1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በይፋ ተመሠረተ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 27 2012

የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ዛሬ በይፋ ሲመሰረት አቶ ደስታ ሌንዳሞ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተመርጠዋል። 190 አባላት ያሉት የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ዛሬ ጠዋት ከተመሠረተ በኋላ የክልሉን ሕገ መንግሥት በሙሉ ድምጽ አጽድቋል። አቶ ሰለሞን ላሌ ዛሬ የተመሠረተው የክልሉ ምክር ቤት አፈጉባኤ ሆነዋል።

https://p.dw.com/p/3enC7
Äthiopien Hawassa Vorbereitungen zu Sidama-Referendum
ምስል DW/Solomon Muche

የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በይፋ ተመስርቶ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክን ተቀላቀለ። የሲዳማ ክልል የፌድራል መንግሥቱ አስረኛ ክልል ሆኗል። የቀድሞው የሲዳማ ዞን አስተዳዳሪ ደስታ ሌዳሞ የመጀመሪያው ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተመርጠዋል። የሲዳማ ክልል የምሥረታ መርሐ ግብር የብሔሩ ፖለቲከኞች፣ የፌድራል መንግሥት እና የደቡብ ክልል ተወካዮች በተገኙበት በዛሬው ዕለት በሐዋሳ ከተማ ተካሒዷል። የዛሬው የሲዳማ ክልል ከነባሩ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ሥልጣን በይፋ የተረከበው ባለፈው ሰኔ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ነበር። 
190 አባላት ያሉት የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ዛሬ ጠዋት ከተመሠረተ በኋላ የክልሉን ሕገ መንግሥት በሙሉ ድምጽ አጽድቋል። የሐዋሳ ምክር ቤት፣ የሲዳማ ዞን ምክር ቤት እና በደቡብ ክልል ምክር ቤት የሲዳማ ተወካዮች የአስረኛው ክልልን ምክር ቤት በአባልነት ተቀላቅለዋል። የቀድሞው የሲዳማ ዞን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ሰለሞን ላሌ ዛሬ የተመሠረተው የክልሉ ምክር ቤት አፈጉባኤ ሆነው ተመርጠዋል።

Äthiopien SNNPR Konferenz zur Sidama-Zone
ሲዳማ ከነባሩ ክልል ሥልጣን የተረከበው የተረከበው ባለፈው ሰኔ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ነበርምስል DW/S. Wegayehu

የክልሉ ሰንደቅ ዓላማ ከላይ ወደ ታች አረንጓዴ፣ ሰመያዊ እና ቀይ ቀለሞች በቅደም ተከተል የተደረደሩበት ሲሆን መሐከሉ ላይ አራት ነጭ ኮከቦች ይገኛሉ።። የክልሉ መንግሥት 16 የካቢኔ አባላት ይኖሩታል። የሲዳማ ዞን አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ደስታ ሌዳሞ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተመርጠዋል።

የምሥረታ መርሐ ግብሩ በሐዋሳ ስታዲየም ሊካሔድ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በድምፃዊ ሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያ እና በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ በሐዋሳ ሚሊኒየም አዳራሽ ውስጥ እንዲወሰን ተደርጓል።

“ሲዳማ ከጥንት ጀምሮ የራሱን አካባቢ ካለ ማንም ጣልቃ ገብነት በማስተዳደር የራሱን ጉዳዮች በራሱ ሲወስን፤ በቋንቋው እና በባሕሉ ሲኮራ የነበረ ሕዝብ ነው” ያሉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ “በተደራጀም ባልተደራጀም መልኩ” ሲታገል መቆየቱን ገልጸዋል። 

የቀድሞው የኢትዮጵያ መሪ መንግሥቱ ኃይለማርያም ሥልጣን ላይ በነበሩባቸው አመታት የብሔሩ ልሒቃን የሚያቀርቡትን ጥያቄ ለማሳካት የሲዳማ አርነት ንቅናቄን እስከመመስረት ደርሰዋል። ደርግ ወድቆ ኢሕአዴግ ሥልጣን ሲይዝም የሲዳማ ጥያቄ ሳይመለስ መቆየቱን አቶ ደስታ በዛሬው መርሐ ግብር ላይ መለስ ብለው አስታውሰዋል። 

አቶ ደስታ ኢሕአዴግ “የሲዳማን ስነ ልቦና ሳያውቅ በእጅ አዙር ለሚፈፅመው ብዝበዛ እንዲያመቸው ብቻ በማሰብ በደቡብ ኢትዮጵያ የሚኖሩ ሕዝቦች አንድ ላይ በማሰባሰብ ለመምራት በመሞከሩ የሲዳማ ራሱን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ከመቶ አመት በኋላም ቢሆን ዋጋ እያስከፈለ ቀጥሎ በተለያዩ ጊዜያት ውድ ልጆቹን ገብሯል። ብዙዎች ታስረዋል፤ ተሰቃይተዋል፤ ተፈናቅለዋል“ ሲሉ ተደምጠዋል። 

Äthiopien: Sidama stimmen über Autonomie ab
ኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሔደ ሕዝበ-ውሳኔ ድምፅ ከሰጡ የዞኑ ነዋሪዎች  ከ98 በመቶ በላይ የሲዳማ ክልል እንዲመሰረት ደግፈዋልምስል AFP/M. Tewelde

አቶ ደስታ ለሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምሥረታ የብሔሩን ትግል እና ከኢሕአዴግ ውስጥ ፈንቅሎ ወጥቷል ያሉትን “የለውጥ አመራር“ ሚና ጠቅሰዋል። የሲዳማ ዞን ክልል ለመሆን ያቀረበውን ጥያቄ ባለፈው ኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሔደው ሕዝበ-ውሳኔ ድምፅ ከሰጡ የዞኑ ነዋሪዎች  ከ98 በመቶ በላይ ደግፈው ነበር። 
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ለ130 አመታት የዘለቀ ያሉት ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱን ካስታወሱ በኋላ ሥራ አጥነት እርሳቸው የሚመሩት ክልላዊ መንግሥት ፈተና እንደሚሆን ገልጸዋል።

“በአዲሱ ክልል የሚኖሩ ዜጎች ሁሉም ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተከብረውላቸው በእኩል የመሳተፍ እና የመጠቀም መብትም ይኖራቸዋል። የመንግሥት ድርሻ በክልሉ የሚኖሩ የልማት አቅሞች በማቀናጀት ሁሉም በዝንባሌ እና በአቅሙ ልክ የሚሳተፍበት ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይሆናል። በዋናነት የአዲሱ ክልል ፈተና ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር ሲሆን፤ ኪራይ ሰብሳቢነት እና ጎሰኝነትን ታግሎ በማሸነፍ ዕኩል ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ይሆናል“ ብለዋል። 

ርዕሰ መስተዳድሩ “የልማት ጸር የሆኑ ሌብነትን፣ አካባቢያዊነትን፣ ጎሰኝነትን እና ኋላ ቀርነትን በመጸየፍ ዕኩል ተጠቃሚነት የሚያደርጉ አሰራሮችን ለመተግበር የሚደረጉ የድርጅት እና የመንግሥት ጥረቶችን እንድትደግፉ እና ሥራ ሳይመርጡ በሚፈጠሩ ዕድሎች ተሳታፊ እና ተጠቃሚ ለመሆን እንድትዘጋጁ“ የሚል ጥሪ አቅርበዋል። 

በዛሬው የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምሥረታ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው እና የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካና ሲቪክ ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ አለሙ ስሜ ተገኝተዋል። 

እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