሬ ዋና ጽህፈት ቤታችን እና ጦሩ በሚንቀሳቀስባቸው በሌሎች ሶስት ዞኖች ቢሰማራም፣ ወታደሮቻችን በሚገባ ያልታጠቁ መሆናቸው የማይካድ ሀቅ ነው። በተለያዩ መንገዶች አደገኛ በሆኑት አካባቢዎች የሚገኙት የጦር ሰፈሮች እና ለነሱ አስፈላጊ የሆነው የስንቅ እና ትጥቅ አቅርቦቱ አሁንም ተጓድሎ ነው የሚገኘው። »
እንደ ማሞ ሲዲኩ አስተሳሰብ፣ ለፀጥታው አለመረጋጋት በዘላቂነት መፍትሔ ለማስገኘትም የሳህል አካባቢ ችግሮችን ባጠቃላይ መመልከት ያስፈልጋል።

« ለዘላቂ የተሳካ ውጤት ወሳኙ ርምጃ ፣ የፀጥታውን  ምላሽ ሳህልን ከሚመለከቱ የተወሳሰበቡ ጉዳዮች ለመለየት አለመሞከር ነው። እርግጥ፣ ካለ ሰላም እና ፀጥታ  ልማትም ሆነ ብልፅግና ሊኖር አይችልም። ይሁን እንጂ፣ በልማት እና በማህበራዊ ኤኮኖሚያዊ ልማት ዘርፍ በተጨባጭ የሚታይ መሻሻል የሚጓደልበት ሁኔታ  የፀጥታ አለመረጋጋትን ይበልጡን ያስፋፋል። »  
በቡርኪና ፋሶ ሽብርተኞች ሰሞኑን በመዲናይቱ ዋጋዱጉ እና ባካባቢዋ በፖሊስ ኬላ ላይ ጥቃት ጥለው የሰው ሕይወት ማጥፋታቸው የሕዝቡን ስጋት ማጠናከሩን ቡርኪናቤው ተንታኝ ሲያካ ኩሊባሊ ገልጸዋል።


«  የቡርኪና ፋሶ የፀጥታ ሁኔታ ከሳምንት ሳምንት እየተበላሸ ሄዷል። እየተፈጸመ ባለው ጥቃት የተነሳ ብቻ ሳይሆን፣ የፀጥታ ኃይላት በመዲናይቱ ሳይቀር እየተበራከቱ ለመጡት ጥቃቶች እየሰጡት ያለው ምላሽ በቂ አለመሆን ሁኔታውን አሳሳቢ አድርጎታል። እና ባጠቃላይ በሀገሪቱ ፣ በተለይ በመዲናዋ ትልቅ ስጋት ተፈጥሯል። »   
አሁን ወደ ኒጀር እና ቡርኪና ፋሶ የተስፋፋው ችግር መላውን አካባቢ ከመጠናወቱ በፊት ትኩረት እንዲያገኝ በተመድ ቋሚ የአፍሪቃ ህብረት ታዛቢ ፋጢማ ኪያራ መሀመድ ጠይቀዋል።
« ሽብርተኝነት እና ኃይል የታከለበት የፅንፈኝነት ተግባር በደቀኑት ስጋት የተነሳ  በማሊ እና በብዙው የሳህል አካባቢ የፀጥታ ሁኔታዎች እየተበላሹ የሄዱበት ድርጊት የአፍሪቃን ህብረት አሁንም እንዳሳሰቡት ይገኛሉ። » 
ህብረቱ ችግሩን ለማቃለል ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋር ባንድነት የሚያስፈልገውን ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን በተመድ ቋሚ የአፍሪቃ ህብረት ታዛቢ ፋጢማ ኪያራ መሀመድ አክለው ገልጸዋል። 

« የሳህል አካባቢ የተደቀነበት የተወሳሰበ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮት፣ ጠንካራ ግንኙነት ባላቸው ፀጥታ እና ልማት ረገድ ፣ የጋራ ምላሻችን እንደሚያስፈልጋቸው ያረጋገጠ ሁነኛ ማስረጃ ነው። በመሆኑም፣ ብሔራዊ እና አካባቢያዊ ሁኔታዎች በተሻለ መንገድ ለመመለስ እንችል ዘንድ የሚጠበቅብንን ጣልቃ የመግባት ርምጃን ማጠናከር ግድ ይላል። ይህን በምናደርግበት ጊዜ ባካባቢው ለሚታየው አለመረጋጋት መንስዔ አስፈላጊውን ትኩረት በመስጠት የኃይሉን ተግባር ማብቃት  እንችላለን። » 

አውሮጳ ይህን የኋላ ኋላ ከአካባቢው አልፎ ለአህጉሯ ስጋት ሊሆን ይችላል ያለችውን በሳህል አካባቢ የሚታየውን የፅንፈኖች እንቅስቃሴ በስጋት በመከታተል ላይ መሆኗን ቻተም ሀውስ የተባለው የብሪታንያውያኑ የፖለቲካ ጥናት ተቋም ተንታን ገልጸዋል።
« የፈላስያን እንቅስቃሴ ግልጽ እንዳደረገው፣ በምዕራብ አፍሪቃ የሚከሰቱ ሁኔታዎች በአውሮጳ ላይ ግዙፍ ተፅዕኖ ያሳርፋሉ፣ ጂሀዲሶትቹ  በምዕራብ አፍሪቃ፣ በተለይም፣ ሁኔታዎች አስተማማኝ ባልሆኑበት በሳህል አካባቢ በነፃ መንቀሳቀስ ከቻሉ፣ ያ ትልቅ ስጋት መደቀኑ አይቀርም፣  በአውሮጳም ፀጥታ ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል። »
አውሮጳ  ባለፉት 20 እና 30 ዓመታት፣ በተለይ ባለፉት 10 እና 15 ዓመታት ምዕራብ አፍሪቃ በልማቱ እና በፖለቲካው ዘርፍ ሀቀኛ መሻሻል እንዲያስገኝ ግዙፍ ድጋፍ አድርጋለች። እና እንደ ፖል ሜሊ አስተያየት፣ የጂሀዲስቶቹ የኃይል ተግባር ከተስፋፋ፣  በብዙዎቹ የምዕራብ አፍሪቃ ሀገራት በወቅቱ የሚታየው ስርዓተ ዴሞክራሲ ሊናጋ ይችላል። 
« እነዚህ ጂሀዲስት ቡድኖች በተጠቀሱት ያካባቢ ሀገራት ያሉትን የመንግሥታት ተቋማትን ነው የሚያጠቁት።  በፖሊስ ኬላዎች፣ በመንግሥት ባለስልጣናት እና  በድንበሩ አካባቢ ባሉ የጦር ሰፈሮች ላይ ጥቃት ይሰነዝራሉ። ለምሳሌ፣  በትምህርቱ እና በጤና ጥበቃው ዘርፎች የልማቱ  ስራ እውን እንዳይሆን  ያስተጓጉላሉ። »

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic