የሲፒጄይና የአፍሪቃ የመ/ብዙሃን ድጋፍ ሰጭ ድርጅት ጥሪ | ኢትዮጵያ | DW | 14.06.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የሲፒጄይና የአፍሪቃ የመ/ብዙሃን ድጋፍ ሰጭ ድርጅት ጥሪ

በኢትዮጰያ የፀረ ሽብር ህግ ተከሰው የታሰሩት ጋዜጠኞች እንዲለቀቁ ለጋዜጠኞች መብትና ለመገናኛ ዘዴዎች ነፃነት የሚታገሉ ሁለት ድርጅቶች ጠየቁ ። ዓለም ዓቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት በእንግሊዘኛው ምህፃር CPJ ና በአፍሪቃ ለግልና

Logos des Committee to Protect Journalists (www.cpj.org), eine weltweit agierende NGO mit Sitz in New York, die für den Schutz von Journalisten und für Pressefreiheit kämpft.

በኢትዮጰያ የፀረ ሽብር ህግ ተከሰው የታሰሩት ጋዜጠኞች እንዲለቀቁ ለጋዜጠኞች መብትና ለመገናኛ ዘዴዎች ነፃነት የሚታገሉ ሁለት ድርጅቶች ጠየቁ ። ዓለም ዓቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት በእንግሊዘኛው ምህፃር CPJ ና በአፍሪቃ ለግልና ለነፃ ሚድያ ባለቤቶች እገዛ የሚያደርገው Africa Media initiative የተባለው ተቋም በጋራ ባወጡት መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት ጋዜጠኞችን እንዲፈታ ጠይቀዋል ። የየፀረ ሽብር ህግ ደግሞ የንግግር ነፃነትን የሚቃረን በመሆኑ እንዲሻሻል ጥሪ አቅርበዋል ። የሁለቱ ድርጅቶች ባለሥልጣናት አዲስ አበባ ሄደው ጉዳዩን ላነጋገሯቸው የኢትዮጵያ የኮምኒክሽን ሚኒስትር ማንሳታቸውንም አስታውቀዋል ። ስለዚሁ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው የCPJ ምክትል ሃላፊ ን አነጋግሬያቸዋለሁ ።
ባለፈው ሳምንት አርብ አዲስ አባባ ውስጥ ከኢትዮጵያ የኮሚኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ በረከት ስምዖን ጋር የተነጋገሩት የ CPJ የቦርድ አባል ቻርሌይን ሃንተር ጋውልት የCPJ ምክትል ሃላፊ ሮበርት ማሆኒና የ Africa Media initiative የቦርድ አባል ዴሌ ኦሎጄ ናቸው ። የCPJ ምክትል ሃላፊ ሮበርት ማሆኒ አዲስ አበባ ውስጥ የተካሄደው ውይይት ዓላማ የሁለቱን ድርጅቶች ስጋት ማሳወቅ እንደነበረ ለዶቼቬለ ተናግረዋል


« የውይይቱ ዓላማ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመገናኘት በኢትዮጵያ የጋዜጠኞች መታሰር እንዲሁም የፀረ ሽብርን ህግ ጋዜጠኞችን ለማሰር መጠቀም ያሳደረብንን ስጋት መግለፅ ነበር ።  እናም የኢትዮጵያ መንግሥት በአሁኑ ሰዓት የታሰሩትን ጋዜጠኞች እንዲፈታና የንግግር ነፃነትን የሚጎዳውን የፀረ ሽብር ህግ አጠቃቀም እንደገና እንዲያጤነው ጥሪ አቅርበናል ።»
በ CPJ መግለጫ መሠረት ኢትዮጵያ ውስጥ 7 ጋዜጠኞች ታስረዋል ።  ኢትዮጵያ በአፍሪቃ ጋዜጠኞችን በማሰር ከኤርትራ ቀጥሎ 2 ተኛነቱን ደረጃ እንደምትይዝ ድርጅቱ በመግለጫው አመልክቷል ። በእስር ላይ ከሚገኙት ጋዜጠኞችም 3 ት ኢትዮጵያውንና 2 ስዊድናውያን ጋዜጠኞች በፀረ ሽብር ህግ ተከሰው መታሰራችውንም ድርጅቱ አስታውቋል ።
የCPJ ና የ Africa Media initiative ሃላፊዎች በአዲስ አበባ ቆይታቸው የጋዜጠኞች መታሰር ያሳደረባቸውን ስጋትና መሻሻል አለባቸው ያሉትን ሲያቀርቡ ከመንግስት በኩል የተሰጣቸው መልስ ግን ከዚህ ቀደም ከሚያውቁት የተለየ እንዳልነበረ ነው ማሆኒ የተናገሩት ።

