የሱዳን ፖለቲካዊ ቀውስ | አፍሪቃ | DW | 08.06.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የሱዳን ፖለቲካዊ ቀውስ

ከሁለት ዓመት በፊት ይፋ በተደረገው መሠረት የሕዝቧ ብዛት 40,5 ሚሊየን ይገመታል፤ ከአፍሪቃ በቆዳ ስፋቷ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው የሱዳን ሪፐብሊክ፤ በሰባት አዋሳኝ ሃገሮች ተከባለች። ግብፅ፣ ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፑብሊክ፣ ቻድ እና ሊቢያ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:17

«እገዳ እና ሽምግልና»

የአባይ ወንዝ ከሁለት የሚከፍላት ሱዳን በምሥራቅ በኩል ግዛቷ ከቀይ ባሕር ጋር በመያያዙ አፍሪቃ እና መካከለኛው ምሥራቅን የምታገናኝ ድልድይም ያደርጋታል። በዳቦ ዋጋ መናር ሰበብ የሱዳን ሕዝብ ተቃውሞ ተጠናክሮ ለ30  ዓመታት ሥልጣን ላይ የከረሙትን ወታደራዊ መሪ ፊልድ ማርሻል ኦማር ሀሰን አህመድ አል በሺርን ከመንበራቸው ሲያወርድ እንዳጀማመሩ እንደሚቀጥል ታስቦ ነበር። መንበራቸውን የተቆጣጠረው ወታደራዊ ምክር ቤት ሥልጣን ለሲቪል አስተዳደር እንዲያስረክብ የሚደረገው ጥያቄ ግን ሰላማዊውን ለውጥ አፍሪቃ ውስጥ ወደተለመደው የዜጎች ደም ማፋሰስ አሸጋገረው።  ለወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥትም ሆነ አገዛዝ እንግዳ ባልሆነችው ሱዳን ሥልጣን ላይ የወጣው ኃይል በዋዛ ከምሁራን እና ዜጎች የሚቀርብለትን እስከምርጫ ሊያደርስ የሚችል በሲቪል የሚመራ የሽግግር መንግሥት የመመሥረት ጥያቄ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ የከበደው መስሏል።

በሕዝባዊ ግፊት ሱዳን ውስጥ ሊከተል የሚችለው ለውጥ በሱዳን ብሔራዊ ፍላጎት እና መሻት ላይ ብቻ የሚያበቃ እንዳልሆነ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ። የኻርቱም ፖለቲካዊ ለውጥ በምሥራቅ አፍሪቃ ባሉ አጎራባች ሃገራት ብቻ ሳይሆን ቀይ ባሕርን ተሻግሮም ሳውድ አረቢያ፣ ቀጠር እና ቱርክ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ይገመታል። ለዚህም ይመስላል የአልበሽርን አስተዳደር በቃኝ ካለው ሕዝብ ጎን ቆሞ እሳቸውን ከመንበራቸው ያነሳው ወታደራዊ ምክር ቤት ከተቃዋሚዎች ጋር ያለማንም ጣልቃ ገብነት ድርድር ሲያደርግ ቆይቶ ካለፈው ሳምንት ወዲህ የሆነው ሁሉ የሆነው።

ወታደራዊው ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ አደባባይ ለተቃውሞ የተሰባሰቡ ዜጎችን በኃይል ለመበታተን የወሰደው የኃይል ርምጃ የአንድ ሰው ሕይወት በመቅጠፍ ጀምሮም እስከ አሁን የተገደሉት ብዛት እያወዛገበ ነው። ተቃዋሚዎች የተገደሉት ከ100 በላይ ናቸው ይላሉ፤ መንግሥት ከ40 አይበልጥም በሚል ይከራከራል። ያም ሆነ ይህ የሲቪል መንግሥት ለመመስረት መንገድ እንዲያመቻች ከውስጥ ከውጭም ውግዘት እና ግፊት የጠነከረበት ወታደራዊ ምክር ቤት አንዴ ድርድሩን በማቋረጥ ስምምነቶችን ሲሰርዝ፤ ቆየት ብሎም ዳግም ለድርድር ጥሪ ሲያቀርብ ነው ሳምንቱን ያገባደደው።

የሱዳንን መንበረ መንግሥት የተቆናጠጠው ወታደራዊ ምክር ቤት የሲቪል አስተዳደር እንዲመሠረት ግፊት ከሚያደርጉት የሱዳን የተቃዋሚ ኃይል መሪዎች ጋር የጀመረውን ድርድር ሰኞ ማምሻውን ማቋረጡን እና ከዘጠኝ ወራት ባልበለጠ ጊዜ ምርጫ ለማካሄድ መዘጋጀቱን አሳወቀ። ውሳኔው በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ተቀባይነት ያጣው የወታደሮች ስብስብ አንድ ቀን አድሮ እንደገና ከተቃዋሚዎች ጋር ድርድሩን ለመቀጠል መዘጋጀቱን አመለከተ። የተቃዋሚዎቹን ይሁንታ ግን አላገኘም።

በብሪታንያ አሳሳቢነት የሱዳን ወታደሮች በዋና ከተማ ኻርቱም ከመከላከያ ሚኒስቴር ደጃፍ ለተቃውሞ የተሰባሰቡትን  ዜጎች ከአካባቢው ለማባረር የወሰዱትን የኃይል እርምጃ ለመመርመር ማክሰኞ ዕለት በዝግ ተሰበሰበው የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በቻይና እና ሩሲያ እምቢተኝነት ድርጊቱን ማውገዝ አልተቻለውም። የውጭ ጣልቃ ገብነት የሱዳንን የፖለቲካ ቀውስ ይበልጥ ሊያባብሰው ይችላል የምትለው ሩሲያ በተለያየ ጎራ የቆሙት የሀገሪቱ ፖለቲከኞች ለብሄራዊ ድርድር ዝግጅዎች እንዲሆኑ ጥሪዋን አቅርባለች። 

ሱዳን አጎራባቾቿ የውስጥ ጉዳያቸው የየራሱ አሳሳቢ ይዞታ ላይ ባለበት በዚህ ወቅት ለገባችበት የፖለቲካ ቀውስ ከውይይት እና ድርድር የተሻለ አማራጭ እንደሌላት የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂያዊ ጥናት ተቋም ባልደረባ የሆኑት የፖለቲካ ተንታኝ አቶ አበበ አይነቴም ይናገራሉ።

«በሱዳን ያለውን ሁኔታ ወደ መፍትሄ ሊወስድ የሚችለው አሁንም በሱዳን ያሉ ኃይሎች በመነጋገር እና በመግባባት በሀገሪቱ ዘላቂ መረጋጋት ሊያመጣ በሚችል ጉዳይ ላይ እስካልተስማሙ ድረስ አሳሳቢ እና አስቸጋሪ መሆኑ አይቀርም።»

የሱዳን ፖለቲካዊ ውዝግብ ያሳሰበው የአፍሪቃ ሕብረት የሰላም እና የፀጥታ ምክር ቤት ሐሙስ ዕለት ወታደራዊው ምክር ቤት ሲቪል መር አስተዳደር ለመመስረት ዝግጁነት ካላሳየ በቀር ሀገሪቱን ከሕብረቱ ማናቸውም እንቅስቃሴዎች ማገዱን አሳውቋል። የሕብረቱን ውሳኔ ደቡብ አፍሪቃ እንደምትደግፍ ወዲያው ነው ያስታወቀችው። በመንግሥታቱ ድርጅት የደቡብ አፍሪቃ ቋሚ ተጠሪ ጄሪ ማቲው ማቲጂላ፤

«በመጀመሪያ የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት የአፍሪቃ ሕብረት የሰላም እና ፀጥታ ምክር ቤት ሱዳንን ለማገድ መወሰኑን ይደግፋል።  በተጨማሪም ምክር ቤቱ ተቀናቃኞቹን ወገኖች ዳግም ወደ ድርድር እንዲመለሱ ያቀረበውን ጥሪም አብሮ ያቀርባል። ሁሉን በማካተት ሥልጣን ወደ ሲቪል አስተዳደር አስተላልፊ በሚለው ላይ ባስቸኳይ ተስማሙ። በዚህ ሂደትም ጥቃት እየቀነሰ እንደሚሁድ፣ እስረኞች እንደሚፈቱ እና ወደ ድርድር እንደሚመለሱ ተስፋ እናደርጋለን።»

የአፍሪቃ ሕብረት ሥልጣን ላይ በሚገኘው ወታደራዊ  ምክር ቤት የኃይል ርምጃ እና አቋም ምክንያት በሱዳን ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ የደገፉለት እንዳሉ ሁሉ፤ ርምጃው ችግሩን ሊያባብስ ይችላል በሚል  ስጋታቸውን የገለፁም አሉ። የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር ከአንድ ቀን ቀደም ብሎ ባወጣው መግለጫ የሕብረቱ አቋም የሱዳንን ቀውስ እንዳያባብስ አሳስቧል። የአፍሪቃ ሕብረት ርምጃም ሆነ ውሳኔ ከመተዳደሪያ ደንቡ የተነሳ መሆኑን አቶ አበበ ያስረዳሉ፤

«እንግዲህ አፍሪቃ ሕብረት የወሰነው ውሳኔ በአፍሪቃ ሕብረት ቻርተር መሠረት ነው። በአንድ ሀገር ሕዝባዊ ምርጫ ወደ ሥልጣን ሳይመጣ ሲቀር ያን ሥልጣን ላይ ያለውን ወገን ከማንኛውም አይነት እንቅስቃሴ ያገልላል እና፤ ያንን ተከትሎ ነው የወሰደው።»