business conference camera journalism © picsfive #16855152

« ከሚኒስትር በረከት ጋር ከ2 ሰዓት በላይ የወሰደ ውይይት አካሂደናል ። ባለሥልጣኑ መንግሥት ከዚህ ቀደም ያለውን ነው የደገሙት ። ጋዜጠኞች የተያዙት በፅሁፎቻቸው ህጉን ጥሰው ሳይሆን በፀረ መንግሥት ሴራ በመካፈልና ከፀጥታ ጋር በተያያዙ አንዳንድ ጥፋቶች መሆኑን ነው የነገሩን »  
እንደ ማሆኒ የ የCPJ ና የ Africa Media initiative ሃላፊዎች በአዲስ አበባ ቆይታቸው የታሰሩትን  ጋዜጠኞች ለመጎብኘት እንዲፈቀድላቸው የኢትዮጵያ የኮምኒኬሽን ሚኒስትርን ጠይቀው ነበር ። ይሁንና ጋዜጠኞቹን ሳያዩ ነው ከኢትዮጵያ የተመለሱት ።

«የኮምኒኬሽን ሚኒስትሩ ባለሥልጣን ጥያቄአችንን ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የእስር ቤት ባለሥልጣናት እንደሚያስተላልፉ ነግረውን ነበር ። ሆኖም ከዚያ በኋላ ከእስር ቤቱ ሃላፊዎችም ሆነ ከኮሚኒኬሽን ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የሰማነው ነገር የለም ። በቀጥታ አይቻልም አላሉንም ። ሆኖም እዚያ በቆየንበት ጊዜ ከታሰሩት ጋዜጠኞች አንዳቸውንም መጎብኘት አልቻልንም ። »

media interview © wellphoto #34433458


ከቡድኑ አንዱ እቅድ ጋዜጠኞችን መጎብኘት ነበርና ባለመሳካቱ ማሆኒ እንዳሉት ቢያዝኑም  በቀጥታ መንግሥት ዘንድ በመሄድ ስጋታቸውን በመግለጻቸው ተደስተዋል ። የታሰሩትን ጋዜጠኞች ማየት ያልቻሉት የቡድኑ አባላት ሥራ ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞችን ግን አነጋግረዋል ።በዚሁ ወቅት በመንግሥት ማተሚያ ቤቶች ተረቆ በቀረበ ውል ውስጥ የተካተቱት ለውጦች ጋዜጠኞችን እንደሚያሳስቧቸውም ሰምተዋል ። ልዑካኑ የሰጡትን አስተያየትና የጋዜጠኞቹንም ስጋት መንግሥት በጥሞና ያጤነዋል የሚል ተሳፋ እንዳላቸው ማሆኒ አስረድተዋል ።
«የታሰሩትን ጋዜጠኞች ጉዳይ እንደገና ፈትሸው ይለቋቸዋል ብዮ ለማሰብ እፈልጋለሁ ። ማናቸውም ጋዜጠኛ ባቀረበው ወይም ባቀረበችው ፅሁፍ ምክንያት መታሰር የለባቸውም ። የኢትዮጵያ የግል ጋዜጦች ስጋቶች በመንግሥት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲታይ እፈልጋለሁ ይህን መልዕክት ለመንግሥት አስተላልፈናል ። እኛ ከሰጠነው አስተያየት ጋር የሚጣጣም ቀና  እርምጃ ይወስዳል ብለን ተስፋ እናደርጋለን ኳሷ ሜዳ ነው ያለችው ። »

ሂሩት  መለሰ

ነጋሽ  መሐመድ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 14.06.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15DNr

ተዛማጅ ዘገባዎች

 • ቀን 14.06.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15DNr