Afrikanische Union Logo

የፖለቲካ ተንታኙ እንዳመለከቱት ኢትዮጵያ ወደ ሽምግልናው አጋድላለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ትናንት ዓርብ ወደ ኻርቱም በማምራት ከወታደራዊ ምክር ቤት መሪዎች እንዲሁም የተቃውሞ እንቅስቃሴን ከሚያስተባብሩት የነፃነት እና ለውጥ ኃይሎች አባላት ጋር መወያየታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ፎቶ አስደግፎ በትዊተር ባሰራጨው መረጃ አመልክቷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአካባቢው ኢትዮጵያ ሰላምን ለማምጣት ቁርጠኛ መሆኗን በማመልከት፤ የሚፈለገውን ሰላም ለማግኘት ደግሞ አስፈላጊው አንድነት መሆኑን በአፅንኦት መግለጻቸውም ተጠቅሷል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኻርቱም ጉዞም ሆነ የማደራደር ርምጃ ኢትዮጵያ በአካባቢው ባለው የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ማለትም ኢጋድ ሊቀመንበርነት ይሁን በቅርብ ጉርብትና ግን የተገለጸ ነገር የለም። ተንታኞችን ግን የፖለቲካ ማሻሻያ ለውጥ አራማጁ ወጣቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በአፍሪቃ ቀንድ እና አካባቢው በሚገኙ ሃገራት መካከል መግባባትን ለማጠናከር የሚያደርጉት ጥረት አካል አድርገውታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ትናንት ኻርቱም እንደገቡ በቅድሚያ ከቡርሃኒ እና ከሌሎች ጀነራሎች ጋር መወያየታቸውን ያመለከቱት ዘገባዎች የፈጣን ድጋፍ ኃይል የተባለው ወታደራዊ ኃይል ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት ጀነራል መሐመድ ሃማድ ዳጋሎ ስብስቡን በሚያሳየው ፎቶ ላይ አለመታየታቸው በቀና የተወሰደ አይመስልም። የዓለም አቀፉ የቀውስ ጉዳዮች ጥናት ተቋም ባልደረባ ረሺድ አብዲም በትዊተር «አጋጣሚውም ሱዳን ውስጥ ተቃዋሚዎች ላይ ለሚፈጸሙ ጥቃቶች ተጠያቂ መሆኑ የሚነገርለትን  የፈጣን ድጋፍ ኃይል የሚመሩት ዳጋሎን ሆን ተብሎ ከዓይን የመሰወር ርምጃ» እንደሆነ ጠቁመዋል። ሐሙስ ዕለት የሱዳን የተቃውሞ እንቅስቃሴ መሪዎች ይህ የፈጣን ድጋፍ ኃይል ባስቸኳይ እንዲበታተን እና መዋቅሩም እንዲፈርስ ጠይቀዋል።

የሱዳን የዶክተሮች ማዕከላዊ ኮሚቴ በዚህ ሳምንት ብቻ ሱዳን ውስጥ የተገደሉት ዜጎች ቁጥር 113 ደርሷል ከ500 የሚበልጡ ደግሞ ተጎድተዋል ብሏል። የኃይል ርምጃውን አጥብቀው የኮነኑት የተመድ እና የአውሮጳ ኅብረት፤ የአፍሪቃ ሕብረት በወታደራዊ ምክር ቤቱ ላይ የወሰደውን የማግለል ርምጃ ሙሉ በሙሉ ደግፈዋል። ጀነራሎቹ ሁሉንም የሚያካትት ድርድር እንዲያደርጉ ግፊቱ የበረታባቸው ከአረብ ሃገራት ጭምር ነው። ከእነዚህ መካከልም የኻርቱም መንግሥት ዋነኛ ደጋፊዎች በመሆናቸው የሚታወቁት ሳውድ አረቢያ እና ዩናይትድ አረብ ኤሜሬቶች ይጠቀሳሉ። ለወራት መንቀሳቀስ ያቃተው የሱዳን ኤኮኖሚን ለማጠናከርም 3 ቢሊየን ዶላር ላስቸኳይ ጊዜ ርዳታ ለመስጠት ቃል ገብተዋል።

የአፍሪቃ ሕብረት በተለያዩ ጊዜያት በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ለውጥ በተደረገባቸው ሃገራት ላይ ተመሳሳይ የማግለል ውሳኔ ሲያሳልፍ ታይቷል። ሕብረቱ የሚወስዳቸው ርምጃዎች ምን ያህል የተፈለገውን አዎንታዊ ውጤት አስገኝተዋል የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው። የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂያዊ ጥናት ተቋም ባልደረባ የሆኑት የፖለቲካ ተንታኝ አቶ አበበ አይነቴ እንደሚሉት ውጤቱ የሚመዘነው እንደየሀገሩ የፖለቲካ እና ነባራዊ ሁኔታ ነው።

በአፍሪቃ ሕብረት የተወሰደው ርምጃም ሆነ በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የተደረገው የማሸማገል ጥረት የወታደራዊ ምክር ቤቱን አቋም አለዝቦ የሱዳን የፖለቲካ ውዝግብ መፍትሄ ማግኘቱ ውሎ አድሮ የሚታይ ነው የሚሆነው።

ሙሉ ቅንብሩን ከድምፅ ዘገባው ያድምጡ።

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic